የጨዋታ ሪፖርት | መከላከያ በቴዎድሮስ ታፈሰ የመጨረሻ ደቂቃ ግብ ከአርባምንጭ ነጥብ ተጋርቷል

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 25ኛ ሳምንት አርባምንጭ ላይ መከላከያን ያስተናገደው አርባምንጭ ከተማ በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረ ግብ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይቷል

አርባምንጭ ከተማ ከተማ ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ ለጨዋታው ትኩረት የሰጠ በሚመስል መልኩ በሙሉው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የተሻለ መንቀሳቀስ ችለዋል፡፡ በመጀመሪያው 15 ደቂቃዎች ላይ አዞዎቹ በእንግዳው ቡድን ላይ እጅግ በርካታ የግብ አጋጣሚወችን መፍጠር የቻሉ ሲሆን በተለይ በአቋም መዋጀቅ ሲታማ የነበረው አመለ ሚልኪያስ ለአርባምንጭ ከተማ ከሌላው ጊዜ በተለደ አሰደናቂ እንቅስቃሴን አድርጓል፡፡

በ22ኛው ደቂቃ በአማካይ ስፍራ ምርጥ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረው ወንድሜነህ ዘሪሁን ከግራ መስመር ያሻገራትን ኳስ እንዳለ ከበደ ወደ ግብነት በመቀየር አዞዎቹን ቀዳሚ ማድረግ ችለሏል፡፡ ያለፉትን የውድድር ዘመናት ከጉዳት ጋር እየታገለ የሚገኘው እንዳለ በዘንድሮው የውድድር ዘመን የመጀመርያ ጎሉን ነው ማስቆጠር የቻለው፡፡

አርባምንጭ ከተማዎች ግብ ካስቆጠሩ በኃላ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር እድሎችን ቢፈጥሩም ተጨማሪ ግብ ሳያስቆጥሩ የመጀመሪያው አጋማሽ በአርባምንጭ የ1-0 መሪነት ተደምድሟል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ አርባምንጭ ከተማ በበርካታ ደጋፊዎቹ ታግዞ እንደመጀመርያው ሁሉ የተሻለ እንቅስቃሴ ሲያደርግ መከላከያ በአንፃሩ በቡድንም ሆነ በተናጠል ይህ ነው የሚይባል እንቅስቃሴን ሳያደርጉ በአርባምንጭ የበላይነት ተወስዶባቸዋል፡፡

የጨዋታው መደበኛ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ 4 ደቂቃዎች ከተጨመሩ በኃላ የአርባምንጭ ከተማ ተከላካዮች በሰሩት ጥፋት በግምት ከ30 ሜትር ርቀት የተሰጠውን ቅጣት ምት ቴዎድሮስ ታፈሰ በመምታት ወደ ግብነት ቀይሮ ጦሩን አቻ በማድረግ ጣፋጭ አንድ ነጥብ ከአዞዎቹ መንጠቅ ችለዋል፡፡ ቴዎድሮስ ከዚህ ቀደምም መከላከያ ወደ ድሬዳዋ ተጉዞ አንድ ነጥብ ይዞ የተመለሰበትን ጎል በቅጣት ምት ማስቆጠሩ የሚታወስ ነው፡፡

ከግቧ መቆጠር በኋላ ባሉት ጥቂት ደቂቃዎች አርባምንጮች የማሸነፍያ ጎል ፍለጋ ተጭነው ቢጫወቱም ሳይሳካ ጨዋታው 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተፈፅሟል፡፡ ባለፈው ሳምንት በደደቢት 2-0 ከመመራት ተነስቶ በመጨረሻው ደቃ በተቆጠረ ግብ ነጥብ ተጋርቶ የወጣው አርባምንጭ በዚህ ሳምንት ደግሞ በመጨረሻ ሰአት በተቆጠረበት ግብ ነጥብ ለመጣል ተገዷል፡፡

ውጤቱን ተከትሎ ሁለቱም ቡድኖች ነጥባቸውን 31 በማድረስ በደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ አንድ ደረጃ በማሻሻል ተቀምጠዋል፡፡

Leave a Reply