የማሊ እገዳ መነሳትን ተከትሎ የኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን ከአፍሪካ ዋንጫው ቀርቷል

ዓለምአቀፉ የእግርኳስ ማህበር (ፊፋ) በማሊ ላይ በጣለው እገዳ ምክንያት ጋቦን በምታዘጋጀው የ2017ቱ የአፍሪካ ታዳጊዎች ዋንጫ የመሳተፍ አጋጣሚውን አግኝቶ በዝግጅት ላይ የነበረው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በውድድሩ የመሳተፍ ዕድሉ ጨልሟል፡፡ ፊፋ በማሊ ላይ የጣለውን የኢንተርናሽናል ውድድር እገዳ በማንሳቱ የማሊ ብሔራዊ ቡድን ወደ ውድድሩ መመለሱን ተከትሎ ነው የቀይ ቀበሮዎቹ የጋቦን ጉዞ የተሰናከለው፡፡

የማሊ የስፖርት ሚኒስቴር የሃገሪቱ የእግርኳስ ፌዴሬሽን አመራሮችን ከስራ በማሰናበቱ ፊፋ እግርኳሱ ውስጥ መንግስት ጣልቃ ገብቷል በሚል ምዕራብ አፍሪካዊቷን ሃገር ከማንኛውም ኢንተርናሽናል ጨዋታዎች አግዶ ነበር። በአፍሪካ የክለቦች ውድድር ላይ ተሳታፊ የነበሩት የባማኮ ክለቦች ጆሊባ እና ኦንዜ ክሬቸርስም በኮንፌዴሬሽን ዋንጫው የማጣሪያ ጨዋታዎች በፎርፌ ተሸንፈው ከውድድሩ እንዲሰናበቱ ሆኗል።

ቀይ ቀበሮዎቹ በማጣሪያው በማሊ በድምር ውጤት 4-1 ተሸንፈው ከውድድር ውጪ ቢሆኑም ካፍ  ግንቦት 6 በሚጀመረው የአፍሪካ ታዳጊዎች ዋንጫ ላይ ማሊን በመተካት እንዲሳተፉ ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጥያቄ በማቅረቡ የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በውድድሩ ለመሳተፍ ውሳኔ አሳልፏል። በአሠልጣኝ አጥናፉ አለሙ የሚመራው ቡድንም 36 የሚሆኑ በማጣርያው ሂደት የነበሩ እና አዲስ የተቀላቀሉ ተጫዋቾችን በመያዝ ዝግጅት ማድረግ ጀምሮ ነበር።

ነገርግን የማሊ ስፖርት ሚኒስቴር እስከ ሚያዝያ 22 በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ የቀድሞ የእግርኳሱ አመራሮችን ወደ ስፍራቸው መመለስን ጨምሮ ሌሎች ማስተካከያዎችን ማድረግ በመቻሉ እገዳው እንዲነሳ ሆኗል። ማሊ ዳግም በኢንተርናሽናል ውድድሮች ላይ መሳተፍ እንደምትችልም ሴኔጋላዊቷ የፊፋ ዋና ፀሀፊ ፋትማ ሳሞውራ ሚያዝያ 20 ቀን ለባለድርሻ አካላት በፃፉት ደብዳቤ አስታውቀዋል። ውሳኔውን ተከትሎም ማሊ ወደ ጋቦኑ የአፍሪካ ወጣቶች ዋንጫ የተመለሰች ሲሆን በምድብ ለ ከታንዛኒያ፣ አንጎላ እና ኒጀር ጋር የምትጫወት ይሆናል።

የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን ቀጣይ ዕጣ ፋንታ ምን እንደሆነ በካፍም ሆነ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በኩል የተባለ ነገር ባይኖርም ኢትዮጵያ የምትሳተፈው የተቀመጠው ቀነ ገደብ እስኪያልፍ ድረስ ማሊ ችግሯን ካልፈታች እንደሆነ በመገለጹ በውድድሩ የመሳተፍ ዕድሉ ያከተመለት ይመስላል። ኢትዮጵያም እ.ኤ.አ. በ1997 ቦትስዋና ላይ ከተደረገው የአፍሪካ ታዳጊዎች ዋንጫ በኋላ ወደ ውድድሩ ለመመለስ ቢያንስ ሁለት ተጨማሪ ዓመታትን መጠበቅ ይኖርባታል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *