የጨዋታ ሪፖርት | ጅማ አባ ቡና በሀይደር ሸረፋ የመጨረሻ ደቂቃ ጎል ወሳኝ ሶስት ነጥቦች ሰብስቧል

በ25ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጅማ ላይ በወራጅነት ስጋት ውስጥ ሆነው የተገናኙት ጅማ አባ ቡና እና ወላይታ ድቻ ያደረጉት ወሳኝ ጨዋታ ባለሜዳዎቹ የበላይነት ተጠናቋል፡፡

ከጨዋታው ወሳኝነት አንጻር እንደተጠበቀው ውጥረት እና ጫና የበዛበት ፣ ከፍተኛ የመሸናነፍ ፍላጎት የታየበት ፣  የተመልካችን ቀልብ የገዛ ፣ የሁለቱም ቡድኖች ግብ ጠባቂዎች ስራ በዝቶባቸው የዋለበት እንዲሁም ድራማዊ ክስተቶችን ያስተናገደ ጨዋታ አስመልክቶናል፡፡ በርካታ ቁጥር ያላቸው የጅማ አባቡና ደጋፊዎች እና ቡድናቸውን ተከትለው ከሶዶ የመጡ ጥቂት የማይባሉ የወላይታ ድቻ  ደጋፊዎችም ስታድየሙን በግሩም ድባብ አላብሰውት ውለዋል፡፡

በሌሎች የሀገሪቱ ስታድየሞች እንደተደረገው ሁሉ ትላንት ከዚህ አለም በሞት የተለዩት የቀድሞ ኮሚሽነር እና ዳኛ ከማል እስማኤል በአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት ከታሰቡ በኋላ ጨዋታው ይጀመራል ተብሎ ሲጠበቅ አንድ አዛውንት በደጋፊዎች መካከል በተፈጠረ ግርግር የመፈንከት ጉዳት  በማጋጠማቸው ምክንያት የወላይታ ድቻ የቡድን መሪ ወደ ህክምና ቦታ ይዘዋቸው ሄደዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የቡድን መሪው እስኪመለሱና ከዛም በኋላ ደጋፊው የተለየ ቦታ ላይ ተቀምጠው ጨዋታውን እንዲከታተሉ ከኮምሽነሩ ጋር በፈጠሩት ክርክር የጨዋታው መጀመርያ ሰአት መዘግየቱ የእለቱ አስገራሚ ክስተት ነበር ።

በጨዋታው የመጀመርያ ደቂቃዎች ወደ ጎል በመድረስም ሆነ በጨዋታ እንቅስቃሴ ብልጫ የነበራቸው እንግዶቹ ድቻዎች ነበሩ፡፡ ገና በ2ኛው ደቂቃ በበዛብህ መለዮ አማካኝነት የጎል ሙከራ አድርገው ጀማል ጣሰው ያዳነበትም ተጠቃሽ ሙከራ ነበር።

ጨዋታው እየተሟሟቀ ሲመጣ ድቻዎች በጠንካራ መከላከል ወደ ኋላ በማፈግፈግ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት በማሰባቸው ጅማ አባቡናዎች ወደ ጨዋታው ተረጋግተው በመመለስ እስከ ጨዋታው መጠናቀቅ ድረስ ሙሉ ለሙሉ ብልጫ መውሰድ ችለዋል፡፡  ሆኖም በ11ኛው ደቂቃ በቅጣት ምት ቢያድግልኝ ኤሊያስ እንዲሁም 38ኛው ደቂቃ ላይ ክርዚስቶም ንታንቢ አማካኝነት ለጎል የቀረቡ ሙከራ ቢያደርጉም ኳስና መረብን ማገናኘት አልቻሉም፡፡  በተለይም 41ኛው ደቂቃ ላይ አሜ መሀመድ ለመሳት የሚከብድ ግልፅ የጎል አጋጣሚ ሳይጠቀም መቅረቱ የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር።

በአንፃሩ በሚያገኙት የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚ እንግዶቹ ድቻዎች 23ኛው ደቂቃ ዳግም በቀለ እና 21ኛው ደቂቃ አማኑኤል ተሾመ አማካኝነት ያደረጉት የጎል ሙከራ ተጠቃሽ ነበር።

ሁለተኛው አጋማሽ በከባድ ዝናብ ጋር ታግዞ የቀጠለ ሲሆን እንደ መጀመርያው አጋማሽ ሁሉ ጨዋታው ግለቱን ጠብቆ ቀጥሏል፡፡ በዚህ የጨዋታ ክፍለ ጊዜም ባለ ሜዳዎቹ ጅማ አባ ቡናዎች ተሽለው በመቅረብ ብልጫ ወስደው ተጫውተዋል፡፡

በጅማ አባ ቡና በኩል በ57ኛው ደቂቃ ኄኖክ ካሳሁን ፣ በ62 እና 75ኛው ደቂቃ አሜ መሀመድ የሞከሩትን ወንድወሰን ገረመው በአስደናቂ ሁኔታ ሲያመክን እንግዶቹ ድቻዎች በ89ኛው ደቂቃ ላይ ዳግም በቀለ ከጀማል ጣሰው ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ አስቆጠረው ተብሎ ሲጠበቅ ጀማል ልምዱን ተጠቅሞ ያዳነበት ኳስ የሚያስቆጭ ነበር።

የዳግም በቀለ ሙከራ በተመለሰበት ቅፅበት ወደ ወላይታ ድቻ የግብ ክልል የተላከውን ኳስ ሀይደር ሸረፋ ከግራ መስመር ወደ ውስጥ በመግባት ከሳጥን ውጭ ግሩም ጎል አስቆጥሮ ስታድየሙ በደስታ እንዲናጥ አድርጓል፡፡ ጨዋታውም በጅማ አባ ቡና አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ጅማ አባ ቡና ጣፋጭ ድል ማስመዝገቡን ተከትሎ የወራጅ ቀጠናውን ለወላይታ ድቻ ሰያስረክብ ከሜዳው ውጪ ድል አልባ ጉዞውን ወደ 20 ያሳደገው ወላይታ ድቻ በ3 አመት ወስጥ ደካማውን የውድድር ዘመን ጉዞ ማድረጉን ቀጥሎበታል፡፡

2 Comments

  1. ጫወታው ከተጠናቀቀ በኀላ ለወላይታ ዲቻ 7 ቁጥር መለያ ለብሶ ሚጫወተው ተጫዋች እጅግ አሳፋሪ በሆነ ሁኔታ ከቡድን ጓደኛው ጋር በተደጋጋሚ ቡጢ እየተሰነዛዘረ ሲደባደብ ታይቷል፡፡ ነገር ግን በየትኛውም ሚዲያ ይህ አሳፋሪ እና አሳዛኝ ትይንት ሽፋን አላገኘም፡፡ ፌዴሬሽኑም ጉዳዩን በትኩረት አይቶ አስተማሪ ቅጣት መቅጣት ይኖርበታል፡፡

  2. You know Dani, Wolaita Dicha foot ball club has a unique funs who devote themselves for the success of the team. To mention some of the sacrifice that they had, before two weeks more than 300 Dicha funs have travelled to Woldiya which is about 1000 km from Wolitta Soddo. Again about 500 fund have travelled to Jimma, even thought they got back with loss of their team. So that the descending of Wolaita Dicha is not a loss for its fans only but also loss for Ethiopian foot ball. Because it has ignited the fire of foot ball throughout the country.Finally I would like to assure that Dicha will neverrrrrrrrrr descend from EPL.

Leave a Reply