የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 25ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ይካሄዳሉ፡፡ ማክሰኞ እና ረቡዕ በሚደረጉት ጨዋታዎች ላይ በቅጣት እና በጉዳት የማይሰለፉ ፣ መሰለፋቸው አጠራጣሪ የሆኑ እና ከጉዳት እና ቅጣት ወደ ሜዳ የሚመለሱ ተጫዋቾችን እንዲህ አጠናቅረነዋል፡፡

የነገ ጨዋታዎች

አዲስ አበባ ከተማ ከ አዳማ ከተማ (08:30 ፤ አአ ስታድየም)

በነገው ጨዋታ ከሁለቱም በኩል በርካታ ተጫዋቾች በጉዳት አይሰለፉም፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ በኩል ዘሪሁን ብርሃኑ ፣ አቤል ዘውዱ ፣ ሙሃጅር መኪ እና ተክለማርያም ሻንቆ የማይሰለፉ ሲሆን የረጅም ጊዜ ጉዳት ያስተናገደው ዮናታን ብርሀነም ወደ ሜዳ አይመለስም፡፡

በአዳማ በኩል ተከላካዮቹ ተስፋዬ በቀለ ፣ ሞገስ ታደሰ እና ሲሳይ ቶሊ ፤ አማካዩ ብሩክ ቃለልቦሬን ፤ አጥቂዎቹ ሚካኤል ጆርጅ እና ታፈሰ ተስፋዬ የነገው ጨዋታ የሚያልፋቸው ተጫዋቾች ናቸው፡፡

አርባምንጭ ከተማ ከ መከላከያ (09:00 ፣ አርባምንጭ)

በአርባምንጭ በኩል ታገል አበበ እና ወንድወሰን ሚልኪያስ በጉዳት የነገው ጨዋታ ያመልጣቸዋል፡፡ ግብ ጠባቂው አንተነህ መሳ እና ሁለገቡ ጸጋዬ አበራ ከጉዳታቸው አገግመው ወደ ሜዳ እንደሚመለሱ ሲጠበቅ ላለፉት ረጅም ጊዜያት ለክለቡ አገልግሎት መስጠት ያልቻለው ተሾመ ታደሰም በነገው ጨዋታ ላይ የመሰለፉ ጉዳይ አጠራጣሪ ነው፡፡

በመከላከያ በኩል አወል አብደላ እና ሽመልስ ተገኝ ከነገው ጨዋታ ውጪ ሲሆኑ ከንግድ ባንክ በተደረገው ጨዋታ ጉዳት ያስተናገደው አቤል ማሞ ከቡድኑ ጋር አብሮ ቢጓዝም የመሰለፍ እድሉ 50/50 ነው ተብሏል፡፡ ምንተስኖት ከበደ ደግሞ ከጉዳት ወደ ሜዳ የሚመለስ ተጫዋች ነው፡፡

ሀዋሳ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና (09:00 ፤ ሀዋሳ)

በሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ባለሜዳው ሀዋሳ ከተማ የመላኩ ወልዴ እና መሳይ ጳውሎስን ግልጋሎት አሁንም በጉዳት ምክንያት ማግኘት ባይችልም የመሀመድ ሲይላ ወደ ሜዳ መመለስ ለቡድኑ እፎይታን የሚፈጥር ነው፡፡

ኢትዮጵያ ቡና የመስመር አጥቂው እየያሱ ታምሩ እና አማካዩ ኤልያስ ማሞን በጉዳት ሳይዝ የተጓዘ ሲሆን ከወልድያ በተደረገው ጨዋታ በጉዳት ተቀይሮ የወጣው አብዱልከሪም መሀመድ ከቡድኑ ጋር አብሮ ቢጓዝም የመሰለፍ እድሉ ዝቅተኛ ነው፡፡

ጅማ አባ ቡና ከ ወላይታ ድቻ (09:30 ፤ ጅማ)

ላለመውረድ በሚደረገው ፉክክር ላይ እየተሳተፉ የሚገኙትን ቡድኖች በሚያገናኘው በዚህ ጨዋታ ጅማ አባ ቡና አማካዩ ኄኖክ ካሳሁንን ከ5 ቢጫ ቅጣት መልስ ያገኘዋል፡፡ በሲዳማው ጨዋታ ጉዳት ያስተናገደው መሀመድ ናስር ልምምድ ላይ አለመገኘቱን ተከትሎ የመሰለፉ ጉዳይ አጠራጣሪ ነው፡፡

በወላይታ ድቻ በኩል በጉዳት ላይ የሚገኘው ተከላካዩ ቶማስ ስምረቱ ለዚህ ጨዋታም አይደርስም፡፡

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ሲዳማ ቡና (10:30 ፤ አአ ስታድየም)

በሁለቱም ቡድኖች በኩል የሚጠቀስ የተጫዋቾች የጉዳትም ሆነ የቅጣት ዜና የለም፡፡

የረቡዕ ጨዋታዎች

ደደቢት ከ ድሬዳዋ ከተማ (08:30 ፤ አአ ስታድየም)

ሰማያዊዎቹ የአጥቂ አማካዩ ሮበን ኦባማን ግልጋሎት የማያገኙ ሲሆን የሽመክት ጉግሳ የመሰለፍ ጉዳይም አጠራጣሪ ሆኗል፡፡

በድሬዳዋ ከተማ በኩል አምበሉ የ5 ቢጫ ቅጣቱን ጨርሶ ለረቡዕ ጨዋታ ብቁ የሆነ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ተቀይሮ የወጣው ቢንያም ሀብታሙ ከጨዋታው በኋላ በነበሩ የልምምድ ፕሮግራሞች አለመገኘቱ የክለቡ ቆይታውን አጠራጣሪ አድርጎታል፡፡

ወልድያ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ (09:00 ፤ ወልድያ)

በወልድያ በኩል የተጫዋች ጉዳት እና ቅጣት ዜና የሌለ ሲሆን በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል በኃይሉ አሰፋ እና ሮበርት ኦዶንካራ በጉዳት ከበድኑ ጋር ወደ ወልድያ አልተጓዙም፡፡ በጉዳት ረጅም ወራት ከሜዳ የራቀው አሉላ ግርማም ወደ ሜዳ አይመለስም፡፡

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ፋሲል ከተማ (10:30 ፤ አአ ስታድየም)

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ግርማ በቀለን በ5 ቢጫ ምክንያት የማያሰልፍ ሲሆን በጉዳት ላይ የሚገኙ ተጫዋቾች መሰለፍ አለመሰለፍ ጉዳይም እስከ ነገ ይታወቃል ተብሏል፡፡

በፋሲል ከተማ በኩል አማካዩ ሰለሞን ገብረመድህን አሁንም በጉዳት ላይ ሲገኝ ሌላው አማካይ ፍቅረሚካኤል አለሙም በጉዳት የማይሰለፍ ተጫዋች ነው፡፡

2 Comments

  1. ደደቢት እኮ ረቡዕ 8:30 ነው፡፡ ይስተካከል ሶከር

  2. ሶከር ኢትዮጵያዎች፡ “A Dynamic Page Updators _ with a timely info updates and live scores”. Love you guys!
    I had the ff query…ማስተካከያ ማድረግ ይገባል፡፡፡
    ጅማ ከተማ ከ ወላይታ ድቻ (09:30 ፤ ጅማ) ያላችሁትን
    ጅማ አባቡና ከ ወላይታ ድቻ ብላችሁ ቀይሩት።

    ጅማዎች ሁለት ምርጥ ቡድኖች አላቸው። እንደ ኢቲቪ ሰው እንዳታምታቱ ብዬ ነው።

Leave a Reply