ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | የ18ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ሲጠናቀቁ አካዳሚ ፣ አርባምንጭ እና ደደቢት አሸንፈዋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ 18ኛ ሳምንት ዛሬ በተደረጉ ሶስት ጨዋታዎች ሲገባደድ ደደቢተ ፣ ኢ/ወ/ስ/ አካዳሚ እና አርባምንጭ ከተማ ድል አስመዝግበዋል፡፡

በአዲስ አበባ ስታድየም 08:30 ላይ ኢትዮጵያ ቡናን የገጠመው ኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ 2-0 ማሸነፍ ችሏል፡፡ የአካዳሚን ሁለት የማሸነፍያ ጎሎች አምበሏ የአብስራ ይታይህ ከእረፍት በፊት እና በኃላ አስቆጥራለች፡፡ ድሉን ተከትሎ አካዳሚ ነጥቡን 16 በማድረስ አንድ ደረጃ ማሻሻል ችሏል፡፡

ቀጥሎ 10:30 ላይ ደደቢት ድሬዳዋ ከተማን አስተናግዶ 3-0 አሸንፏል፡፡ ደደቢት በተፈተነበት የመጀመርያ አጋማሽ ድሬዳዋ ከተማዎች በርካታ የግብ እድል ቢፈጥሩም ብርቱካን ገብረክርስቶስ ባስቆጠረችው ግሩም ጎል ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡ ከእረፍት መልስ የተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ጨዋታውን የተቆጣጠረው ደደቢት በሎዛ አበራ እና ሰናይት ባሩዳ ተጨማሪ ጎሎች 3-0 ማሸነፍ ችሏል፡፡

በምድብ ለ አርባምንጭ ላይ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለከተማን ያስተናገደው አርባምንጭ ከተማ 2-0 ማሸነፍ ችሏል፡፡

ሊጠናቀቅ የ1 ሳምንት መርሀ ግብር ብቻ የቀረው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ምድብ ሀን ደደቢት ፣ ምድብ ለን ኢትዮጵያ ንግድ ባነክ ማሸነፋቸውን ሲያረጋግጡ ፣ በምድብ ሀ አዳማ ከተማ በቀጣይ ጨዋታ ከ10 የግብ ልዩነት በታች መሸነፍ አልያም የአቻ ውጤት በሁለተኛ ደረጃ ለማጠናቀቅ በቂው ሲሆን ሀዋሳ ከተማ ከምድብ ለ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁን አረጋግጧል፡፡ በዚህም ግንቦት 6 የምድብ ሀ አሸናፊ ከ ምድብ ለ አሸናፊ ለዋንጫ ፣ የምድብ ሀ 2ኛ ከ ምድብ ለ ሁለተኛ ለ3ኛ ደረጃ ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ይሆናል፡፡

የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን የደደቢቷ ሎዛ አበራ በ30 ጎሎች ስትመራ የሀዋሳ ከተማዋ አይናለም አሳምነው በ23 ጎሎች ትከተላለች፡፡

 

Leave a Reply