የጨዋታ ሪፖርት | የታፈሰ ተስፋዬ የጭማሪ ደቂቃ ግብ አዳማ ከተማን ከሽንፈት ታድጋለች

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 26ኛ ሳምንት መርሃ ግብር አዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም ላይ የወራጅነት ስጋት የተደቀነበት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ያስተናገደው አዳማ ከተማ ታፈሰ ተስፋዬ በ90+1ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ማራኪ ግብ በሜዳው ዘንድሮ ለመጀመርያ ጊዜ ከመሸነፍ አድኖታል፡፡

ባለሜዳው አዳማ ባሳለፍነው ማክሰኞ ወደ አዲስ አበባ ከተማ አቅንቶ አዲስ አበባን 3-1 ከረታውን ቡድን ስብስብ ላይ ምንም ቅያሬ ሳያደርግ በተመሳሳይ የ4-3-3 ቅርፅ ወደ ጨዋታው ሲገባ በአንጻሩ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ፋሲል ከተማን 3-1 ከረታው ቡድን ስብስብ ውስጥ በጉዳት በዛሬው ጨዋታ ላይ መሰለፍ ያልቻለው ቢንያም በላይን በዮናስ ገረመው ተክተው በ4-2-3-1 ቅርፅ ጨዋታውን መጀመር ችለዋል፡፡

ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት የአዳማ ከተማ ደጋፊዎች “ከሙስና የፀዳ ትውልድ ለኢትዮጵያ እግርኳስ እድገት” የሚል ለየት ያለ ባነር በማሰራት በሜዳው የተለያዩ ክፍሎች እየተዟዟሩ በተለያየ ስታዲየሙ ክፍል ለሚገኘው ተመልካች ያሳዩበት ሂደት በሜዳው በተገኘው ተመልካች ላይ አግራሞት የፈጠረ ክስተት ሆኖ አልፏል፡፡

ለተመልካች እጅግ አሰልቺ በነበረው የመጀመርያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሁለቱም ቡድኖች ከተከላካይ እና ከግብ ጠባቂ በቀጥታ በሚጣሉ አላማ የለሽ ረጃጅም ኳሶችና እንዲሁም ቶሎ ቶሎ የሚቆራረጡ ቅብብሎች በርከት ብለው የተስተዋሉበት ነበር፡፡

እንግዎቹ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በሜዳው የላይኛው ክፍል ለብቻው ተነጥሎ የሚገኘውንና በጨዋታው በብቸኛ አጥቂነት የተሰለፈው ቢኒያም አሰፋ ጋር በተደጋጋሚ ከተከላካይ በሚነሱ ተሻጋሪ ኳሶች ለመድረስ ያደረጉት ጥረት በተደጋጋሚ በአዳማ ተከላዮች ሲከሽፍ ተስተውሏል፡፡ ከዚህም የተነሳ በሚመስል መልኩ ቢኒያም አሰፋ በአመዛኙ በመጀመሪያው አጋማሽ ብቸኛ የዘጠኝ ቁጥር አጥቂ ሊገኝበት ከሚገባው ቦታ ይልቅ በጥልቀት ወደ ኃላ በመመለስ እንዲሁም መስመር በመውጣት ኳሶችን ለማግኘት ጥረት ሲያደርግ ታይቷል፡፡

ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በ2ኛው ደቂቃ ላይ ከተከላካይ በቀጥታ የላከለትን ኳስ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ከአዳማ ተከላካዮች አምልጦ በመግባት ከአዳማ ከተማ በውሰት በውድድር አጋማሽ ንግድ ባንክን የተቀላቀለው ጥላሁን ወልዴ ከጃኮብ ፔንዜ ጋር 1ለ1 ተገናኝቶ ካመከናት ኳስ ውጪ በመጀመርያው አጋማሽ ይህ ነው የሚባል የግብ እድልን መፍጠር አልቻሉም፡፡

አዳማ ከተማዎችም በተመሳሳይ በቀጥተኛ አጨዋወት ለመጫወት ጥረት አድርገዋል፡፡ በዚህም አጨዋወት በአዳማዎች በኩል በቀኝ የመስመር አጥቂነት የተሰለፈው ሱራፌል ዳኛቸውን በመጠቀም በጨዋታው በተለይም በመጀመሪያው አጋማሽ በኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በኩል ደካማ ጎናቸው በነበረው የግራ መስመር በኩል በተደጋጋሚ አደጋ ሊፈጥሩ የሚችሉ ኳሶችን ለማሻማት ጥረት አድርገዋል፡፡ አዳማዎች ንግድ ባንኮች አግኝተው በጥላሁን ወልዴ ካልተጠቀሙበት ኳስ ጋር በሚመሳሰል መልኩ ሱሌይማን መሀመድ ከራሳቸው የግብ ክልል በቀጥታ የላከለትን ኳስ ዳዋ ሆቲሳ በግሩም ሆኒታ ተቆጣጥሮ ወደ ግብ ቢሞክርም ኢማኑኤል ፌቦ በግሩም ሆኔታ ሊያድንበት ችሏል፡፡

በንጽጽር በተሻለ መንቀሳቀስ የቻሉት ባለሜዳዎቹ አዳማ ከተማዎች በርከት ያሉ ኳሶችን ከቆመ ኳስ እንዲሁም ከሳጥን ውጪ በቀጥታ በመምታት ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም ኢማኑኤል ፌቮ ግን የሚቀመስ አልሆነም፡፡ በተለይም በ33ኛው ደቂቃ ላይ የሮቤል ግርማን ስህተት ተከትሎ የተገኘችውን ኳስ ሱራፌል ዳኛቸው ከቀኝ መስመር ሰብሮ በመግባት ወደ መሀል ያቀበለውን ኳስ በንግድ ባንክ የግብ ክልል ጠርዝ ላይ በጥሩ አቋቋም የነበረው ቡልቻ ሹራ ከኳሷ ጋር በአግባቡ መገናኘት ባለመቻሉ ሳይጠቀምባት የቀረችው ኳስ የምታስቆጭ አጋጣሚ ነበረች፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያዋ ግብ እስክትቆጠር ድረስ በመጀመሪያው አጋማሽ በነበረበት ሂደት ሊቀጥል ችሏል፡፡ ነገርግን በ55ኛው ደቂቃ ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በመልሶ ማጥቃት ያገኙትን አጋጣሚ ጥላሁን ወልዴ ወደ መሀል ሲያሻማ ዮናስ ገረመው ተቆጣጥሮ ከግብ ክልል ውጪ ለነበረው ጋብሬል አህመድ አቀብሎት ናይጄርያዊው አማካይ በግሩም ሆኔታ መሬት ለመሬት አክርሮ በመምታት የመጀመሪያዋን ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡

ከዚህች ግብ መቆጠር በኃላ ላለመውረድ እየተፍጨረጨሩ የሚገኙት ንግድ ባንኮች ሶስት ነጥቧን ይዘው ለመውጣት በጥልቀት ወደ ኃላ ተስበው ለመከላከል ጥረት አድርገዋል፡፡ የአዳማ ከተማው አሰልጣኝ ተገኔ ነጋሽ በአንጻሩ አማካዮችን በመቀነስ ታፈሰ ተስፋዬንና ሚካኤል ጆርጅን ቀይረው በማስገባት እንዲሁም ጨዋታውን በመሀል ተከላካይነት የጀመረው ሙጂብ ቃሲምን ወደ አጥቂነት በማምጣት ከዳዋ ሁቴሳ ጋር በማጣመር በ4 አጥቂ ለመጫወት ጥረት አድርገዋል፡፡ የአዳማ ከተማ ተጫዋቾች ተቀይረው ከሜዳ  በሚወጡበት ወቅትም ከደጋፊዎች እጅግ ከፍተኛ የሆነ ተቃውሞ ሲሰነዘርባቸው ተስተውሏል፡፡

የአሰልጣኝ ተገኔ ለውጦች ግን የሚፈለገውን ውጤታማነት ማስገኘት አልቻለም፡፡ በበርካታ አጋጣሚዎች እነዚህ አራት አጥቂዎች ኳስ ወደፊት በሚላክበት ቅጽበት በተመሳሳይ ስፍራ ላይ ስለሚሆኑ ኳሶችን በአግባቡ መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡

አዳማዎች የአቻነቷን ግብ ለማግኘት በሚያደርጉት ወቅት ፊት ላይ የሚገኙት አጥቂዎችና ከኃላቸው የነበሩት ሁለት የአጥቂ አማካዮች ተቆርጠው በሚቀሩበት አጋጣሚ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በበርካታ አጋጣሚ በመልሶ ማጥቃት ኳሶችን ቢያገኙም መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡

77ኛው ደቂቃ ላይ በግምት ከ25 ሜትር ርቀት ያገኙትን የቅጣት ምት ዳዋ ሆቴሳ በጥሩ ሁኔታ ቢሞክርም በጨዋታው ድንቅ የነበረው ኢማኑኤል ፌቮና የግቡ አግዳሚ ተጋግዘው ያዳኑት ኳስ ምናልባትም አዳማን ወደ ጨዋታው ልትመልስ የምትችል ነበረች፡፡

በቀሩት የጨዋታው ደቂቃዎች በተለይም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመሀል ተከላካይ የነበሩት አቤል አበበና ቢኒያም ሲራጅ ከፊት ለሚገኙት አራቱ የአዳማ አጥቂዎች በቀጥታ ከተከላካይ በሚሻማ ኳስ ለመድረስ የሚያደርጉትን ጥረት በማጨናገፍ በኩል የተዋጣላቸው ነበሩ፡፡

ጨዋታው በንግድ ባንኮች የበላይነት ተጠናቀቀ ተብሎ በሚጠበቅበት ሰአት የጨዋታው የመደበኛ ሰአት ተጠናቆ የእለቱ የመሀል ዳኛ በሰጡት ተጨማሪ 5 ደቂቃዎች ላይ በ90+1ኛው ደቂቃ ከመስመር የተሻገረውን ኳስ ቁመተ መለሎው ሚካኤል ጆርጅ በግንባሩ ሸረፍ አድርጎ አቀብሎት ታፈሰ ተስፋዬ ከግብ ክልሉ ጠርዝ ላይ በማራኪ ሆኔታ መትቶ ግሩም የሆነች ግብ በማስቆጠር ቡድኑን ከሽንፈት ሲታደግ የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ደግሞ ላለመውረድ በሚያደርጉት ጥረት በእጃቸው ገብቶ የነበረውን ወሳኝ ሶስት ነጥብ አሳጥቷል፡፡

ውጤቱን ተከትሎ ለዋንጫ በመፎካከር ላይ የሚገኙት አዳማ ከተማዎች በ43 ነጥብ አሁንም በ5ኛ ደረጃ ላይ ሲገኙ በአንጻሩ በወራጅ ቀጠና ወስጥ እየዳከሩ የሚገኙት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በ24 ነጥብ አሁንም በ15ኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ ተገደዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *