የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 25ኛ ሳምንት ነገ እና ከነገ በስቲያ በሚደረጉ ጨዋታዎች ሲቀጥል ሶከር ኢትዮጵያም በጨዋታዎቹ ዙርያ ያሉትን እውነታዎች እና የእርስ በእርስ ግንኙነቶች እንዲህ ባለ መልኩ አጠናቅረነዋል፡፡

የነገ ጨዋታዎች

አዲስ አበባ ከተማ ከ አዳማ ከተማ (08:30 ፤ አአ ስታድየም)

– ሁለቱም ቡድኖች ደካማ ጎናቸውን ይዘው ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡ አአ ከተማ በዘንድሮው የውድድር ዘመን በሜዳው ድል ማስመዝገብ የቻለው 1 ጊዜ ብቻ (ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ) ሲሆን አዳማ ከተማም ከሜዳው ውጪ ያስመዘገበው ድል 1 ብቻ (ሀዋሳ ከተማ) ነው፡፡

– አዳማ ከተማ ዘንድሮ አአ ስታድየም ላይ ባደረጋቸው 5 ጨዋታዎች ድል ማስመዝገብ ቀርቶ አንድም ግብ ማስቆጠር አልቻለም፡፡ (ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ደደቢት ፣ ኢትዮጵያ ቡና ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ )፡፡ አዳማ በአጠቃላይ የመጨረሻዎቹ 7 የአአ ስታድየም ጨዋታዎች ላይ ጎል ማስቆጠር ያልቻለ ሲሆን ለመጨረሻ ጊዜ ያሸነፈውም ሆነ ግብ ያስቆጠረው ከአንድ አመት በፊት በዚሁ ሳምንት ኤሌክትሪክን 1-0 በመርታት ነበር፡፡፡

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ አንድ ጊዜ ብቻ የተገናኙ ሲሆን አዳማ ላይ አዳማ ከተማ በቡልቻ ሹራ ጎሎች 2-1 ማሸነፉ ይታወሳል፡፡

አርባምንጭ ከተማ ከ መከላከያ (09:00 ፣ አርባምንጭ)

– አርባምንጭ ከተማ ደካማ የሜዳ ላይ ሪኮርዱን ለመቀልበስ በማለም ወደ ሜዳ ይገባል፡፡ በሁለቱ ቡድኖች የእርስ በእርስ ግንኙነት መከላከያ ወደ አርባምንጭ ተጉዞ ያለፉትን 4 አመታት ግብ ሳይቆጠርበት ያለ ሽንፈት (2 ድል እና 2 አቻ) ተመልሷል፡፡ አርባምንጭ ከተማ ለመጀመርያም ለመጨረሻም ጊዜ መከላከያን በሜዳው ያሸነፈው በ2004 የውድድር ዘመን ነው (3-1)፡፡

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 11 ጊዜ ተገናኝተው ሁለቱም 3 ድል አስመዝግበዋል፡፡ 5 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተፈፅሟል፡፡ ሁለቱም ቡድኖች እኩል 8 ግቦች ሲያስቆጥሩ በመጀመርያው ዙር አዲስ አበባ ስታድየም ላይ አርባምንጭ 2-1 ማሸነፉ ይታወሳል፡፡

ሀዋሳ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና (09:00 ፤ ሀዋሳ)

– ሀዋሳ ከተማ በቡና ላይ በሜዳው ያለውን የበላይነት ለማስቀጠል ወደ ሜዳ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ ቡና ባለፉት 20 አመታት ወደ ሀዋሳ ተጉዞ በድል የተመለሰው በአንድ አጋጣሚ ብቻ ነው፡፡ ቡና ከ1999 የውድድር ዘመን ወዲህ ሀዋሳ ላይ አሸንፎ አያውቅም፡፡

– የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ግቦች የማያጡት ጨዋታ ነው፡፡ ከ1996 ጀምሮ በሁለቱ ክለቦች ግንኙነት ቢያንስ አንድ ግብ ይቆጠራል፡፡

