ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ – ጅማ ከተማ ሲሸነፍ ሀላባ እና ሻሸመኔ ወሳኝ ድል አስመዝግበዋል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 21ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሰኞ እና ዛሬ በክልል ከተሞች እና አአ ስታድየም ተደርገው መሪው ጅማ ከተማ ሲሸነፍ ተከታዮቹ ድል አስመዝግበው ልዩነታቸውን ማጥበብ ችለዋል፡፡

በደረጃ ሰንጠረዡ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሀላባ ከተማ ድሬዳዋ ፖሊስን አስተናግዶ 2-1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ከመሪው ጅማ ከተማ ጋር ነጥቡን አስተካክሏል፡፡   በ38 ደቂቃ ከጌታሁን ሽመልስ የተሻማውን ኳስ ስንታየው መንግስቱ በግንባሩ በመግጨት ሀላባን ቀዳሚ ሲያደርግ በ56ኛው ደቂቃ ደምሴ አያዛ ያገኘውን ቅጣት ምት ወደ ጎልነት በመለወጥ የሀላባን መሪነት ወደ ሁለት አስፍቷል፡፡ የድሬዳዋ ፖሊስን ብቸኛ ጎል ያስቆጠረው የቀድሞው የድሬዳዋ ከተማ ተጫዋች ዘርዓይ ገብረ ስላሴ ነው፡፡

በዚሁ ምድብ ተጠባቂ የነበረው ጨዋታ ሀድያ ሆሳዕናን ከወልቂጤ ከተማ ያገናኘው መርሃ ግብር ነበር፡፡ በቅርቡ በፌደሬሽኑ የ6 ነጥብ ቅነሳ ቅጣት የተላለፈበት ሀድያ ሆስዕና ይህን ጨዋታ በአሸናፊነት አጠናቋል፡፡ ለሀድያ ሆሳዕና ቢንያም ታዬ በ45ኛው ደቂቃ ብቸኛዋን የማሸነፍያ ጎል ማስቆጠር ችሏል፡፡

ዲላ ላይ ዲላ ከተማ ናሽናል ሲሜንትን አስተናግዶ 2-1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ወደ ደረጃ ሰንጠረዡ አናት መገስገሱን ቀጥሏል፡፡ ለዲላ ከተማ በ2ኛው ደቂቃ ኩምሴ ሞጨራ እና በ76ኛው ደቂቃ ሀብታሙ ፍቃዱ ሲያስቆጥሩ ናሽናል ሴሜንትን ከሽንፈት ያላደነች ጎል ዳንኤል በ90ኛው ደቂቃ አስቆጥሯል፡፡

ጅንካ ላይ ጅንካ ከተማ ነገሌ ቦረናን አስተናግዶ 2-1 ሲያሸንፍ ካፋ ቡና ስልጤ ወራቤን 2-1 በሆነ ተመሳሳይ ውጤት አሸንፏል፡፡ ነቀምት ላይ ነቀምት ከተማ ከ አርሲ ነገሌ ያደረጉት ጨዋታ ደግሞ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡

ትላንት ኦሜድላ ሜዳ ሊካሄድ የነበረውና በጣለው ዝናብ ምክንያት ሜዳው በመበላሸቱ ወደ ዛሬ የተላለፈው የፌዴራል ፖሊስ እና ጅማ ከተማ ጨዋታ 03:00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ተካሂዶ ፌዴራል ፖሊስ 2-1 በሆነ ውጤት አሸንፏል፡፡ ፌዴራል ፖሊስ ሊቀ አልታየ ባስቆጠረው የፍፁም ቅጣት ምት ጎል ቀዳሚ ሲሆን አስራት ቱንጆ በመጀመርያው አጋማሽ ማብቂያ ለጅማ አስቆጥሮ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡ ከእረፍት መልስ ሊቁ አልታየ ለራሱ ሁለተኛውን ፌዴራል ፖሊስንም ወደ ድል የመራች ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በፌዴራል ፖሊስ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

በተመሳሳይ ሻሸመኔ ላይ በዝናብ ምክንያት ያልተካሄደው የሻሸመኔ ከተማ እና ደቡብ ፖሊስ ጨዋታ ዛሬ 04:00 ላይ ተካሂዶ ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ሴኮንዶች ሲቀሩት አብዱላዚዝ ኡመር ባስቆጠረው ግብ ሻሸመኔ ከተማ 1-0 በማሸነፍ ደረጃውን ወደ 3ኛ ከፍ አድርጓል፡፡

5 Comments

  1. Halaba is gonna be on the bottom am sure other wishers you just be cool down lol

  2. የሀዲያ ሆሳዕና 6 ነጥብ መልስሉልን እንጂ ! አምሀ ተስፋዬ ስለ ውሳኔ።

  3. ሀድያ ሆሳዕና ጨዋታዉን ያደረገው በዝግ ስታዲዮም አይደለም !!! who is the source of this information ?????

  4. ስለ ሻሸመኔ ብዙም አላወራኅም አምኃ፡፡ ክለቡ ፕሪምየርሊጉን የመቀላቀል ሰፊ እድል አለው..ደጋፊውም ያለስስት ድጋፉን ሰቷል

Leave a Reply