የጨዋታ ሪፖርት | አዳማ ከተማ በዋንጫ ፉክክር ውስጥ የሚያቆየውን ድል አአ ከተማ ላይ አስመዝግቧል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 25ኛ ሳምንት የመክፈቻ ጨዋታ አአ ስታድየም ላይ አዲስ አበባ ከተማ አዳማ ከተማን አስተናግዶ 3-1 በሆነ ውጤት ተሸንፏል፡፡

በትላንትናው እለት ከዚህ አለም በሞት የተለዩትና ለረጅም አመታት በዳኝነት እና ኮሚሽነርነት ያሳለፉት አቶ ከማል እስማኤልን በአንድ ደቂቃ የህሊና ጸሎት በማሰብ የተጀመረው ጨዋታ በዳፍ ትራከ እና ቀኝ ጥላፎቅ ሰብሰብ ብለው ሲደግፉ በነበሩ የአዳማ ከተማ ደጋፊዎች የታጀበ፣  በፈጣን እንቅስቃሴ የተሞላ እና በርካታ ሙከራ የተስተናገደበት ነበር፡፡

አዲስ አበባ ከተማ ቀዳሚ የሚሆንበትን ግብ ለማስቆጠር የፈጀበት 2 ደቂቃ ብቻ ነበር፡፡ ወደ አዳማ የግብ ክልል የተሻገረው ኳስ ሲመለስ ከሳጥኑ አቅራቢያ የነበረው አሊ አያና አየር ላይ እንዳለ አክርሮ በመምታት በግሩም ሁኔታ አስቆጥሯል፡፡ በውድድር ዘመኑ አጋማሽ አአ ከተማን የተቀላቀለው አሊ ለቡድኑ ግብ ሲያስቆጥር ለመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡

ከጎሉ መቆጠር በኋላ አዳማ ከተማ የአቻነት ግብ ለማግኘት ተጭኖ የተጫወተ ሲሆን ተደጋጋሚ ሙከራዎችንም ማድረግ ችሏል፡፡ በ13ኛው ደቂቃ አዲስ ህንጻ የደረጄ አለሙ ስህተትን ተጠቅሞ ወደ ጎል ያጠፈውን ኳስ የአአ ተከላካዮች ቀድመው ያወጡት ፣ በ31ኛው ደቂቃ ዳዋ ሁቴሳ ከቅጣት ምት በቀጥታ የመታውን ኳስ የግቡ አግዳሚ የገጨበት ፣ ከአንድ ደቂቃ በኋላ ደግሞ ሱራፌል ከርቀት አክርሮ የመታውን ኳስ ደረጄ ያወጣበት አዳማ ከተማ አቻ ሊሆን የሚችልባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡

በአዲስ አበባ በኩል በ16ኛው ደቂቃ ከነአን ማርክነህ በተከላካዮች መሀል ሰንጥቆ ያሻገረውን ኳስ ኃይሌ እሸቱ በአግባቡ ተቆጣጥሮ በጃኮ አናት ላይ ቢሰደውም ቶጓዊው ግብ ጠባቂ እንደምንም ያወጣበት ኳስ አአ የግብ ልዩነቱን ሊያሰፋበት የሚችልበት አጋጣሚ ነበር፡፡

በ36ኛው ደቂቃ ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ ሱራፌል ወደ ግብ ሲመታው በአዲስ ህንፃ ተጨርፎ አቅጣጫ በመቀየር የአአ መረብ ላይ አርፋለች፡፡ በሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ግብ ያስቆጠረው አዲስ በቅርብ ጨዋታዎች ወደቀደመ ድንቅ አቋሙ እየተመለሰ መሆኑን ማሳየት ችሏል፡፡

አዳማ ከተማ ከአቻነት ግቡ መቆጠር በኋላም ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር ጥረት አድርጓል፡፡ በተለይም በማጥቃት አማካዮቹ አዲስ ህንጻ እና ሱራፌል ዳኛቸው አማካኝነት የግብ እድሎች ቢፈጥርም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር የመጀመርያው አጋማሽ 1-1 ተጠናቋል፡፡

በሁለተኛው ግማሽ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የታየበት ሲሆን የሚደረጉ ቅብብሎችም በመሀለኛው የሜዳ ክፍል የተገደቡ ሆነው ታይተዋል፡፡ በዚህም ሁለቱም ቡድኖች ከርቀት በሚሞከሩ ኳሶች የግብ እድሎችን መፍጠር ችለዋል፡፡ በ56ኛው ደቂቃ ዳዋ ሁቴሳ የመታው ቅጣት ምት በደረጄ ሲመለስበት በ58ኛው ደቂቃ ኤፍሬም ቀሬ ከርቀት አክርሮ የሞከረው ኳስ በጃኮ ተይዞበታል፡፡

ጨዋታው በዚህ ሂደት ቀጥሎ በ65ኛው ደቂቃ ዳዋ ሁቴሳ ፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ያገኘውን ኳስ በአግባቡ ተጠቅሞ አዳማ ከተማን ከተመሪነት ወደ መሪነት አሸጋግሯል፡፡

በጨዋታው መጀመርያ ያስቆጠሩትን ጎል ማስጠበቅ የተሳናቸው አዲስ አበባ ከተማዎች በድጋሚ ወደ ጨዋታው ለመመለስ የመጨረሻዎቹን 25 ደቂቃዎች ተጭነው ቢጫወቱም በምኞት ደበበ እና ሙጂብ ቃሲም የተመራው ጠንካራውን የአዳማ ከተማ የተከላካይ መስመር መስበር አልቻሉም፡፡ በዚህም ከተሻጋሪ ኳሶች እና ከርቀት በሚሞከሩ መከራዎች አደጋ ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል፡፡ በ67ኛው ደቂቃ እንየው ከርቀት መትቶ ጃኮ ያዳነው ፣ በ70ኛው ደቂቃ ከሁለቱም መስመሮች ያሻገሯቸው አደገኛ ኳሶችን ጃኮ ለመቆጣጠር የተቸገረበት ፣ በ72ኛው ደቂቃ ጊት ጋትኮች ያመከነው መልካም አጋጣሚ ለዚህ እንደማሳያ የሚሆኑ ናቸው፡፡

በጥልቀት በመከላከል በሚገኙ አጋጣሚዎች በመልሶ ማጥቃት ውጤታቸውን ለማስጠበቅ የተንቀሳቀሱት አዳማ ከተማዎች ተሳክቶላቸው 90 ደቂቃው ተጠናቆ በተጨመረው ደቂቃ መባቻ ላይ ከቅጣት ምት የተሻገረውን ኳስ ሙጂብ ቃሲም በግንባሩ በመግጨት የአዳማ ከተማን መሪነት ያሰፋች ግብ አስቆጥሯል፡፡ ጨዋታውም በአዳማ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ውጤቱን ተከትሎ አዳማ ከተማ ከ1 አመት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ በአዲስ አበባ ስታድየም ጎል ማስቆጠር እና ድል ማድረግ ሲችል ነጥቡን 42 በማድረስም በዋንጫ ፉክክሩ መቆየት ችሏል፡፡ 19 ነጥቦች ላይ የረጋው አዲስ አበባ ከተማ በአንጻሩ ለከርሞ በኢትዮጵያ ፕሪሞየር ሊግ የመቆየቱን ተስፋ ጠባብ አድርጓል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *