በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ19ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታዎች ንግድ ባንክ ደረጃውን ሲያሻሽል የወራጅ ቡድኖችን ፍንጭ የሰጡ ውጤቶችን ተመዝግበዋል፡፡
በ9 ሰአት ቦዲቲ ላይ በ ‹‹ደንጉዛ ደርቢ›› ወላይታ ድቻ አርባምንጭ ከነማን አስተናግዶ 1-1 አቻ ውጤት ተለያይተዋል፡፡ ግብ በማስቆጠር ቅድሚያውን የያዙት አርባምንጮች ሲሆኑ የወላይታ ድቻው ተከላካይ ተክሉ ታፈሰ ራሱ ላይ ግብ አስቆጥሯል፡፡ ለወላይታ ድቻ የአቻነቷን ግብ ከመረብ ያሳረፈው ግዛቸው ጊቻ ነው፡፡
አዲስ አበባ ላይ ከሜዳው ውጪ የተጫወተው ዳሽን ቢራ ደደቢትን ዮናታን ከበደ በግንባሩ ገጭቶ ባስቆጠረው ግብ 1-0 አሸንፎ ወሳኝ ሶስት ነጥቦችን ሰብስቧል፡፡ በተመሳሳይ ከዳሽን ቢራ በ1 ነጥብ ዝቅ ብሎ የሚገኘው መብራት ኃይልም አበበ ቢቂላ ላይ ሲዳማ ቡናን በፍቅረእየሱስ ተክለብርሃን ብቸኛ ግብ 1-0 አሸንፎ ጠቃሚ ሶስት ነጥብ አግኝቷል፡፡
ከወራጅ ቀጠናው እምብዛም ያልራቀው ሙገር ሲሚንቶ ወደ ሀዋሳ ተጉዞ ከሀዋሳ ከነማ ጋር ካለምንም ግብ 0-0 ሲለያይ በእለቱ የመጨረሻ ጨዋታ ኢትዮጵ ንግድ ባንክ ሀረር ሲቲን አሸንፎ ደረጃውን በአጅጉ አሻሽሏል፡፡ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የድል ግቦቹን ጫላ ድሪባ እና ደረጀ መንግስቱ ሲያስቆጥሩ ለሀረር ሲቲ ገዛኸኝ እንዳለ በቅጣት ምት አስቆጥሯል፡፡ ሽንፈቱን ተከትሎ ሀረር ሲቲ 12ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው መብራት ኃይል በ3 ነጥቦች ርቆ 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
ፕሪሚየር ሊጉን ቅዱስ ጊዮርጊስ በ55 ነጥብ ሲመራ ኢትዮጵያ መድን እና ሀረር ሲቲ የመጨረሻ ደረጃውን ይዘዋል፡፡