ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ – በ20ኛ ሳምንት ጨዋታዎች መሪዎቹ በሙሉ ነጥብ ጥለዋል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 20ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ማክሰኞ በአዲስ አበባ እና ክልል ከተሞች ሲደረጉ በደረጃ ሰንጠረዡ ከ1-6ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡ ቡድኖች በሙሉ ነጥብ የጣሉበት ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡

ሽረ ላይ መሪው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲን ያስተናገደው ሽረ እንዳስላሴ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተላያይቷል፡፡ 8 የማስጠንቀቂያ ካርዶች የተመዘዙበት ይህ ጨዋታ ጥንቃቄ የተሞላበት እንቅስቃሴ ተስተውሎበታል፡፡

ተቀራራቢ የሆነ ፉክክር በተስተዋለበት የመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሽረ እንዳስላሴ በሳሙኤል ተስፋዬ እና ብሩክ ሀዱሽ አማካኝነት ጥሩ የጎል ሙከራ ሲያደርጉ ወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲ በአብርሃ ተዓረ ፣ አፈወርቅ ሀይሉ ፣ ከድር ሰለህ እና ቴዎድሮስ መንገሻ አማካኝነት ለጎል የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል፡፡

በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ሽረ እንደሥላሴ የተጨዋች እና የአቀራረብ ለውጥ ያደረገ ሲሆን ጨዋታውንም በበላይነት መምራት ችሎ ነበር፡፡ በተለይ 57 እና 70ኛው ደቂቃ ሲዒድ ሑሴን ያገኘውን አጋጣሚ በቀላሉ ባያመክን ኖሮ የሽረ ብለልጫ ወደ ውጤት በተቀየረ ነበር፡፡ የወልዋሎው አሰልጣኝ ብርሃኔ ገ/እግዚአብሔር ቡድናቸውን በዚህ አጋማሽ አፈግፍጎ እንዲጫወት ያደረጉ ሲሆን ተሳክቶላቸው ግብ ሳያስተናግዱ ጨዋታው ያለ ግብ ተፈጽሟል፡፡

በደረጃ ሰንጠረዡ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው መቀለ ከተማ ወደ ለገጣፎ አምርቶ 2-0 በሆነ ውጤት በመሸነፍ የምድቡን መሪነት የመያዝ እድሉን አምክኗል፡፡ ለለገጣፎ ልደቱ ለማ በ 56ኛው ደቂቃ እንዲሁም ሳዲቅ ተማም በ63ኛው ደቂቃ ጎሎቹን ማግባት የቻሉ ተጫዎቹች ናቸው፡፡

ባህርዳር ላይ ባህርዳርን ወሎ ኮምበልቻን አስተናግዶ 1-1 በመለያየት ከመሪዎቹ ያለውን ልዩነት የማጥበብ እድሉን ሳየይጠቀም ቀርቷል፡፡  ወሎ ኮምቦልቻ በ 44ኛው ደቂቃ በፋሲል አስማማው ጎል ቀዳሚ መሆን ቢችሉም ከእረፍት በፊት በተጨማሪው ደቂቃ ኪዳኔ ተስፋዬ ባሀህርዳርን አቻ አድርጓል፡፡

በዚህ በ20ኛ ሳምንት ሶስት ቡድኖች ከሜዳቸው ውጪ ድል አስመዝግበው ተመልሰዋል፡፡ ወደ አዲስ አበባ የተጓዘው ሱልልታ ከተማ አራዳ ክፍለ ከተማን 2-1 በሆነ ውጤት ሲያሸንፍ በተመሳሳይ አክሱም ላይ ቡራዩ ከተማ አክሱምን 1-2 በሆነ ውጤት አሸንፎ ተመልሷል፡፡ ሌላው አዲስ አበባ ላይ በተካሄደው ጨዋታ አዲስ አበባ ፖሊስን የገጠመው ሰበታ ከተማ 1-0 ማሸነፍ ችሏል፡፡

ደብረ ብርሀን ላይ ሰሜንሸዋ ደብረብርሃን ከ ኢትዮጵያ መድን እንዲሁም ባህርዳር ላይ አማራ ውሃ ስራ ከኢትዮጵያ ውሃ ስፖርት ያለምንም ጎል የተጠናቀቁ ጨዋታዋች ናቸው፡፡

ምስጋና

የሽረ እንዳስላሴ እና ወልዋሎን ጨዋታ ለመከታተል ሽረ በተገኘንበት ወቅት የክለቡ አመራሮች ላደረጉልን አቀባበል እና መስተንግዶ ከፍ ያለ ምስጋና እናቀርባለን

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *