የፋሲል ከተማው አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ ክለቡ በትላንትናው እለት በኢትዮጵያ ንግደድ ባንክ 3-1 መሸነፉን ተከትሎ ከክለቡ አሰልጣኝነት ለመልቀቅ መወሰናቸው ቢነገርም አሰልጣኙ ለህክምና ወደ ታይላንድ እንደሚያመሩ እንጂ ከክለቡ ጋር ለመለያየት እንዳልወሰኑ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡
በዘንድሮ አመት የኢትዮዽያ ፕሪሚየር ሊግ ፋሲል ከተማን ጠንካራ ተፎካካሪ አድርጎ የቀረበው አሰልጣኝ ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ የጤና ሁኔታ አሳሳቢ በመሆኑ ምክንያት ትላንት ከኢትዮዽያ ንግድ ባንክ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ለቡድኑ አባላት ቅዳሜ ወደ ታይላንድ እንደሚሄድ የገለፀ ሲሆን በዚህም ተጨዋቾቹ የቡድኑ አባላት ተደናግጠው እንደነበረ ለማወቅ ችለናል።
በጉዳዩ ዙርያ ሶከር ኢትዮዽያ ዛሬ ማለዳ ላይ ከአሰልጣኝ ዘማርያም ጋር በአደረገችው አጭር ቆይታ የጤንነቱ ሁኔታ አሳሳቢ እንደሆነ ገልፆ የፊታችን ቅዳሜ ወደ ታይላንድ እንደሚያቀና ፤ ሕክምናውንም በአግባቡ ተከታትሎ ለመምጣት ለአንድ ወር እንደሚቆይ አሳውቋል፡፡
አሰልጣኝ ዘማርያም ከክለቡ እና ደጋፊዎች ጋር ልዩነት ስለመፈጠሩ ቢነገርም ችግር እንዳልተፈጠረና ክለቡን ለመልቀቅ እንዳልወሰነ ገልጿል፡፡ ” ከክለቡ ስለ መልቀቅ አልወሰንኩም፡፡ አሁን የጤናዬ ሁኔታ ነው የሚያሳስበኝ ፤ ቅድሚያ የምሰጠውም ለእርሱ ነው። ከደጋፊውም ጋር ቢሆን በጣም የማይረሳ የፍቅር ታሪክ ነው ያለኝ፡፡ ምንም አይነት ችግል የለኝም ፤ ጤናማ የሆነ ግኑኝነት ነው ያለን” በማለት ገልጿል፡፡
ፋሲል ከተማ በቀሩት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ላይ ክለቡን በዋና አሰልጣኝነት የሚመራውን አሰልጣኝ ለማወቅ ባደረግነው ጥረት ፋሲል ከተማ የዘማርያም ረዳት በሆነው ምንተስኖት ጌጡ የሚመራ ይሆናል፡፡