ኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢ በኡመድ ኡኩሪ ግብ ነጥብ ተጋርቷል

 በ25ኛ ሳምንት የግብፅ ፕሪምየር ሊግ ኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢ ኢትሃድ አሌክሳንደሪያን አስተናግዶ 2 አቻ ሲለያይ ኢትዮጵያዊው የፊት መስመር ተሰላፊ ኡመድ ኡኩሪ አንድ ግብ አስቆጥሮ በሊጉ ያስቆጠራቸውን የግቦች መጠን 7 አድርሷል፡፡

ዋና አሰልጣኙ ሻውኪ ጋርብ በገዛ ፍቃዳቸው ከለቀቁ በኃላ በሙክታር ሙክታር እየተመራ የሚገኘው ኤል ኤንታግ በሁለተኛው ዙር ከፍተኛ የውጤት ማጣት ገጥሞት ላለመውረድ መታገል ጀምሯል፡፡ ከወራጅ ቀጠናው በአራት ነጥብ ብቻ ከፍ ያለው ክለቡ በሊጉ ለመቆየት የሚያደርገው ትግልም ቀጥሏል፡፡

ዛሬ ምሽት ካይሮ በሚገኘው አል ሰላም ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ ኤል ኤንታጎች በተጋጣሚያቸው ተብለጠው አምሽተዋል፡፡ ግብ በማግባት ቅድሚያውን የያዙት በተደጋጋሚ በፈጣን መልሶ ማጥቃት የባለሜዳዎቹን ግብ የፈተሹት እንግዶቹ ነበሩ፡፡ በጥሩ ቅብብል የመጣውን እድል መሃመድ ጌዶ በ16ኛው ደቂቃ በቮሊ ኳስ እና መረብን አዋህዶ ኢትሃድ አሌክስአንድሪያን መሪ አድርጓል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ማጥቃትን መሰረት ያደረገ አጨዋወት የተከተለው ኤል ኤንታግ ግቦችን ቢያስቆጥርም በእጅጉ የሳሳው የተከላካይ መስመሩ ዋጋ አስከፍሎታል፡፡ የቀድሞ የዛማሌክ ኮከብ መሃሙድ ፋታላህ በ59ኛው ደቂቃ በቅጣት ምት አስቆጥሮ ባለሜዳዎቹን አቻ ሲያደርግ በ71ኛው ደቂቃ መሃመድ ባዙካ በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር ዳግም የአሌክሳንደሪያውን ክለብ መሪ ማድረግ ችሏል፡፡ በ85ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት ተሻግሮ ፋታህ በግንባሩ የገጨውን ኳስ ከግቡ በቅርብ ርቀት የተገኘው ኡመድ ኡኩሪ በአክሮባት በማስቆጠር ቡድኑን ከመሸነፍ ታድጓል፡፡

ከወራጅ ቀጠናው ይበልጥ ለመራቅ ሙሉ ሶስት ነጥብ ማሳካት ይገባው የነበረው ኤል ኤንታግ ይህን ሳይፈፅም ቀርቷል፡፡

ክለቡ በውጤት ቀውስ ውስጥ ቢገኝም ኡመድ በግሉ የተሳካ የውድድር አመት ማሳለፉን ቀጥሏል፡፡ ኡመድ በ2013/14 የውድድር ዘመን በግብፅ ፕሪምየር ሊግ በዋዲ ደግላ መለያ 7 የሊግ ግቦች ያስቆጠረው ሳላዲን ሰዒድ ተከትሎ በሊጉ 7 ግቦችን በአንድ የውድድር ዘመን ያስቆጠረ ሁለተኛው ኢትዮጵያዊ ሆኗል፡፡

ኤል ኤንታግ በደረጃ ሰንጠረዡ ነገ ጨዋታውን ከመሪው አል አሃሊ ጋር የሚያደርገው ታንታን በግብ ክፍያ በልጦ በ24 ነጥብ 13ኛ መሆን ችሏል፡፡ አል አሃሊ አሁንም የሊግ ዋንጫ ድሉን ለመድገም የሚያገድው ያለ አይመስልም፡፡ ሰኞ ጨዋታው የሚያደርገው አሃሊ ከተከታዩ ምስር ኤል ማቃሳ በ10 ነጥቦች ርቆ ሊጉን በ64 ነጥብ እየመራ ይገኛል፡፡

የኡመድን ጎል ይመልከቱ   YouTube Link

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *