‹‹ በሁለቱ ቀናት ውስጥ 23 ተጨዋቾች እንመርጣለን›› ዮሃንስ ሳህሌ

ዛሬ በኢንተር ኮንቲኔንታል አዲስ በተካሄደው ጋዜጣዊ መግለጫ የብሄራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ፣ የቡድን መሪው አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ ፣ ረዳት አሰልጣኙ ፋሲል ተካልኝ እና የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ አሊ ረዲ ተገኝተዋል፡፡ ከጋዜጠኞች የቀረቡትን ጥያቄዎችንም መልሰዋል፡፡

በጋዜጣዊው መግለጫ ላይ የአሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌን ንግግሮች አጠቃለን እንዲህ አቅርበናቸዋል፡፡

 

ስለ ምርጫው

‹‹ ባለን አጭር ጊዜ 44 ተጫዋቾችን መርጠን ባለፈው ሳምንት አሳውቀናል፡፡ ብዙዎቹ ወደ ሆቴል እየገቡ ነው፡፡ ምሽት ላይ ተጠቃለው እንደሚገቡ እንጠብቃለን፡፡ ባዘጋጀነው እቅድ መሰረት ነገ 2፡30 ላይ ልምምድ እንጀምራለን፡፡ ቡድኑን በ4 በመክፈልና እርስ በእርስ ለሁለት ቀናት በማጫወት በአሰልጣኝ ቡድኑ ውሳኔ መሰረት 23 ተጫዋቾችን እንመርጣለን፡፡ ሁኔታዎች ከተስተካከሉ ወደ ባህርዳር ሄደን ከሌሴቶ ጋር የሚደረገውን ጨዋታ እናካሂዳለን፡፡

‹‹ 44 ተጫዋቾች የመረጥኩት እኔ ነኝ፡፡ ፋሲል ተካልኝ በክለብ ስራ ላይ ስለነበር ሙሉ ለሙሉ ተጫዋቾችን የመረጥኩት እኔ ነኝ፡፡ የግብ ጠባቂ ምርጫ ላይ ከአሊ ረዲ ተወያይተናል፡፡ አመቱን ሙሉ ጨዋታዎችን ስመለከት ስለቆየሁ ምርጫው አላስቸገረኝም፡፡ ያስቸገረኝ የጥራት ጉዳይ ነው፡፡ እንደሚታወቀው በየቦታው ጠንካራ የሚባሉት ተጫዋቾች የውጭ ዜጎች ናቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ተጫዋቾች ጥሩ የሚሆኑት ክለቡ ጠንካራ ስለሆነ ይሆናል፡፡ በተቃራኒው ብቃታቸውን የክለቡ ደካማ አቋም የሚሸፍንባቸው ተጫዋቾችም አሉ፡፡ ስለዚህ 44 ተጫዋቾች በውድድር ዘመኑ አቋማቸው መርጠን 23 የተሻሉ ተጫዋቾችን ለመለየት ተገደናል፡፡ የምርጫ ጉዳይ ላይ በመገናኛ ብዙሃን የሚነገሩ ነገሮችን ስሰማ ነበር፡፡ ምርጫ ለመምረጥ መወዳደር ያስፈልጋል፡፡ ያልተወዳደረ ወይም ያልተጫወተን ተጫዋች በስሙ ብቻ መምረጥ አልችልም፡፡

‹‹ በ4 እና 5 የወዳጅነት ጨዋታዎች ተጫዋቾችን መምረጥ ብንችል ደስ ይለን ነበር፡፡ ነገር ግን ስራዎችን የምንሰራው ከጊዜ አንፃር ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በየቦታው አራት ተጫዋቾችን መርጠን እርስ በእርስ ለማጫወት ተገደናል፡፡ ››

 

ዲሲፕሊን

‹‹ ስነ-ስርአት ላይ አንደራደርም፡፡ በምንም መልኩ ስርአት አልባ ከሆነ ተጫዋች ጋር መስራት አንችልም፡፡ የሃገርን ኃላፊነት ተሸክሞ ስነ-ስርአት ከሚያበላሽ ጋር ድርድር አይኖርም፡፡ ››

 

ከሃገር ውጪ ስለሚመጡ ተጫዋቾች

‹‹ ከ44 ተጫዋቾች 23 ተጫዋቾችን ከመረጥን በኋላ ከውጪ 5 ተጫዋቾችን ጨምረን 28 ተጫዋቾች እንይዛለን፡፡ ከቱርክ (ዋሊድ አታ) ፣ ከደቡብ አፍሪካ (ጌታነህ ከበደ) እንዲሁም ከግብፅ (ሳላዲን ሰኢድ ፣ ኡመድ ኡኩሪ እና ሽመልስ በቀለ) 23ቱን ተጫዋቾች ይቀላቀላሉ፡፡ ከ23 ተጫዋቾች በተጨማሪ ከውጭ የሚመጡትን የያዝንበት ምክንያት በቻን ውድድር ላይ እነዚህ መሳተፍ ስለማይችሉ ነው፡፡

‹‹በየሱፍ ሳሌህ ቦታ ላይ በርካታ ተጨዋቾች ስላሉ ወቅታዊ አቋሙን የማናውቀውን ተጫዋች መምረጥ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ጌታነህ ፣ ኡመድ እና ሳላዲን የሚመጡት በነሱ ደረጃ የሚጫወት ጥራት ያለው አጥቂ ሃገር ውስጥ ባለመኖሩ ነው፡፡

‹‹ ዛሬ (ግንቦት 24) ወደ ሆቴል የማይገቡ ተጫዋቾች ለነገው ልምምድ መድረስ ስለማይችሉ በብሄራዊ ቡድኑ ውስጥ አይካተቱም፡፡ ››

 

የተጫዋቾች አመራረጥ

‹‹ የእግርኳስ ጨዋታዎችን የምመለከተው እንደሙያተኛ ነው፡፡ የብሄራዊ ቡድን አሰልጣን ሆንኩም አልሆንኩም የተጫዋቾችን ብቃት የምመለከተው እንደ አሰልጣን ነው፡፡

‹‹ እያንዳንዱ አሰልጣኝ የየራሱ አመለካከት አለው፡፡ ሰውነት ቢሻው ተጫዋቾችን የሚመለከትበት መንገድ የተለየ ነው፡፡ ባሬቶም እንደዛው፡፡ ስለዚህ ዮሃንስ ሳህሌም የራሱ የሆነ አመለካከት እና ነገሮችን የሚያይበት መንገድ አለው፡፡ ተጫዋቾችን የማልመርጠው ስለማዳላ አይደለም፡፡ ለራሴ የጨዋታ እቅድ እና ዘይቤ የሚስማማውን ተጫዋች መርጫለሁ፡፡ ››

 

ስለ ስራ ነፃነት

‹‹ የስራ ነጻነት አለኝ፡፡ ነገር ግን በፌዴሬሽን ውስጥ የአሰራር ችግሮች አሉ፡፡ ነገር ግን በቅርበት በመነጋገር ለችግሮች መፍትሄ እያገኘን ነው፡፡ አሁን እየሰራን ያለው አሰራር ከአሁን በፊት ያልተለመደ ነው፡፡ ከ8 ቀናት በፊት ተጫዋቾችን መርጬ አሳውቄያለሁ፡፡ ትጥቅ እንዲሟላ እና የሆቴሉ ነገርም ቀድሞ እንዲያልቅ ተደርጓል፡፡ ከአስተዳደር ሰዎች ጋር ግንኙነት የምናደርግበት መንገድም ተበጅቷል፡፡

 

ስለ ወዳጅነት ጨዋታው

‹‹ ምንም ሳንጫወት ወደ ዋና ውድድር ከመግባት የወዳጅነት ጨዋታውን ማድረግ ይጠቅመናል፡፡ አዳዲስ ተጫዋቾችን ለመፈተሸ እና የቡድኑን አቋም ሌሴቶ ላይ ከመፈተሽ ዛምቢያ ላይ መፈተሸ ይሻላል፡፡

‹‹ ከጨዋታዎቹ በኋላ በመሃል የአንድ ወር እረፍት ስለሚኖር እና የክለብ ውድድሮች በመጠናቀቃቸው ልምምድ ብቻ ማድረጉ ጥቅም የለውም፡፡ ስለዚህ ከኬንያ እና ሌሴቶ ጨዋታ በኋላ ከአስተዳደሩ ጋር በድጋሚ እንወያያለን፡፡ ››

 

ስለ አሰልጣኞች ቡድን

<< አሁን ያለው የአሰልጣኞች ቡድን (coaching staf) በቂ ነው ብለን እናምናለን፡፡ በዚህ አጭር ጊዜ መሰረታዊ የሆኑ የአካል ብቃት ፣ የስነ-ምግብ እና ስነ-ልቡና ችግሮችን ማስተካከል አንችልም፡፡ ጊዜው አጭር በመሆኑ ሰራን ለማለት ካለሆነ በቀር ያን ያህል አስፈላጊ አይደለም፡፡ መሰረታዊ የሆኑ የታክቲክ ፣ የስነ-ልቡና ፣ የአካል ብቃት እና አመጋገብ ስራዎች የሚሰሩት ከታች ባሉ የእድሜ እርከኖች ነው፡፡>>

ያጋሩ