– ከ1990 ጀምሮ በሊጉ ከሚገኙ 3 ቡድኖች መካከል የሆኑት ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 37 ጊዜ ሲገናኙ ሀዋሳ ከተማ 12 ድል በማስመዝገብ ቀዳሚ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ቡና 11 ድል ሲያስመዘግብ 14 ግንኙነቶች በአቻ ውጤት ተፈፅመዋል፡፡ ሀዋሳ 41 ጎሎች (3 የፎርፌ ጎሎች ጨምሮ) ሲያስቆጥር ኢትዮጵያ ቡና 44 ጎሎች አስቆጥሯል፡፡

ጅማ አባ ቡና ከ ወላይታ ድቻ (09:30 ፤ ጅማ)

– ጅማ አባ ቡና ዘንድሮ ከሜዳቸው ውጪ ድል ማስመዝገብ ከተሳናቸው ክለቦች አንዱ የሆነው ወላይታ ድቻን ይገጥማል፡፡ ድቻ በመጋቢት ወር 2008 ወደ አአ ተጉዞ መከላከያን 2-1 ከረታ ወዲህ በአጠቃላይ 19 ተከታታይ የሜዳ ውጪ ጨዋታዎችን ማሸነፍ አልቻለም፡፡ (12 ሽንፈት እና 7 አቻ)

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ አንድ ጊዜ ብቻ ሲገናኙ በአንደኛው ዙር ሶዶ ላይ ወላይታ ድቻ በበዛብህ መለዮ ጎል 1-0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው፡፡

የረቡዕ ጨዋታዎች

ደደቢት ከ ድሬዳዋ ከተማ (08:30 ፤ አአ ስታድየም)

ደደቢት ድሬዳዋ ከተማን በሚያስተናግድባቸው ጨዋታዎች ያለውን የበላይነት የማስቀጠል አላማን ይዞ ወደ ሜዳ ይገባል፡፡ ሰማያዊዎቹ ድሬዳዋ ከተማን በሜዳቸው 4 ጊዜ ገጥመው ሁሉንም አሸንፈዋል፡፡

– ሁለቱ ቡድኖች በ2004 እና 2008 እንደ ዘንድሮው ሁሉ 25ኛ ሳምንት ላይ ተገናኝተው በሁለቱም ላይ ደደቢት ባለ ድል ሆኗል፡፡

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 9 ጊዜ ተገናኝተው ደደቢት 6 በማሸነፍ የበላይ ነው፡፡ ድሬዳዋ 2 ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጨዋታ (ዘንድሮ በመጀመርያው ዙር) በአቻ ውጤት ደምድመዋል፡፡

ወልድያ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ (09:00 ፤ ወልድያ)

ወልድያ በሰንጠረዡ ወገብ ላይ የሚገኝ ቢሆንም በሜዳው የማይደፈር ክለብ ነው፡፡ ወልድያ ለመጨረሻ ጊዜ በሜዳው ሽንፈት ያስተናገደው ግንቦት 2007 ላይ በመከላከያ ሲሆን ከዛ ወዲህ በ14 ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች በአጠቃላይ ደግሞ (ከፍተኛ ሊግ ጨምሮ) 29 ተከታታይ ጨዋታዎችን አልተሸነፈም፡፡

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 3 ጊዜ ተገናኝተው ሁሉንም ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲያሸንፍ 8 ጎል በወልድያ መረብ ላይ አስቆጥሯል፡፡ ወልድያ በአንጻሩ 1 ጎል ብቻ አስቆጥሯል፡፡

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ፋሲል ከተማ (10:30 ፤ አአ ስታድየም)

– ፋሲል ከተማ ዘንድሮ ወደ አዲስ አበባ ተጉዞ ባደረጋቸው 5 ጨዋታዎች ሽንፈት አላስተናገደም፡፡ ቡና ፣ ወልድያ ፣ ኤሌክትሪክ እና አአ ከተማን ሲያሸንፍ ከመከላከያ አቻ ተለያይቷል፡፡

– ሁለቱ ክለቦች በሊጉ 2 ጊዜ ብቻ ተገናኝተዋል፡፡ (2000 እና 2009) ፋሲል ከተማ ሁለቱንም ሲያሸንፍ 3 ጎሎች አስቆጥሯል፡፡ ንግድ ባንክ በአንፃሩ ምንም አላስቆጠረም፡፡

Leave a Reply