የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 26ኛ ሳምንት የቡድን ዜናዎች

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 26ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገ እና ሰኞ በሀገሪቱ የተለያዩ ከተሞች ይካሄዳሉ፡፡ ሶከር ኢትዮጵያም እንደተለመደው ከጨዋታዎቹ ጋር የተያያዙ የቡድን ዜናዎች ማለትም የጉዳት እና ቅጣት ዜናዎች እንዲሁም ወደ ጨዋታ የሚመለሱ ተጫዋቾችን እነዲህ ባለ መልኩ አጠናቅራዋለች፡፡

እሁድ ሚያዝያ 22 ቀን 2009

ኢትዮጵያ ቡና ከ ጅማ አባ ቡና (08:30 አአ ስታድየም)

ቡናማዎቹ አሁንም የኤልያስ ማሞ እና አብዱልከሪም መሀመድን ግልጋሎት በጉዳት የማያገኙ ሲሆን እያሱ ታምሩ ከጉዳቱ በማገገሙ በጨዋታው ላይ ሊሰለፍ ይችላል፡፡ በጅማ አባ ቡና በኩል ኪዳኔ አሰፋ ከጉዳት አገግሞ ለጨዋታው ብቁ ሆኗል፡፡

ወላይታ ድቻ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ (09:00 ሶዶ)

ባለሜዳዎቹ ድቻዎች እስከ ውድድር አመቱ መጨረሻ በጉዳት የሚያጡት ቶማስ ስምረቱን የማያሰልፉ ሲሆን በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል ሁሉም ተጫዋቾች ለጨዋታው ብቁ መሆናቸው ታውቋል፡፡

ሲዳማ ቡና ከ አአ ከተማ (09:00 ይርጋለም)

የሊጉ ግርጌ ላይ የሚገኘው አአ ከተማ አሁንም በተጫዋቾች ጉዳት መታመሱኖ ቀጥሏል፡፡ እንየው ካሳሁን በብሽሽት ጉዳት ወደ ይርጋለም ያልተጓዘ ሲሆን ተክለማርያም ሻንቆ ፣ ዘሪሁን ብርሀኑ ፣ አቤል ዘውዱ ፣ ዮናታን ብርሀነ እና ሙሀጅር መኪ አሁንም ጉዳት ላይ የሚገኙ ተጫዋቾች ናቸው፡፡ በሲዳማ ቡና በኩል ደግሞ ጸጋዬ ባልቻ በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጪ መሆኑ ታውቋል፡፡

አዳማ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ (09:00 አዳማ)

አዳማ አሁንም የብሩክ ቃልቦሬ ፣ ሞገስ ታደሰ ፣ ታፈሰ ተስፋዬ እና ተስፋዬ በቀለን ግልጋሎት የማያገኝ ሲሆን ሲሳይ ቶሊ እና ሚካኤል ጆርጅ ከጉዳታቸው በማገግማቸው ወደ ጨዋታ ይመለሳሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በንግድ ባንክ በኩል ጥላሁን ወልዴ የመሰለፉ ጉዳይ አጠራጣሪ ሲሆን ግርማ በቀለ ከ5 ቢጫ ቅጣት የሚመለስ ይሆናል፡፡

መከላከያ ከ ደደቢት (10:30 አአ ስታድየም)

በደደቢት በኩል ሮበን ኦባማ በትከሻ ጉዳት ለሳምንታት ከሜዳ የሚርቅ ሲሆን ሽመክት ጉግሳ ከጉዳት ፣ ክሌመንት አዞንቶ ከ5 ቢጫ ቅጣት ወደ ሜዳ የሚመለሱ ተጫዋቾች ናቸው፡፡ የአክሊሉ አየነው ለጨዋታው ብቁ የመሆን ጉዳይ ደግሞ 50/50 ነው ተብሏል፡፡ በመከላከያ በኩል የመስመር ተከላካዩ ሽመልስ ተገኝ የመሰለፉ ጉዳይ አጠራጣሪ ከመሆኑ በቀር ሌሎቹ ለጨዋታው ብቁ ሆነዋል፡፡

ሰኞ ሚያዝያ 23 ቀን 2009

ፋሲል ከተማ ከ አርባምንጭ ከተማ (09:00 ጎንደር)

የአሰልጣኝ ለውጥ ባደረገው ፋሲል ከተማ በኩል ሰለሞን ገብረመድህን እና ያሬድ ዝናቡ ጉዳት ላይ ሲሆኑ ፍቅረማርያም አለሙ ከጉዳት አገግሞ ለጨዋታው ብቁ ሆኗል፡፡ በአርባምንጭ በኩል ደግሞ ግብ ጠባቂው ጃክሰን ፊጣ በጉዳት ከጨዋታው ውጪ ሆኗል፡፡

ድሬዳዋ ከተማ ከ ወልድያ (10:00 ድሬዳዋ)

በሁለቱም በኩል የቅጣትም ሆነ የጉዳት ዜና የለም፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ሀዋሳ ከተማ (10:00 አአ ስታድየም)

የቅዱስ ጊዮርጊስ ወሳኝ ተሰላፊዎች የሆኑት ሮበርት ኦዶንካራ እና በሀይሉ አሰፋ ከጉዳታቸው አገግመው ልምምድ በመጀመራቸው ለጨዋታው ብቁ ሲሆኑ አዲስ የተመዘገበ የተጫዋች ጉዳት የለም፡፡ በሀዋሳ ከተማ በኩል መሳይ ጳውሎስ ከጉዳት ሲመለስ መላኩ ወልዴ በዚህም ጨዋታ አይኖርም፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *