የጨዋታ ሪፖርት | ሲዳማ ቡና ከኤሌክትሪክ አቻ ተለያይቶ የሊጉን መሪነት የመያዝ እድሉን አምክኗል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 25ኛ ሳምንት የእለቱ የመጨረሻ መርሀ ግብር አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ተካሂዶ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ሲዳማ ቡና ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተያይተዋል፡፡ ሲዳማ ቡናም ቢያንስ ለ24 ሰአታት የሊጉ መሪ ሊሆን የሚችልበትን እድል አምክኗል፡፡

በሌሎች ጨዋታዎች ላይ እንደተደረገው ሁሉ በዚህ ጨዋታ መጀመርያ ለረጅም አመታት በኢትዮጵያ እግርኳስ ውስጥ በዳኝነት እና ኮሚሽነርነት ያገለገሉትና በትላንትናው እለት ከዚህ አለም በሞት የተለዩት አቶ ከማል እስማኤልን ለማሰብ በ1 ደቂቃ የህሊና ጸሎት ነበር ጨዋታው የተጀመረው፡፡

በግራ የካታንጋ ክፍል ሰብሰብ ብለው ክለባቸውን ሲያበረታቱ በነበሩት የሲዳማ ቡና ደጋፊዎች እና በቀኝ ካታንጋ በነበሩ የኢትዮ ኤሌክትሪክ ወጣት ተጫዋቾች እና ደጋፊዎች ድጋፍ የታጀበው ጨዋታ ቀዝቃዛ እና እምብዛም ማራኪ እንቅሰስቃሴ ያልታየበት ሆኖ አምሽቷል፡፡

ጨዋታው በመሀል ሜዳ ላይ ያመዘነ እና ተመጣጣኝ የነበረ ቢሆነም በግብ ሙከራዎች እንግዶቹ የተሻሉ ነበሩ፡፡ በ17ኛው ደቂቃ በጨዋታው ጥሩ የተንቀሳቀሰው ፍጹም ተፈሪ በረጅሙ ያሻገረውን ኳስ ትርታዬ ሞክሮ ወደ ውጪ ሲወጣበት በ21ኛው ደቂቃ ላኪ ሳኒ የሞከረውን ኳስ ግብ ጠባቂው አቡ ሱሌይማና ይዞበታል፡፡ በ32ኛው ደቂቃ ላኪ ሳኒ ጥሩ የግብ አጋጣሚ አግኝቶ ሳይጠቀምበት ሲቀር በ44ኛው ደቂቃ ደግሞ ፍጹም ተፈሪ በቀጥታ የሞከረውን ቅጣት ምት አቡ ሱሌይማና አድኖበታል፡፡

በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል ዳንኤል ራህመቶ የሞከረውን ኳስ ለአለም በቀላሉ ሲይዝበት ዳዊት እስጢፋኖስ የመታው ኳስ ወደ ውጪ የወጣበት በመጀመርያው አጋማሽ ካደረጓቸው ሙከራዎች የሚጠቀሱ ነበሩ፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ሲዳማ ቡናዎች ጎለል ለማስቆጠር የተሻለ ቢንቀሳቀሱም የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው በኢትዮ ኤሌክትሪክ በቀላሉ ሲጨናገፍ አምሽቷል፡፡ በ48ኛው ደቂቃ ትርታዬ ደመቀ ያሻማውን ኳስ ላኪ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ውጪ ሲወጣበት በ60ኛው ደቂቃ ናይጄርያዊው አጥቂ ላኪ ጎል አስቆጥሮ የሲዳማን ደጋፊ ቢያስፈነጥዝም ከጨዋታ ውጪ አቋቋም ላይ የነበረ በመሆኑ ጎሉ ሳይፀድቅ ቀርቷል፡፡

ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በተለይም በረጅሙ በሚሻገሩ ኳሶች የግብ እድል ለመፍጠር ጥረት ማድረግ ችለዋል፡፡ በተለይ በ52ኛው እና 54ኛው ደቂቃዎች በዳዊት እና አወት አማካኝነት የግብ ሙከራ አድርገው ለአለም ብርሀኑ አክሽፏቸዋል፡፡

የጨዋታው ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር በዋንጫው ፉክክር ውስጥ የሚገኙት ሲዳማ ቡናዎች ተጭነው ተንቀሳቅሰዋል፡፡ በ66ኛው ደቂቃ ፍፁም ፣ በ66ኛው ደቂቃ ትርታዬ እንዲሁም በ75ኛው ደቂቃ ጸጋዬ ባልቻ የሞከሯቸው ኳሶች ወደ ውጪ ሲወጡ በ77ኛው ደቂቃ ፍፁም ተፈሪ በበርካታ የኢትዮ ኤሌክትሪክ ተከላካዮች መሀል በግሩም ሁኔታ አሾልኮ ወደ ግብ የመታው ኳስ ግብ ጠባቂው ሱሌማና ሳይደርስበት ቢቀርም አወት ከግቡ መስመር በማውጣት ጎል ከመሆን ታድጓታል፡፡

ከዚህች አስደንጋጭ ሙከራ በኋላም ሲዳማዎዎች በአዲስ ግደይ ፣ ጸጋዬ ባልቻ እና ሳውሬል ኦልሪሽ አማካኝነት የግብ ሙከራ ማድረግ ቢችሉም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ በዚህም ጨዋታው ግብ ሳይስተናገድበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል
በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃ አበበ ጥላሁን እና ዳዊት እስጢፋኖስ ግጭት ውስጥ ገብተው በዳኞች ገላጋይነት ግጭታቸው ረግቧል፡፡ በዚህ ክስተት ዳኞቹ ተጫዋቾቹን ከመገሰፅ ይልቅ በማገላገል ማለፋቸው አስገራሚ ሆኗል፡፡

ውጤቱን ተከትሎ ሲዳማ ቡና ቢያንስ ለ24 ሰአታት የሊጉን መሪነት የሚጨብጡበትን እድል ሲያመክን ከሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች ያገገመው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ28 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *