የጨዋታ ሪፖርት | ደደቢት ደረጃውን ወደ 2ኛ ያሻሻለበትን ድል በድሬዳዋ ላይ አስመዝግቧል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 25ኛ ሳምንት በሁለተኛ ቀን ውሎው 3 ጨዋታዎችን ሲያስተናግድ አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ከሻምፒዮንነት ፉክክሩ ዋና ተዋናዮች አንዱ በሆነው ደደቢት እና ባለፋት ጨዋታዎች ነጥቦችን መሰብሰብ ቢችልም አሁንም ከወራጅነት ስጋት ነፃ መሆን ባልቻለው ድሬዳዋ ከተማ መሀከል የተደረገው ጨዋታ በባለሜዳው ቡድን 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በጨዋታው መጀመሪያ ላይ ከቀናት በፊት ዲላ ላይ ጌዲዮ ዲላ ከ ሀዋሳ ከተማ ጋር ያደረጉትን የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ በኮሚሽነርነት መርተው ሲመለሱ ባጋጠማቸው የመኪና አደጋ ከዚህ አለም በሞት ለተለዩት አቶ ከማል እስማኤል የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት የተደረገ ሲሆን ጌታነህ ከበደ ክለቡ ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ካደረገው ጨዋታ በኋላ ባሳየው ያልተገባ ባህሪ ያሳዘናቸውን የክለቡ ደጋፊዎች አበባ በማበርከት ይቅርታ ጠይቋል።

ደደቢቶች በጨዋታው ጌታነህ ከበደ እና ዳዊት ፍቃዱን ከፊት አሰልፈው እንደተለመደው ከኋላ በተለይ ጌታነህ ከበደን ዒላማ አድርገው በሚላኩ ረጅም ኳሶች ለመጠቀም ጥረት አድርገዋል። ድሬዳዋ ከተማ በአንፃሩ በ4-1-3-2 ቅርፅ ከበረከት ይስሀቅ እና ሀብታሙ ወልዴኀላ ዮሴፍ ዳሙዬ፣ ይሁን እንዳሻውና ሱራፌል በማሰለፍ በአጭር ቅብብል እና ከመስመር ኳስን ይዞ ወደ አደጋ ክልሉ በመግባት ወደግብ ለመድረስ ሲሞክሩ ተስተውሏል።

ደደቢት ጨዋታውን በጥሩ የማጥቃት አጨዋወት የጀመረ ሲሆን ገና በ26ኛው ሰከንድ ጌታነህ ከበደ ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ ወደግብ አክርሮ የመታው ኳስ በድሬዳዋ ከተማው ግብ ጠባቂ ሳምሶን አሰፋ ተመልሶበታል። ድሬዳዋ ከተማዎች ወደ ጨዋታው ለመግባት ብዙ ጊዜ ያልፈጀባቸው ሲሆን በ6ኛው ደቂቃም ሱራፌል ዳንኤል ከቀኝ ክንፍ ኳስን ይዞ በመግባት ወደ መሀል  ቢያሻማም ሀብታሙ ወልዴ ለጥቂት ሳይደርስበት ቀርቷል። ደደቢቶች በተደጋጋሚ ከርቀት በሚመቱ ኳሶች ግብ ለማስቆጠር ጥረት ያደረጉ ሲሆን ጌታነህ ከበደ እና ሰለሞን ሀብቴ የሞከሯቸው ኳሶች ዒላማቸውን ሳይጠብቁ ቀርተዋል።

በ30ኛው ደቂቃ ጌታነህ ከበደ ከስዩም ተስፋዬ የተሻገረለትን ኳስ ወደግብ ቢሞክርም በግብጠባቂው ሳምሶን አሰፋ የተመለሰበት ሲሆን ሳምሶን ከዚህ በተጨማሪ ዳዊት ፍቃዱ እና ብርሃኑ ቦጋለ ወደግብ የመቷቸውን ኳሶች በመመለስ በጥሩ ብቃት ላይ እንደሚገኝ አሳይቷል። በረከት ይስሀቅ ከሳጥን ውጪ ወደግብ መትቶ ግብጠባቂው ታሪክ ጌትነት የመለሰበት፣ እንዲሁም ሱራፌል ዳንኤል የሰጠውን ኳስ ሀብታሙ ወልዴ መትቶ የወጣበት ሙከራዎች በመጀመሪያው አጋማሽ ከድሬዳዋ ከተማ በኩል የሚጠቀሱ ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ ድሬዳዋ ከተማዎች የግብ ሙከራ የበላይነት የነበራቸው ሲሆን በበረከት ይስሀቅ፣ ተስፋዬ ዲባባ እና ዮሴፍ ዳሙዬ አማካኝነትም ከርቀት ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል። በጨዋታው 60ኛ ደቂቃ በረከት ይስሀቅ ከግብ ጠባቂው ታሪክ ጌትነት ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ የተመለሰበት ኳስ ለድሬዳዋ ከተማ የሚያስቆጭ ዕድል ነበር። በ71ኛው ደቂቃ ይሁን እንዳሻው ኳስን ይዞ ወደተጋጣሚው ሳጥን ውስጥ በሚገባበት ሰዓት ጥፋት ተሰርቶብኛል ብሎ በመውደቅ ፍፁም ቅጣት ምት እንዲሰጠው ቢጠይቅም ዳኛው አስመስለህ ወድቀሀል ብለው የማስጠንቀቂያ ካርድ ሰጥተውታል።

በደደቢት በኩል 72ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት ፍቃዱ ከግብጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ግብ ማስቆጠር የሚችልበት ወርቃማ ዕድል ቢያገኝም በሳምሶን አሰፋ ተመልሶበታል። ከዚህ ሙከራ በኋላ ድሬዳዋ ከተማ በሱራፌል ዳንኤል እና ፉአድ ኢብራሂም አማካኝነት ከርቀት ሙከራዎችን ቢያደርግም ግብ ማስቆጠር የቻለው ግን ደደቢት ነበር። ዳዊት ፍቃዱ ተቀይሮ የገባው አቤል እንዳለ ከመሀል ያሻገረለትን ድንቅ ኳስ አየር ላይ በቮሊ በመምታት የውድድር ዘመኑን የመጀመሪያ ግብ በግሩም ሁኔታ አስቆጥሮ ደደቢትን መሪ አድርጓል። ከግቡ መቆጠር በኋላ የድሬዳዋ ከተማ ተጫዋቾች ከሳጥን ውጪ በመምታት አቻ የሚያደርጋቸውን ግብ ለማግኘት ጥረት ቢያደርጉም ተስፋዬ ዲባባ ሞክሮ በታሪክ ጌትነት ከተመለሰበት ኳስ ውጪ ለግብ የቀረበ ሙከራ አልታየም።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ደደቢት 44 ነጥቦችን በመያዝ ለ30 ደቂቃዎች ያህል ሊጉን መምራት ችሎ የነበረ ቢሆንም ቅዱስ ጊዮርጊስ ማሸነፉን ተከትሎ በሁለተኛ ደረጃ ተቀምጧል። ተሸናፊው ድሬዳዋ ከተማ በ28 ነጥብ ከወራጅ ቀጠናው በሁለት ነጥቦች ብቻ ከፍ ብሎ 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

Leave a Reply