የጨዋታ ሪፖርት | መከላከያ ከ ደደቢት ነጥብ ተጋርተዋል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 26ኛ ሳምንት ዛሬ በተደረጉ 5 ጨዋታዎች ሲጀመሩ በአአ ስታድየም መከላከያ ከ ደደቢት ያደረጉት የእለቱ የመጨረሻ መርሀ ግብር ያለ ግብ ተጠናቋል፡፡

በመጠነኛ ዝናብ እና ዝቅተኛ የተመልካች ቁጥር በተካሄደው ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ 4-1-3-2 አሰላለፍ ወደ ሜዳ የገቡ ሲሆን ጨዋታው ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ እና የግብ ሙከራዎች ተስተናግደውበታል፡፡

ቀዝቀዝ ብሎ በጀመረው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመርያ 25 ደቂቃ እንቅስቃሴ ተመጣጣኝ የነበረ ሲሆን በመስመር በኩል የሚደረጉ ያለልተሳኩ የማጥቃት እንቅስቃሴዎች እና ከቆሙ ኳሶች የሚደረጉ ሙከራዎች ታይተዋል፡፡ በ6ኛው ደቂቃ ከማዕዘን የተሻማው ኳስ በደደቢት ተከላካዮች ሲመለስ አዲሱ ተስፋዬ በግንባሩ ያመከነው ኳስም በእነዚህ ደቂቃዎች ውስጥ የተደረገ ብቸኛው ሙከራ ነበር፡፡

የመጀመርያው አጋማሽ እየተጋመሰ ሲመጣ የተሻለ እና ፈጣን እንቅስቃሴ የታየ ሲሆን በርከት ያለሉ ሙከራዎችም ተስተናግደዋል፡፡ በ25ኛው ደቂቃ ስዩም በግሩም የማጥቃት እንቅስቃሴ አንድ ሁለት ተቀባብሎ ያሻገረውን ኳስ በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው ጌታነህ ኳሷን ሳይደርስባት ቀርቶ ወደ ውጪ ስትወጣ በመልሰ ምት ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ያደረጉት መከላከያዎች በማራኪ ወርቁ አማካኝነት ሞክረው ታሪክ ጌትነት አድኖታል፡፡

በ31ኛው ደቂቃ ሰለሞን ሐብቴ ከርቀት ሞክሮ ወደ ውጪ የወጣቀት ፣ በ34ኛው ደቂቃ ዳዊት ሳጥን ውስጥ የመታውን ኳስ አቤል በድንቅ ብቃት ያመከነበት ፣ በ36ኛው ደቂቃ ሳሙኤል ሳሊሶ ከርቀት ሞክሮ ታሪክ እንደምንም ያወጣበት እና በ45ኛው ደቂቃ ሚካኤል ደስታ ከቅጣት ምት ሞክሮ የወጣበት ሙከራዎች በሁለቱም በኩል በመጀመርያው አጋማሽ የሚጠቀሱ የግብ እድሎች ነበሩ፡፡

የሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ እንደመጀመርያው ሁሉ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የታየበት እና የመከላከያ የግብ ሙከራ የበላይነት የተስተዋለበት አጋማሽ ነበር፡፡

በ52ኛው ደቂቃ ምንይሉ ወንድሙ የመታው ቅጣት ምት ወደ ውጪ ሲወጣበት በ64ኛው ደቂቃ ጌታነህ ከበደ ከቀኝ መስመር ወደ ግብ የመታው ኳስ በተመሳሳይ ወደ ውጪ ወጥቶበታል፡፡ ከ1 ደቂቃ በኋላ በኃይሉ ግርማ ያሻገረው ኳስ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ማራኪ ወርቁ እና ግብ ጠባቂው ታሪክን ቢያገናኝም የመታው ኳስ በግቡ አናት ወደ ውጪ ወጥቶበታል፡፡ በ66ኛው ደቂቃ ደግሞ የደደቢቱ ሰለሞን ሐብቴ ከማዕዘን ምት አንድ ሁለት ተቀባብሎ ወደ ሳጥኑ ጠርዝ በመጠጋት የመታው ኳስ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷል፡፡

ጨዋታው እንዲህ ባለ መልኩ ቀጥሎ 82ኛው ደቂቃ ላይ የደደቢቱ አጥቂ ዳዊት ፍቃዱ በሰራው ጥፋት የማስጠንቀቂያ ካርድ ሲሰጠው ያልተገባ ተቃውሞ በማሳየቱ በ2ኛ ቢጫ ከሜዳ ተወግዶ ሰማያዊዎቹ ቀሪዎቹን ደቂቃዎች በ10 ተጫዋቾች ለመጨረስ ተገደዋል፡፡ ሆኖም መከላከያዎች የቁጥር የበላይነቱን ለመጠቀም ያደረጉት ጥረት እምብዛም ነበር፡፡ ተቀይሮ የገባው አማካዩ ቴዎድሮስ ታፈሰ በግሉ ከሚያደርገው እንቅስቃሴ እና ከርቀት ከሚያደርጋቸው ኢላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች ውጪም ጫና ፈጥረው መንቀሳቀስ ሳይችሉ ጨዋታው ያለግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡

በሁለቱ ቡድኖች ግንኙነት ለ3ኛ ተከታታይ ጊዜ ጨዋታው ያለ ግብ ሲጠናቀቅ በዋንጫ ፉክክሩ ላይ የሚገኘው ደደቢት ነጥብ መጣሉን ተከትሎ በመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ጫና የሚያሳድርበትን እድል ሳይጠበቀምበት ቀርቷል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *