ፕሪምየር ሊግ | በኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ የገንዘብ ቅጣት ተጣለ

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዲሲፕሊን ኮሚቴ በሸገር ደርቢ ላይ በተፈጠሩ የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለቶች ተጠያቂ ያደረጋቸው ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ የገንዘብ ቅጣት ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

ሚያዝያ 7 ተደርጎ በነበረው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ  ቡና ጨዋታ ላይ የሁለቱንም ክለብ መለያ የለበሱ ደጋፊዎች ድንጋይ እና ቁሳቁሶች መወርወራቸው በጨዋታው ኮሚሽነር ሪፖርት በመቅረቡ የዲሲፕሊን ኮሚቴው ሁለቱን ክለቦች እያንዳንዳቸው 40,000 ብር ቅጣት ጥሎባቸዋል፡፡ ፌዴሬሽኑ በቅጣት ማብራርያው ላይ ጨምሮ እንደገለጸው የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች የቅዱስ ጊዮርጊሱ አዳነ ግርማን  “በፅሁፍ ለመግለጽ የሚከብዱ” ስድቦችን በመሰንዘራቸው ክለቡ ተጨማሪ 75,000 ብር ተቀጥቷል፡፡

አዳማ ላይ ከአዳማ ከተማ ጋር በተደረገው ጨዋታ በተፈጠረው ተመሳሳይ ተግባር መነሻነት ክለቡ ደጋፊዎችን የማስተማር ስራ እንዲሰራ ቢገለፅም በበቂ ሁኔታ ባለማከናወኑ በ30 ቀናት ውስጥ ደጋፊውን የማስተማር ስራ በማከናወን ሪፖርት እንዲያደርግ ፌዴሬሽኑ አሳስቧል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *