የጨዋታ ሪፖርት | ንግድ ባንክ ፋሲልን በመረታት ላለመውረድ በሚያደርገው ጥረት ቀጥሏል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 25ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታዲየም ፋሲል ከተማን ያስተናገደው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 3-1 በማሸነፍ በሊጉ ለመቆየት ለሚያደርገው ትግል ወሳኝ የሆነ ድል አስመዝግቧል።

ጨዋታው ከቀናት በፊት ዲላ ላይ ጌዲዮ ዲላ ከ ሀዋሳ ከተማ ጋር ያደረጉትን የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ በኮሚሽነርነት መርተው ሲመለሱ ባጋጠማቸው የመኪና አደጋ ከዚህ አለም በሞት ለተለዩት አቶ ከማል እስማኤል የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት በማድረግ ነበር የተጀመረው።

ፋሲሎች በጨዋታው በ4-2-3-1 ቅርፅ ከተከላካይ አማካዮቹ ፊት በቀኝ ኤርሚያስ ሀይሉ፣ በግራ አብዱልራህማን ሙባረክ እንዲሁም ከፊት አጥቂው ኤዶም ሆሮሶውቪ ጀርባ ኤፍሬም አለሙን በመጠቀም ከመስመር በሚነሱ ኳሶች ግብ ለማስቆጠር ሞክረዋል። ንግድ ባንኮችም ተመሳሳይ የጨዋታ አቀራረብ የነበራቸው ሲሆን የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውም በዋነኛነት ኳስን ለቢንያም አሰፋ በማድረሱ ላይ ያተኮረ ነበር።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመጀመሪያውን ግብ ለማስቆጠር ብዙ ጊዜ ያልወሰደበት ሲሆን ገና በ3ኛው ደቂቃም ቢንያም አሰፋ በፋሲል ከተማ የግብ ክልል ውስጥ በታደለ ባይሳ ተጠልፎ በመውደቁ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት እራሱ ቢንያም በማስቆጠር ቡድኑን መሪ አድርጓል።

ፋሲል ከተማዎች ገና ጨዋታው ከመጀመሩ በተቆጠረባቸው ግብ ሳይደናገጡ በማጥቃት አጨዋወታቸው የቀጠሉ ሲሆን በተለይም ከመከላከል ወደ ማጥቃት በሚያደርጉት ሽግግር ኳስን በፍጥነት የሚያንሸራሽሩበት መንገድ ጥሩ የሚባል ነበር። በ9ኛው ደቂቃ ኤዶም ያመቻቸለትን ኳስ ኤፍሬም አለሙ ሞክሮ ግብ ጠባቂው ኢማኑኤል ፌቮ ያዳነበት እና በ19ኛው ደቂቃም ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ ሰዒድ ሀሰን በግንባሩ ገጭቶ በተከላካዮች የተመለሰበት ኳሶች ፋሲልን አቻ ለማድረግ የተቃረቡ ሙከራዎች ነበሩ። በጨዋታው 23ኛ ደቂቃም አምሳሉ ጥላሁን ከቅጣት ምት ያሻማውን ኳስ ይስሀቅ መኩሪያ በግንባሩ ጨርፎ በማስቆጠር አፄዎቹን አቻ ማድረግ ችሏል። ከግቡ መቆጠር በኋላ በአመዛኙ በመሀል ሜዳ እንቅስቃሴ ላይ ያተኮረ ጨዋታ የተመለከትን ሲሆን ከርቀት ከሚመቱ ዒላማቸውን ያልጠበቁ ኳሶች ውጪም ይህ ነው የሚባል ሙከራ ሳይስተናገድ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።

በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ፋሲሎች ወደመሪነቱ የሚያመጣቸውን ግብ ለማስቆጠር ተደጋጋሚ ሙከራዎች ያደረጉ ሲሆን በ52ኛው ደቂቃ  ኤፍሬም አለሙ ከርቀት አክርሮ መትቶ ለጥቂት የወጣበት፣ እንዲሁም አብዱልራህማን ሙባረክ በሁለት አጋጣሚዎች ከቀኝ መስመር ኳስን ይዞ ወደ አደጋ ክልሉ ገብቶ ያመከናቸው ዕድሎች ለአፄዎቹ የሚያስቆጩ ነበሩ። ኤርሚያስ ሀይሉ እና ኤፍሬም አለሙ ከሳጥኑ ውጪ በመምታት ግብ ለማስቆጠር ተጨማሪ ሙከራዎችን ያደረጉ ቢሆንም ሊሳካላቸው አልቻለም ነበር።

ንግድ ባንኮች በበኩላቸው በፍቅረየሱስ ተ/መድህን እና ተቀይሮ በገባው ፒተር ኑዋዲኬ አማካኝነት ሙከራዎችን ያደረጉ ሲሆን በ86ኛው ደቂቃም ወደ መሪነቱ የመለሳቸውን ግብ ማግኘት ችለዋል። ናይጄሪያዊው አጥቂ ፒተር ኑዋዲኬ ከግቡ 25 ሜትር አካባቢ በግራ በኩል ያገኘውን ቅጣት ምት በቀጥታ መትቶ በማስቆጠር ንግድ ባንክን ዳግም መሪ አድርጓል። ከግቡ መቆጠር በኋላ የፋሲል ከተማ ተጫዋቾች በቀረው ጥቂት ጊዜ ግብ ለማስቆጠር ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ በተጋጣሚያቸው የሜዳ ክፍል ውስጥ በመግባት መጫወት የጀመሩ ሲሆን መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ከተጠናቀቀ በኋላ በጭማሪ ሰዓት ንግድ ባንኮች በመልሶ ማጥቃት ያገኙትን ዕድል ተጠቅመው ልዩነቱን ማስፋት ችለዋል። ፍቅረየሱስ ተ/መድህን በሚደነቅ ሁኔታ ኳስን እየገፋ ወደ ፋሲል የግብ ክልል ከተጠጋ በኋላ ያሾለከለትን ኳስ ቢንያም አሰፋ ወደ ግብ በመለወጥ የባንክን አሸናፊነት አስተማማኝ አድርጓል።

ጨዋታው ፋሲል ከተማ አዲስ አበባ ላይ በውድድር ዓመቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሸነፈበት ጨዋታ ሆኖ ሲመዘገብ ውጤቱን ተከትሎ የመጣ የደረጃ ለውጥ ግን የለም። አሸናፊው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነጥቡን ወደ 23 በማሳደግ በሊጉ ለመቆየት የሚያደርገው ጥረት ላይ ነፍስ ቢዘራበትም አሁንም 13ኛ ደረጃ ላይ ካለው ጅማ አባ ቡና በ4 ነጥብ ርቆ በ15ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ባሳለፍነው ሳምንት በአዲስ አበባ ከተማ፣ ዛሬ ደግሞ በንግድ ባንክ ተሸንፎ 6 ነጥቦችን ያጣው ፋሲል ከተማ በበኩሉ ወደ ሻምፒዮንነት ፉክክሩ መጠጋት ሳይችል በ35 ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *