የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ 18ኛ ሳምንት ዛሬ በአዲስ አበባ ስታድየም በተካሄዱ ሁለት የምድብ ለ ጨዋታዎች ቀጥሎ ሲውል ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አንድ ጨዋታ እየቀረው ምድብ ለን በበላይነት ማጠናቀቁን አረጋግጧል፡፡ ሲዳማ ቡናም ልደታ ክፍለ ከተማን በማሸነፍ እስከ አምስተኛ ባለው ደረጃ የመጨረስ እድሉን አስፍቷል፡
ቅድሚያ በ8:30 የተገናኙት ልደታ ክፍለ ከተማና ሲዳማ ቡና ነበሩ፡፡ በጨዋታው ሲዳማ ቡናዎች ከፍፁም የጨዋታ የበላይነት ጋር 3-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል፡፡ ሲዳማ ቡና በመጀመሪያው አጋማሽ በቲቲና ኡስማን እና ረድኤት አስረሳሃኝ እንዲሁም በሁለተኛው አጋማሽ 64ኛው ደቂቃ ላይ ተከላካይዋ ገነሜ ወርቁ የልደታን አራት ተጫዋቾች እና ግብጠባቂዋን በማለፍ እጅግ ውብ የሆነችን ግብ አስቆጥራ 3-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል፡፡
ሲዳማ ቡናዎች ነጥባቸውን ከ24 ወደ 27 ከፍ በማድረግ ከነበሩበት 6ኛ ደረጃ ቢያንስ እስከ ነገ ወደ 4ኛ ደረጃ ከፍ በማለት እስካሁን ባለየለት የሊጉን ተሳታፊ ቁጥሮች የመለየት ሂደት እንደ መለያ መስፈርት የተቀመጠውን 5ኛ ደረጃ ይዘው በሊጉ ለመቆየት ያላቸውን ተስፋ አለምልመዋል፡፡
በዚህ ምድብ ለ የሚገኙት ቅዱስ ጊዮርጊስና አዲስአበባ ከተማ 27 እና 25 ነጥብ በመያዝ ከሲዳማ ቡና ቀጥሎ ያለውን 5ኛና 6ኛ ደረጃ የያዙት ቡድኖች ነገ ወሳኝ የተባለውን ጨዋታ በ8:30 በአዲስ አበባ ስታድየም ያደርጋሉ፡፡
በመቀጠል የተገናኙት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ቅድስት ማሪያም ዩኒቨርስቲ ነበሩ፡፡ በጨዋታውም ንግድ ባንኮች በቀላሉ ተጋጣሚያቸውን 4-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የምድቡን የበላይነት አረጋግጠዋል፡፡
በጨዋታው የንግድ ባንክን የመጀመሪያውን ግብ ያስቆጠረችው አምና በሀዋሳ ከተማ ስኬታማ ጊዜያትን ማሳለፍ የቻለችው ካጋጠማት የረጅም ጊዜ ጉዳት አገግማ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ መጀመርያ 11 አሰላለፍ ገብታ የተሰለፈችው አዲስ ንጉሴ ነች፡፡ ቀሪዎቹን ግቦች ረሂማ ዘርጋው ሁለት እንዲሁም ብዙነሽ ሲሳይ ማስቆጠር ችለዋል፡፡
በዚህ ውጤት መሠረት ምድብ ለን አንድ ጨዋታ እየቀረው በ46 ነጥብ የበላይ ሆኖ ያጠናቀቀው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከምድብ ሀ አሸናፊው ደደቢት ጋር በመጪው ግንቦት 6 በአዲስ አበባ ስታድየም የፕሪምየር ሊጉ አሸናፊ ለመሆን የሚጫወት ይሆናል፡፡