ፋሲል ከተማ በአዲስ አሰልጣኝ እየተመራ ወደ ድል ተመልሷል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 26ኛ ሳምንት ጎንደር ፋሲለደስ ስታድየም ላይ አርባምንጭ ከተማን ያስተናገደው ፋሲል ከተማ በአዲስ አሰልጣኝ እየተመራ የመጀመርያውን ድል ማስመዝገብ ችሏል፡፡

የፋሲል ከተማ የበላይነት በታየበት የመጀመርያው አጋማሽ አፄዎቹ ግብ ማስቆጠር የቻሉት ገና ጨዋታው እንደተጀመረ ነበሮ፡፡ በ1ኛው ደቂቃ ሙሉቀን አቡሃይ ያቀበለውን ኳስ ኤፍሬም አለሙ ተቆጣጥሮ ለአቤል ያለው ያሻገረውን ኳስ ወጣቱ አጥቂ ወደ ግብነት ለውጦ ፋሲልን ቀዳሚ አድርጓል፡፡ ከደደቢት በግማሽ የውድድር ዘመን ወደ ፋሲል ከተማ ያመራው አቤል በቀይ እና ነጩ ማልያ የመጀመርያ ጎሉን ማስቆጠር ችሏል፡፡

ከጎሉ መቆጠር በኋላም ፋሲሎች ተደጋጋሚ ሙከራዎች ያደረጉ ሲሆን በአቤል ያለው ፣ ናትናኤል ጋንጂላ እና ኤፍሬም አለሙ አማካኝነት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል፡፡

በ24ኛው ደቂቃ የመጀመርያውን ጎል ያስቆጠረው አቤል ያለው ያሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ኤፍሬም አለሙ የፋሲል ከተማን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል፡፡

ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ በታየበት የሁለተኛው አጋማሽ አርባምንጮች ተሻሽለው የቀረቡ ሲሆን በጎል ሙከራዎች ረገድም የተሻሉ ነበሩ፡፡ ሆኖም ተጨማሪ ግብ ሳይስተናገድ ጨዋታው በፋሲል ከተማ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ከአሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ ጋር የተለያየው ፋሲል ከተማ በምንተስኖት ጌጡ እየተመራ የመጀመርያ ጨዋታዎን በድል ሲወጣ ከወትሮው በቁጥር ቀንሶ በስታድየም የታደመው ተመልካችም በክለቡ እንቅስቃሴ ተደስቶ ወጥቷል፡፡

ውጤቱን ተከትሎ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ፋሲል ከተማ በ38 ነጥቦች 6ኛ ደረጃ ላይ ሲደላደል በሁለተኛው ዙር የውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኘው አርባምንጭ ከተማ በ31 ነጥቦች ከወራጅ ቀጠናው በ4 ነጥቦች ብቻ ለመራቅ ተገዷል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *