የ26ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ዛሬ በተለያዩ ከተሞች ቀጥሎ ሲውል የዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ኢትዮጵያ ቡና ጅማ አባ ቡናን አስተናግዶ ጨዋታው ያለግብ ተጠናቋል ።
ስታድየሙ በደጋፊዎች ድባብ ደምቆ እና የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ማህበር ለጅማ አባ ቡና አቻው ባበረከተው የፎቶ ስጦታ እንዲሁም ጅማዎችም አፀፋውን በመለሱበት የክለቦቹን ወንድማማችነት በሚያመላክት ክንውን ነበር የጀመረው ። የጨዋታው ማጀመስርያ ፊሽካ ከመነፋቱ በፊትም ባለፈው ሳምንት ከዚህ አለም በሞት ለተለየው የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊ ቢንያም የአንድ ደቂቃ የህሊና ጸሎት ተደርጓል፡፡
የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ በእንቅስቃሴ የተቀዛቀዘ እና ከሁለቱም ቡድኖች ብዙ ሙከራዎች ያልታዩበት ነበር። ሁለት ለግብ የቀረቡ ዕድሎች አግኝተው የነበሩት አባ ቡናዎች በተለይ በመጀመሪያው አስር ደቂቃ በራሳቸው ሜዳ ላይ ተጋጣሚያቸውን ኳስ በማስጣል እና ወደፊት በመግባት ዕድሎችን ለመፍጠር ሞክረዋል ። በሁለተኛው ደቂቃ ላይም በ አህመድ ረሻድ ስህተት ግራ መስመር ላይ ያገኙትን ዕድል ኪዳኔ አሰፋ ሞክሮ ሀሪሰን ሲመልስበት ሀይደር ሸረፋ በድጋሜ ቢሞክርም የግቡ አግዳሚ አውጥቶበታል ። ከተከላካይ መስመሩ ፊት የተሰለፉት የቡድኑ ተጨዋቾች ጠንካራ የመከላከል ሽፋን ቡድኑ በቀላሉ በተለይ መሀል ለመሀል ጥቃቶችን እንዲያቋርጥ ያገዘው ቢሆንም በማጥቃቱ በኩል ግን ክሪዚስቶም ንታንቢ በግሉ ያደርጋቸው ከነበሩ ጥረቶች ውጪ እምብዛም ተጋጣሚያቸውን ማስጨነቅ አልቻሉም ። ከ2ተኛው ደቂቃ ሙከራ በሁዋላም ጅማዎች ሌላ ግልፅ የግብ ዕድል ለማግኘት 41ኛው ደቂቃ ላ የኢትዮጵያ ቡናው ኤፍሬም ወንደሰን በሰራው ስህተት ኪዳኔ አሰፋ ያገኘውን ኳስ ምክሮ ሀሪሰን እስካወጣበት ጊዜ ድረስ መታገስ ነበረባቸው ።
21ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያ የግብ ሙከራቸውን በመስዑድ መሀመድ አማካይነት ከረጅም ርቀት ያደረጉት ቡናማዎቹ ከ አራት ደቂቃዎች በኋላም አህመድ ረሻድ የአጋማሹን ጥሩ የግብ ዕድል በቀኝ መስመር በኩል አግኝቶ አምክኖታል ። ከነዚህ ሙከራዎች ሌላ በ16ኛው ደቂቃ ሳኑሚ በተከላካዮች ስህተት ያገኘውን ዕድል በመቀስ ምት ለማስቆጠር ከሞከረበት ጊዜ ውጪ ቡናዎች ለጎል መቅረብ ተስኗቸው ታይተዋል ። የተወሰደባቸውን የ ኳስ ቁጥጥር ብልጫም የመስመር አጥቂዎቻቸውን ለአማካይ መስመሩ ቀርበው እንዲጫወቱ በማድረግ ለማካካስ ቢሞክሩም 17ኛው ደቂቃ ላይ የጋቶች ፓኖም በጉዳት መውጣት መሀል ሜዳ ላይ የነበረውን ጉሽሚያ የበዛበትን የጅማዎች አጨዋወት ለመቋቋም እንዲከብዳቸው ምክንያት ሆኗል ።
