ወልድያ ከወራጅ ቀጠናው የራቀበትን ድል ከሜዳው ውጪ አስመዝግቧል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 26ኛ ሳምንት ዛሬም ቀጥሎ ሲውል ወልድያ ከሜዳው ውጪ ወሳኝ ሶስት ነጥብ አስመዝግቧል፡፡

ድሬዳዋ ላይ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አንድ ጨዋታ በዝግ ስታድየም እንዲጫወት የተወሰነበት ድሬዳዋ ከተማ ወልድያ ከተማን በዝግ ስታድየም አስተናግዶ 2-0 ተሸንፏል፡፡ ጨዋታው ያለ ተመልካች መካሄዱን ተከትሎም የድሬዳዋ ከተማ ደጋፊዎች በጎሉ ጀርባ በሚገኝ ተራራ ላይ ጨዋታውን ለመከታተል ሲሞክሩ ታይተዋል፡፡

በመጀመርያዎቹ 15 ደቂቃዎች ባለሜዳዎቹ የእንቅስቃሴ የበላይነት እና አስደንጋጭ ሙከራዎች ማድረግ የቻሉ ቢሆንም በ14ኛው ደቂቃ ወደ ግብ ክልሉ የመጣውን ኳስ ግብ ጠባቂው ኤሚክሪል ቤሊንጌ ተቆጣጥሮ በረጅሙ ሲለጋው አንዱአለም ንጉሴ ጨርፎት በጥሩ አቋቋም ላይ ያልነበረው ወርቅነህ ዲባባ መረብ ላይ አሳርፎታል፡፡

ከመሪነቱ ጎል በኋላ ወልድያ መሪነቱን ለማስፋት የፈጀበት አንድ ደቂቃ ብቻ ነበር፡፡ በ16ኛው ደቂቃ አንዱአለም ንጉሴ የወልድያን መሪነት አስተማማኝ ያደረገበትን ጎል ሲያስቆጥር በውድድር ዘመኑ ያስቆጠራቸውን ግቦች መጠንም 9 አድርሷል፡፡

ከጎሎቹ መቆጠር በኋላ ወልድያዎች በሚታወቁበት ጥብቅ መከላከል ውጤቱን አስጠብቀው መውጣት ሲችሉ ድሬዳዋ ከተማ በጊዜ የተቆጠሩባቸው ጎሎችን ለመቀልበስ ያደረጉት የማጥቃት እንቅስቃሴ ያልተደራጀ እና በቀላሉ በወልድያ ቁጥጥር ስር የገባ ነበር፡፡

ድሉን ተከትሎ ለወራጅ ቀጠናው ተጠግቶ የነበረው ወልድያ  ነጥቡን 33 በማድረስ ከወራጅ ቀጠናው በ5 ነጥቦች በመራቅ ከገባበት ስጋት መጠነኛ እፎይታ ሲያገኝ በተከታታይ 3 ጨዋታዎች የተሸነፈው ድሬዳዋ ከተማ በአንጻሩ 28 ነጥቦች ላይ ረግቶ በወራጅ ቀጠናው ውስጥ ተቀምጧል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *