የጨዋታ ሪፖርት | ሲዳማ ቡና ከመመራት ተነስቶ አአ ከተማን አሸንፏል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 26ኛ ሳምንት ዛሬ 5 ጨዋታዎች ሲጀመር በቻምፒዮንነት ፉክክር ውስጥ የሚገኘው ሲዳማ ቡና ይርጋለም ላይ የሊጉ ግርጌ ላይ የሚገኘው አዲስ አበባ ከተማን 1-0 ከመመራት ተነስቶ 3-1 በማሸነፍ ደረጃውን ወደ 2ኛ ከፍ ማድረግ ችሏል፡፡

በጨዋታው የመጀመሪያ 20 ደቂቃዎች እንግዶቹ አዲስ አበባ ከተማዎች የእንቅስቃሴ የበላይነት መውሰድ ቢችሉም የግብ እድሎቸን በመፍጠር ረገድ የተሻሉ የነበሩት ሲዳማ ቡናዎች ነበሩ፡፡ በተለይ በሁለተኛው ዙር በበርካታ ጨዋታዎች የመሰለፍ እድሎችን ያገኘው ናይጄሪያዊው ላኪ ሳኒ የአዲስ አበባ ከተማ ተከላካዮችን በማስጨነቅ ረገድ የተሻለ መንቀሳቀስ ችሏል፡፡

በ18ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር የተሻማውን ኳስ በደረቱ በማብረድ አጥቂው ኃይሌ እሸቱ የዋና ከተማውን ክለብ ቀዳሚ አድርጓል፡፡ አአ ከተማ ከሜዳው ውጪ ካስቆጠራቸው ጎሎች አመዛኙን ላስቆጠረው ኃይሌ በውድድር ዘመኑ 7ኛ ግብ ሆናም ተመዝግባለች፡፡

የአአ የመሪነት ጎል መዝለቅ የቻለው ለ10 ደቂቃዎች ብቻ ነበር፡፡ ሲዳማዎች አቻ ለመሆን በፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ የግብ እድል ለመፍጠር ያደረጉት ጥረት ፍሬ አፍርቶ  በ28ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር ወሰኑ ማዜ ያሻገረውን ኳስ በጨዋታው ጥሩ የተንቀሳቀሰው ላኪ ሳኒ ወደ ግብነት ቀይሮ ሲዳማ ቡናን አቻ አድርጓል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ሲዳማ ቡና የጨዋታ ብልጫ መውሰድ ችሏል፡፡ የሁለተኛው አጋማሽ ከተጀመረ ብዙም ሳይገፋም አዲስ ግደይ ከማዕዘን ምት ያሻማውን ኳስ ላኪ ሳኒ ወደ ግብነት ቀይሮ ሲዳማ ቡናን መሪ አድርጓል፡፡

በ52ኛው ደቂቃ ኢንተርናሽናል አርቢትር ብሩክ የማነብርሀን የአዲስ አበባ ከተማው ተከላካይ ዳንኤል አባተ ተንሸራቶ ኳስ በእጁ በመንካቱ በሁለተኛ ቢጫ ከሜዳ መውጣት አዲስ አበባ በጨዋታው ይበልጥ እንዲቸገር አድርጎታል፡፡

በ56ኛው ደቂቃ አዲስ ግደይ በግል ጥረቱ እየገፋ ወደ ውስጥ በመግባት የግብ ጠባቂው ደረጄ አለሙን መውጣት ተመልክቶ በመምታት የሲዳማን መሪነት ወደ ሁለት ግብ ልዩነት ያሰፋበትን ጎል አስቆጥሯል፡፡ ይህ ግብ ለፈጣኑ የመስመር አጥቂ በውድድር ዘመኑ 7ኛ ግብ ነች፡፡

ከጎሉ መቆጠር በኋላ ባሉት ደቂቃዎች ሲዳማ ቡና ጫና ፈጥሮ ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር የሚችልባቸውን እድሎች መፍጠር ቢችልም ሳይጠቀምባቸው ቀርቶ ጨዋታው በይርጋለሙ ቡድን 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ሲዳማ ቡናም በውድድር ዘመኑ በሜዳው ያለመሸነፍ ክብሩን አስጠብቆ ወጥቷል፡፡

ከጨዋታው በኃላ አሰልጣኝ አለማየሁ አባይነህ በሰጡት አስተያየት በርካታ የግብ እድሎች ቢያመክኑም በቡድናቸው እንቅስቃሴ ደስተኛ እንደሆኑ ሲገልጹ የአአ ከተማ አቻቸው አስራት አባተ በበኩላቸው በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ ለማሳየት ቢሞክሩም ያለልተገቡ የዳኝነት ውሳኔዎች እክል እንደፈጠረባቸው ገልፀዋል፡፡ በሊጉ የመቆየት እድላቸው እንዳልተሟጠጠም አያይዘው ተናግረዋል፡፡

Leave a Reply