የጨዋታ ሪፖርት | ወላይታ ድቻ ደረጃውን ያሻሻለበትን ወሳኝ ድል ኤሌክትሪክ ላይ አስመዝግቧል

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 26ኛ ሳምንት ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኝ የነበረው ወላይታ ድቻ ለቀጠናው እጅግ ቀርቦ የሚገኘው ኢትዮ ኤሌክትሪክን አስተናግዶ 1-0 በማሸነፍ ላለመውረድ በሚያደርገው ፉክክር ላይ ወሳኝ የሆነ 3 ነጥብ መሰብሰብ ችሏል፡፡

ከጨዋታው መጀመር በፊት የወላይታ ዞን አስተዳዳሪ ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ በስታድየሙ በመዞር የታደሙትን ተመልካቾች ሲያበረታቱ እና ለድጋፍ ሲያነሳሱ ተስተውሏል፡፡

በመጠነኛ ዝናብ ታጅቦ በተጀመረው ጨዋታ የመጀመሪያዎቹን 15 ደቂቃዎች ወላይታ ድቻዎች በፈጣን እንቅስቃሴ በእንግዳው ላይ የበላይ መሆን ችለው ነበር፡፡ በተለይም ዳግም በቀለ ከግብ ጠባቂው ሱሌይማን አቡ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ያመከናቸው ሁለት ያለቀላቸው እድሎች የወላይታ ድቻን እንቅስቃሴ የሚያሳዩ ነበሩ፡፡

ጨዋታው እየተጋመሰ ሲመጣ ኤሌክችሪኮች የድቻን ፈጣን እንቅስቃሴ በመግታት ወደ ጨዋታው ሪትም መግባት የቻሉ ሲሆን የተመጣጠነ ፉክክር ማሳየትም ችለዋል፡፡ በተለይም አማካዩ በኃይሉ ተሻገር ድንቅ እንቅስቃሴ ማድረግ የቻለ ሲሆን በመጀመርያው አጋማሽ ኤሌክትሪክ ላደረገው ብቸኛ ሙከራም ምክንያት ነበር፡፡

በ36ኛው ደቂቃ በዛብህ መለዮ ከቀኝ መስመር ወደ አደጋ ክልሉ ያሻገራትን ኳስ የኤሌክትሪክ ተከላካዮችን ትኩረት ማጣት ተጠቅሞ አናጋው ባደግ ወደ ግብነት በመቀየር ወላይታ ድቻን መሪ አድርጎ የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የእንቅስቃሴ የበላይነቱን መውሰድ የቻሉት ኤሌክትሪኮች ነበሩ፡፡ በተለይም በዳዊት እስጢፋኖስ ፣ በሀይሉ ተሻገር እና ኢብራሂም ፎፎናን ቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ተክሉ ተስፋዬ ኤሌክትሪኮች አቻ የሚሆኑበትን አጋጣሚዎች ሳይጠቀሙባቸው ቀርተዋል፡፡

ወላይታ ድቻዎች በአንጻሩ በጥልቀት በመከላከል እና መልሶ ማጥቃት ውጤታቸውን አስጠብቀው ለመውጣት ያደረጉት ጥረት ተሳክቶ አሸንፈው መውጣት ችለዋል፡፡ ድሉን ተከትሎም ሁለት ደረጃዎችን በማሻሻል በ29 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችለዋል፡፡

ከጨዋታው በኃላ አሰልጣኝ መሣይ ተፈሪ በሰጡት አስተያየት የመረጡት የጨዋታ ዘይቤ ለድላቸው አስተዋፅኦ እንዳበረከተ ገልጸው ወላይታ ድቻ ወደ ከፍተኛ ሊጉ እንደማይወርድ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮ ኤሌክትሪኩ አሰልጣኝ ብርሀኑ ባዩ በበኩላቸው የሜዳው ለእንቅስቃሴ አመቺ አለመሆን እክል እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *