የ2017 ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የምድብ ድልድል ይፋ ሆኗል

የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌድሬሽን በስሩ ከሚስተዳድራቸው ውድድሮች በክለቦች መካከል የሚደረገው አንዱ ነው፡፡ የቻምፒየንስ ሊጉ እና ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ድልድል ዛሬ ከሰዓት ካይሮ በሚገኘው የካፍ ዋና ፅህፈት ቤት ፕሬዝደንቱ አህመድ አህመድ በተገኙበት ተደርጓል፡፡

ቻምፒየንስ ሊግ

በቻምፒየንስ ሊጉ የምድብ ድልድል ሁለቱ የሱዳን ሃያላን ክለቦች በአንድ ምድብ ሲደለደሉ፣ የኢትዮጵያው ተወካይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከወቅቱ አሸናፊ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ፣ ኤስፔራንስ ደ ቱኒዝ እና ኤኤስ ቪታ ክለብ ጋር ተመድቧል፡፡ የ2016 የቻምፒየንስ ሊጉ አሸናፊ ዛማሌክ ከአልጄሪያው ዩኤስኤም አርጀር ጋር ይፋጠጣል፡፡ በዘንድሮው የውድድር ዘመን በሊጉ ደካማን ጉዞን እያደረገ ለሚገኘው ዛማሌክ የዘንድሮው የቻምፒየንስ ሊግ ውድድር በደጋፊዎቹ ያጣውን አመኔታ ለመመለስ እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ አል አሃሊ ዳግም ከዋይዳድ ካዛብላንካ ጋር ተመድቧል፡፡ ዋይዳድ ባሳለፍነው ሳምንት በካዛብላንካ ደርቢ የከተማ ባላንጣውን ራጃ ካዛብላንካን አሸንፎ የሞሮኮ ቦቶላ ሊግ ክቡን ከፉስ ራባት ለመንጠቅ መንገድ ላይ ነው፡፡ የዛምቢያው ዛናኮም አምና ዜስኮ ዩናይትድ በአሃሊ ላይ የወሰደው ብልጫ ለመድገም በዚሁ ምድብ ውስጥ ይገኛል፡፡

የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታዎች ከግንቦት 4-6 ባሉት ቀናት ውስጥ ሲደረጉ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ደቡብ አፍሪካ በማቅናት ከማሜሎዲ ሰንዳውንስ ጋር የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታውን ያካሂዳል፡፡

ሙሉ ድልድል

ምድብ ሀ፡ ኤቷል ስፖርቲቭ ደ ሳህል (ቱኒዚያ)፣ አል ሂላል (ሱዳን)፣ ኤል ሜሪክ (ሱዳን)፣ ክለብ ፌሮቫያሪዮ ደ ቤይራ (ሞዛምቢክ)

ምድብ ለ፡ ዛማሌክ (ግብፅ)፣ ዩኤስኤም አልጀር (አልጄሪያ)፣ አል አሃሊ ትሪፖሊ (ሊቢያ)፣ ካፕስ ዩናይትድ (ዚምባቡዌ)

ምድብ ሐ፡ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ (ደቡብ አፍሪካ)፣ ኤስፔራንስ ደ ቱኒዝ (ቱኒዚያ)፣ ኤኤስ ቪታ ክለብ (ዲ.ሪ. ኮንጎ)፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ (ኢትዮጵያ)

ምድብ መ፡ አል አሃሊ (ግብፅ)፣ ዋይዳድ አትሌቲክ ክለብ (ሞሮኮ)፣ ኮተን ስፖርት (ካሜሮን)፣ ዛናኮ (ዛምቢያ)

ኮንፌድሬሽን ዋንጫ

አምስት የሰሜን አፍሪካ ክለቦች በሚሳተፉበት የዘንድሮ የኮንፌድሬሽን ዋንጫ የወቅቱ አሸናፊ ቲፒ ማዜምቤ በምድብ አራት ከሱፐርስፖርት ዩናይትድ ጋር ተገናኝቷል፡፡ በቻምፒየንስ ሊጉ አምና እስከ ፍፃሜ ግማሽ መጓዝ የቻለው ዜስኮ ዩናይተድ በምድብ ሶስት ውስጥ ተካቷል፡፡ ምደብ አንድ ከቀሪዎቹ ምድብ ጠንካራ ፉክክር እንደሚስተናገድበት ይጠበቃል፡፡ በዚሁ ምድብ የዩጋንዳው ኬሲሲኤ ተገኝቷል፡፡

እንደ ቻምፒየንስ ሊጉ ሁሉ የምድብ የመክፈቻ ጨዋታዎች ከግንቦት 4-6 ባሉት ቀናት የሚካሄዱ ይሆናል፡፡

ምድብ ሀ፡ ፋት ዩኒየን ስፖርት (ሞሮኮ)፣ ክለብ አፍሪኬን (ቱኒዚያ)፣ ሪቨርስ ዩናይትድ (ናይጄሪያ)፣ ካምፓላ ሲቲ ካውንስል ኦቶሪቲ (ዩጋንዳ)

ምድብ ለ፡ ክለብ ስፖርቲቭ ሴፋክሲየን (ቱኒዚያ)፣ ፕላቲኒየም ስታርስ (ደቡብ አፍሪካ)፣ ሞሊዲያ ክለብ ደ አልጀር (አልጄሪያ)፣ ምባባኔ ስዋሎስ (ስዋዚላንድ)

ምድብ ሐ፡ ዜስኮ ዩናይትድ (ዛምቢያ)፣ ክለብ ሬክሬቲቮ ዴስፖርቲቮ ደ ሊቦሎ (አንጎላ)፣ አል ሂላል ኦባያድ (ሱዳን)፣ ስሞሃ (ግብፅ)

ምድብ መ፡ ቲፒ ማዜምቤ (ዲ.ሪ. ኮንጎ)፣ ሱፐርስፖርት ዩናይትድ (ደቡብ አፍሪካ)፣ ሆሮያ (ጊኒ)፣ ሲኤፍ ሞናና (ጋቦን)

Leave a Reply