የጨዋታ ሪፖርት | ቅዱስ ጊዮርጊስ የወልድያን በሜዳ ያለመሸነፍ ጉዞ ገትቷል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 25ኛ ሳምንት ዛሬም ቀጥሎ ሲውል ወደ ወልድያ ያመራው ቅዱስ ጊዮርጊስ 1-0 በማሸነፍ ለደቂቃዎች የተነጠቀውን የሊግ መሪነት መልሶ ተረክቧል፡፡ የወልድያን የ14 የፕሪምየር ሊግ የሜዳ ጨዋታ ያለመሸነፍ ጉዞንም ገትቷል፡፡

ከትላንት በስቲያ ከዚህ አለም በሞት የተለዩት የቀድሞ ዳኛ እና ኮምሽነር አቶ ከማል እስማኤልን በአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት በማሰብ የተጀመረው ጨዋታ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ በበርካታ ተመልካች እና በሁለቱ ቡድኖች ደጋፊዎች ደማቅ ድባብ ታጅቦ ተካሂዷል፡፡ ጨዋታውን ለመከታተል ከደሴ ፣ ቆቦ እና ሌሎች በወልድያ ዙሪያ ካሉ ከተሞች በርካታ ቁጥር ያለው ደጋፊ መምጣቱን ተከትሎም አዲሱ የወልድያ ስተታድም ከምንግዜውም የበለጠ የደጋፊዎች ብዛት ታይቶበታል።

የጊዮርጊሶች መጠነኛ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ እና ጥቂት የግብ ሙከራዎች የታየበት የመጀመሪያው አጋማሽ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በፕሪንስ ሰቨሪንሆ እና አብዱልከሪም ኒኪማ አማካኝነት በተሻጋሪ ኳሶች ላይ ያመዘነ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ወልድያዎች በአንፃሩ በመልሶ ማጥቃት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ማደድረግ ችለው ነበር፡፡

በ11ኛው ደቂቃ ያሬድ ሀሰን በመልሶ ማጥቃት የተገኘችውን ኳስ ከሳጥኑ የቀኝ ጠርዝ ወደ ጎል ሞክሮ ግብ ጠባቂው የያዘበት የጨዋታው የመጀመርያ ሙከራ ነበር፡፡ ከ4 ደቂቃዎች በኋላ አዳነ ግርማ ከመስመር የተሻማውን ኳስ ለተስፋዬ አለባቸው አመቻችቶለት ተስፋዬ በጠንካራ ምት ቢሞክረውም በጎሉ አናት ወደ ውጪ ወጥቶበታል፡፡

በመጀመርያዎቹ 25 ደቂቃዎች ሁለቱም በመረጡት የጨዋታ አቀራረብ የግብ እድል ለመፍጠር ሞክረዋል፡፡ በወልድያ በኩል 16ኛው ደቂቃ ሙሉጌታ ረጋሳ በመልሶ ማጥቃት በፈጣን ሩጫ ይዞ የገባውን ኳስ ሰላሀዲን በርጊቾን አታሎ በጥሩ ሁኔታ ወደ ጎል ቢመታውም ዘሪሁን ያዳነበት ፤ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ደግሞ በ22ኛው ደቂቃ ፕሪንስ በቀኝ መስመር በኩል ፍጥነቱን ተጠቅሞ የወልድያ ተከላካዮችን በማለፍ መሬት ለመሬት ያሻገረውን ሳላዲን ሰኢድ ሞክሮ ወደ ውጪ የወጣበት ለዚህ ማሳያ ነበሩ፡፡

የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ በመጣ ቁጥር የሁለቱም የማጥቃት እንቅስቃሴ እየተገደበ እና በተደጋጋሚ ጥፋቶች በሚነፋ የዳኛ ፊሽካ እየተቆራረጠ የመጀመርያው አጋማሽ ያለ ግብ ተጠናቋል፡፡ በመጀመርያው አጋማሽ የመጨረሻዎቹ 15 ደቂቃዎችም ወልድያዎች በ31ኛው ደቂቃ ያሬድ ብርሀኑ ካመከነው ጥሩ የግብ እድል ውጪ የሚጠቀስ የግብ ሙከራ አልነበረም፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ በሁለቱም በኩል ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ ቢታይም ከመጀመሪያው አጋማሽ ያነሰ የግብ ሙከራ የተስተናገደበት ነበር፡፡  በ54ኛው ደቂቃ ሳላሀዲን በግምባሩ አመቻችቶ የሰጠውን ኳስ በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው ፕሪንስ ሞክሮ ወደ ውጭ የወጣበት ሊጠቀስ የሚችል የግብ ሙከራ ነበር፡፡

ጨዋታው በዚህ ሁኔታ ቀጥሎ በ67ኛው ደቂቃ ሳላሀዲን ሰኢድ ኳሱን ከቀኝ መስመር ወደ መሀል እየገፋ በሚገባት ጊዜ የወልድያ ተከላካዩች ወደእርሱ መሳባቸውን ተከትሎ ለብቻው ተነጥሎ በጥሩ አቋቋም ላይ ለነበረው አብዱልከሪም ንኪማ አቀብሎት ቡርኪናፋሷዊው አማካይ አክርሮ በመምታት በወልድያ መረብ ላይ አሳርፏታል፡፡

ከዚህ ጎል መቆጠር በኋላ ወልድያዎች አቻ ለመሆን የሚያስችላቸውን ግብ ለማስቆጠር ተጭነው ተጫውተዋል፡፡ አሰልጣኝ ንጉሴ አጥቂዎቹ በድሩ ኑርሁሴን እና ጫላ ድሪባ እንዲሁም አማካዩን ሙሉጌታ ወልድጊዩርጊስን ቀይረው በማስገባት የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስደው ተጭነው ለመጫወት የሞከሩ ቢሆንም በ76ኛው ያሬድ ብርሀኑ ከአንዷለም የተሻገረለትን ኳስ በግምባሩ በመግጨት ሞክሮ ዘሪሁን ከያዘበት ሙከራ ውጭ በሜዳው ሶስተኛ ክፍል ላይ መናበብ እና ግልፅ የግብ እድል መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡

ደጉ ደበበ ፣ ናትናኤል ዘለቀ እና አቡበክር ሳኒን ቀይረው ያስገቡት ፈረሰኞቹ በአንጻሩ አፈግፍገው በመጫወት ውጤቱን አስጠብቆ ለመውጣት ያደረጉት ጥረት ተሳክቶላቸው ጨዋታውን 1-0 በሆነ ውጤት አሸንፈዋል።

ውጤቱን ተከትሎ ደደቢት ለደቂቃዎች ይዞት የነበረውን መሪነት በ46 ነጥቦች ሲረከብ በአጠቃላይ በሁሉም ውድድሮች ለ2 አመታት ፣ ለ29 ጨዋታዎች (በፕሪምየር ሊጉ 14 ጨዋታዎች) በሜዳው ያልተሸነፈው ወልድያን ጉዞ መግታት ችሏል፡፡ ወልድያ ወደ አዲሱ መሀመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ስታድየም ከተዛወረ ወዲህም በዚህ ሜዳ የመጀመርያ ሽንፈቱን አስተናግዷል፡፡

1 Comment

Leave a Reply