በሁለተኛው አጋማሽ እስከ 60ኛው ደቂቃ የነበረው ሁኔታ ከመጀመሪያው አጋማሽ እምብዛም የተለየ አልነበረም ። በነዚህ የመጀመሪያ 15 ደቂቃዎች ኢትዮጵያ ቡናዎች በሳሙኤል ሳኑሚ እና አማኑኤል ዮሀንስ አማካይነት የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለው ነበር ። የመጨረሻዎቹ 30 ደቂቃዎች ግን ለጨዋታው ሌላ መልክ የሰጡ ነበሩ ። ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴዎች እና በርከታ ያሉ ሙከራውችም ተስተውለዋል ።
የጅማዎችን የአማካይ እና የተከላካይ መስመር ሰብሮ ለመግባት የተቸገሩት ቡናዎች እንደወትሮው የሜዳውን ስፋት ለመጠቀም የሚያደርጉት ጥረት ተዳክሞ ታይቷል ። ሰዐቱ በገፋ ቁጥርም ረጃጅም ኳሶችን ወደፊት በመላክ ባልተለመደ መልኩ ወደግብ ለመድረስ ሲሞክሩ ታይቷል ። ቡድኑ በጣም ለግብ የቀረበበት አጋጣሚም በ77ኛው ደቂቃ ላይ ከያቡን ዊልያም የተገኘ ነበር ። ከጅማዎች ሳጥን ውስጥ ያቡን አክርሮ የሞከረው ኳስ የግቡን ቋሚ ለትሞ ወጥቷል ። 62ተኛው እና 78ተኛው ደቂቃ ላይም አስቻለው ግርማ ከመስዑድ እና ከአቡበከር ኳስ ተቀብሎ ያደረጋቸው ሙከራዎች ኢላማቸውን ሳይጠብቁ ቀርተዋል።
በ59ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት ተፈራን ቀይረው ወደሜዳ ያስገቡት አባ ቡናዎች በጥሩ አደረጃጀት እና መነቃቃት ጨዋታውን ለማሸነፍ የሚረዱ ዕድሎችን መፍጠር ችለዋል ። ወደኋላ በመሳብ እና ኳስ በማስጣል የሚጀመሯቸው መልሶ ማጥቃቶች ምንም እንኳን በቁጥር በበዙ ተጨዋቾች ባይታገዙም የቡና ተጨዋቾች ወደፊት መሄዳቸውን ተከትሎ ከተከላካዮች ጀርባ የሚኖረውን ክፍተት ለመጠቀም ዕድል ሰጥቷቸው ነበር። በመልሶ ማጥቃት ከፈጠሯቸው ዕድሎች መሀከል 86ተኛው ደቂቃ ላይ ንታንቢ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ ኤኮ ፌቨር በግንባሩ ለማውጣት ሲሞክር ኳስ ወደራሱ ጎል ሄዳ ሀሪሰን እንደምንም ያዳነበት አጋጣሚ የሚጠቀስ ነው ። የፊት አጥቂው አሜ መሀመድ 82ተኛው ደቂቃ ላይ ከሱራፌል የተሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ከሀሪሰን ጋር ተገናኝቶ ይመከነው እና ዳዊት ተፈራ የሀሪሰንን ከግብ ክልል መውጣት ተመልክቶ ከረጅም ርቀት በ88 እና 89ኛው አቂቃ ላይ የሞከራቸው ኳሶች የእንግዶቹ ሌሎች ድንቅ ሙከራዎች ነበሩ ። ጅማዎች እንደመጀመሪያው 10 ደቂቃ ሁሉ በመጨረሻውም 10 ደቂቃ የተሻለ ብልጫ መውሰድ ቢችሉም ጨዋታው ግን ያለግብ ተጠናቋል ። ውጤቱን ተከትሎም ቡድኖቹ በደረጃ ሰንጠረዡ በነበሩበት አራት እና አስራሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል ።