በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 25ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን መርሃ ግብር ወደ ሀዋሳ ያቀናው ኢትዮጵያ ቡና በአስቻለው ግርማ ብቸኛ ግብየውድድር ዘመኑን የመጨረሻ ከሜዳ ውጪ ጨዋታውን በድል በመደምደም አሁንም በዋንጫ ፉክክር ውስጥ መቆየት ችሏል፡፡
ባለሜዳዎቹ ሀዋሳ ከተማዎች ባለፈው ሳምንት ወደ ሶዶ አቅንቶ በወላይታ ድቻ 1-0 ከተሸነፈው ስብስባቸው ውስጥ በጉዳት ያልነበረው መሀመድ ሲይላን በወንድማገኝ ማእረግ ብቻ ተክተው በተመሳሳይ የ4-3-3 ቅርጽ ጨዋታውን መጀመር ችለዋል፡፡ በአንጻሩ ኢትዮጵያ ቡናዎች ባሳለፍነው ሳምንት ወልዲያ ከተማን 2-1 ከረታው ቡድናቸው ውስጥ በጨዋታው ጉዳት ያጋጠመው አብዱልከሪም መሀመድን በአስናቀ ሞገስ እንዲሁም ያቡን ዊልያምን በመስኡድ መሀመድ በመተካት ወረቀት ላይ ሲታይ 4-3-3 ፤ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ 4-5-1 በሚመስል ቅርጽ ጨዋታውን ጀምረዋል፡፡
ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት በትላንትናው እለት በ18ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ዲላ ላይ ጊዲዮ ዲላ ከ ሀዋሳ ከተማ ያደረጉትን ጨዋታ በኮሚሽነርነት መርተው ሲመለሱ ባጋጠማቸው የመኪና አደጋ ህይወታቸው ላለፈው አቶ ከማል እስማኤል የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት በማድረግ ነበር የተጀመረው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሀዋሳ ከተማ ስፖርት ክለብ ለቀድሞዋ የሉሲ አምበል እየሩሳሌም ነጋሽ የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል፡፡
በጨዋታው በተለይም የመጀመሪያ 15 ደቂቃዎች ላይ ሀዋሳ ከተማዎች እጅግ የተለዩ ነበሩ፡፡ የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቾች እጅጉን ወደ መሀል ሜዳ በማስጠጋት የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾች ኳስ ከራሳቸው የግብ ክልል መስርተው እንዳይወጡ በማድረግ እንዲሁም ኳስ በተነጠቁበት ቅጽበት በፍጥነት መልሶ በመንጠቅ በኩል ሀዋሳዎች እጅግ የሚያስደምሙ ነበሩ፡፡
ባለሜዳዎቹ ሀዋሳዎች በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ጫና በመፍጠር ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል በመድረስ ጫና መፍጠር የጀመሩት ገና በማለዳው ነበር፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆኑት በመጀመሪያው ደቂቃ መድሀኔ ታደሰ ከፍሬው ተሻማለትን ኳስ ሞክሮ ሀሪሰተን ያዳነበት እንዲሁም በ7ኛው ደቂቃ ፍሬው ሰለሞን ከቅጣት ምት ሞክሮ በተመሳሳይ ሀሪስተን ያዳነበት ኳስ ተጠቃሾች ነበሩ፡፡
ኢትዮጵያ ቡናዎች በአንጻሩ ወደ ኃላ በማፈግፈግ ሁለት የመከላከል መስመር በመስራት ሀዋሳ ከተማዎች እንደሚፈልጉት ኳሱን እያንሸራሸሩ እንዳይጫወቱ ለማድረግ ሞክረዋል፡፡ በኢትዮጵያ ቡና በኩል የቀድሞ ክለቡን የገጠመው አክሊሉ ዋለልኝ የሀዋሳ ከተማዎችን እንቅስቃሴ በማቋረጥ በኩል እጅግ በአስገራሚ ብቃት ሲንቀሳቀስ ተስተውሏል፡፡
ቡናዎች በመልሶ ማጥቃት እንዲሁም ወደ መሀል ሜዳ ተጠቅጥቀው ሲከላከሉ የነበሩት የሀዋሳ ከተማ ተከላካዮች ከጀርባቸው ትተው የሚሄዱትን ክፍተት በቀጥታ ከተከላካይ በሚላኩ ኳሶች ለመጠቀም ያደረጉት ጥረት እምብዛም ውጤታማ አልነበረም፡፡ በዚሁ በመጀመሪያው አጋማሽ ኢትዮጵያ ቡናዎች አማኑኤል ከሰጥኑ ጠርዝ ላይ ሞክሯት ሚንሳ ካወጣበት ኳስ በስተቀር ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም፡፡
የመጀመሪያው አጋማሽ ሊገባደድ ሁለት ደቂቃዎች ሲቀሩ የሀዋሳ ከተማው አጥቂ የሆነው ጃኮ አራፋት በኤፍሬም ወንደሰን ተጎትቶ ወድቋል በማለት ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት የመሩት ፌደራል ዳኛ እያሱ ፈንቴ ለሀዋሳ ከተማ አጨቃጫቂ ፍፁም ቅጣት ምት ቢሰጡም ፍሬው ሰለሞን ሳይጠቀምባት ቀርቶ የመጀመርያው አጋማሽ ያለ ግብ ተጠናቋል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች የተሻለ የመሸናነፍ ፉክክርን አሳይተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ቡናዎች በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው በተሻለ የሀዋሳ ተከላካዮች ከጀርባቸው ትተው የሚሄዱትን ክፍተት ለመጠቀም በተሻለ ጥረት በማድረግ በሁለት አጋጣሚዎች ሳኑሚ እንዲሁም መስኡድ አግኝተው ያልተጠቀሙባቸው አጋጣሚዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በ76ኛው ደቂቃ ኢትዮጵያ ቡናዎች በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ያገኙትን ኳስ ጋቶች ፓኖም ከግብ ክልል ውጪ በቀጥታ በመምታት የሞከራት ኳስ የግቡን ቋሚ ለትማ ስትመለስ አስቻለው ግርማ ዳግም በመምታት ኢትዮጵያ ቡና በ10 አመታት ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ሀዋሳ ተጉዞ ድል ያስመዘገበበትን ብቸኛ ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡ ከግቧ መቆጠር አስቻለው ግርማ ለቀድሞ ክለቡ ክብር በመስጠት ደስታውን ሳይገልፅ ቀርቷል፡፡
በቀሩት ደቂቃዎች ኢትዮጵያ ቡናዎች ወደ ኃላ በማፈግፈግ ውጤቱን አስጠብቀው ለመውጣት ችለዋል፡፡
እጅግ በርካታ ቁጥር ያለው ደጋፊዎች በተከታታሉት በዚሁ ጨዋታ ቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉ የሲዳማ ቡና ደጋፊዎች በብዛት ወደ ስፍው ካቀኑት የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ጋር በመሆን እጅግ ደማቅ የሆነ ድጋፍን አሳይተዋል፡፡
ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ነጥቡን 42 በማድረስ ቢያንስ ለ24 ሰአታት በደረጃ ሰንጠረዡ 3ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ከደካማ የውድድር ዘመን ጅማሮ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ 3ኛ ደረጃን መያዝ ችሏል፡፡
በቀሩት ደቂቃዎች ኢትዮጵያ ቡናዎች ወደ ኃላ በማፈግፈግ ውጤቱን አስጠብቀው ለመውጣት ችለዋል፡፡
የአሰልጣኞች አስተያየት
ገዛኸኝ ከተማ – ኢትዮጵያ ቡና
ስለ ድሉ
“በሁለተኛው ዙር እጅግ ጥሩ መሻሻል እያሳየ ከሚገኘው ሀዋሳ ከተማ ጋር ያደረግነውን ወሳኝ ጨዋታን ድል በማድረጋችን እንዲሁም ከ10 አመታት በኃላ እዚህ ሜዳ ላይ ድል በማድረግ ታሪክ በመስራታችን ደስ ብሎኛል፡፡”
ተከላክለው ስለመጫወታቸው
“ከዚህ ቀደም የነበሩ የሀዋሳ ከተማ ጨዋታዎች ላይ ተንተርሰን የራሳችንን ዝግጅት አድርገን መጫወት ችለናል፡፡”
ውበቱ አባተ – ሀዋሳ ከተማ
ስለ ጨዋታው
“ኢትዮጵያ ቡና ጠንካራ ደጋፊ ያለው ጥሩ እግርኳስ የሚጫወት ቡድን ነው፡፡ጨዋታው በራሳችን ስህተት ነው ከእጃችን የወጣው፡፡”
ስለ ጫና ውስጥ መገኘት
“ተከታታይ ውጤት በማጣታችን ጫና ውስጥ ልንገባ እንችላለን፡፡ከአመጣጣችን አንጻር አሁን ያለንበት ነገር መጥፎ የሚባል አይደለም፡፡”