” የውጪ ግብ ጠባቂዎች መኖር ጥንካሬን ይሰጠኛል ፤ ሆኖም መብዛታቸው ለሀገሪቱ እግርኳስ አሳሳቢ ነው” አቤል ማሞ

የመከላከያው ግብ ጠባቂ አቤል ማሞ በክለቡ የመጀመርያ የውድድር ዘመኑ መልካም ጊዜያት እያሳለፈ ይገኛል፡፡

በ2008 መጨረሻ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጋር በዝግጅት ላይ በደረሰበት ጉዳት ለወራት ከሜዳ የራቀው አቤል ከታሰበው ጊዜ ቀደም ብሎ በማገገም ወደ ሜዳ ተመልሶ ድንቅ ብቃቱን እያሳየ የሚገኝ ሲሆን ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረገው ቆይታ በጉዳት ያሳለፈው ጊዜ አስቸጋሪ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ” አስቸጋሪ ጊዜ ነበር ። በመጀመርያ ጉዳቱን ከባድ ያደረገው የሙገርን ውል ጨርሼ ወደ መከላከያ የምገባበት ወቅት ነበር። ከዚህ በተጨማሪ ብሄራዊ ቡድኑን ከመጥቀም አንፃር ይህን ባለማሳካቴ ወቅቱ ለእኔ አስቸጋሪ ነበር። ሆኖም በርካታ ሰዎች ከጎኔ በመሆናቸው ቶሎ አገግሜ የራሴንም ጥንካሬ ጨምሬ ወደ ሜዳ ልመለስ ችያለው። ”

በ2008 የውድድር ዘመን አቤል የብሄራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ የነበረ ቢሆንም አመቱን ያሳለፈው በከፍተኛ ሊግ ይወዳደር በነበረው ሙገር ሲሚንቶ ነበር፡፡ በሁለት የውድድር ዘመናት ሁለቱ ሊጎች ላይ ያሳለፈው አቤል ፕሪምየር ሊጉ እና ከፍተኛ ሊጉን እንዲህ ያነፃፅራል፡፡

” ከፍተኛ ሊግ መጫወትን ስትገልፀው ሁሉም ጨዋታ ጠንካራ ነው። ይሄ ጨዋታ ቀላል ነው የምትለው የለም። በየደቂቃው በሁሉም አቅጣጫ ኳስ ቶሎ ቶሎ ወደ ጎል የሚመጣበት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የሚሰሩ ጥፋቶች ይበዙበታል። በአጭሩ በአቅም ደረጃ እራስህን የምታይበት ሊግ ነው። ወደ ፕሪሚየር ሊግ ስትመጣ ደግሞ የብዙ ቡድኖች አጨዋወት ተመሳሳይ እንደመሆኑ መጠን በጣም የሚያስቸግር ባይሆንም ከፍተኛ ሊጉ ላይ ያለው ፈታኝነት አይደለም ያለው። ሆኖም ደረጃ እየጨመረ በመጣ ቁጥር የአእምሮ አቅምህም የሚለካበት ቦታ ነው ፕሪሚየር ሊጉ፡፡”

በኢትዮጵያ በፕሪምየር ሊግ ከሚካፈሉ 16 ቡድኖች ግማሹ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በመጡ ግብ ጠባቂዎች ይጠቀማሉ፡፡ ይህ ልማድ የብሄራዊ ቡድኑን አማራጭ የሚገድብ ቢሆንም የራሱ የሆኑ ጠንካራ ጎኖች እንዳሉት አቤል ያምናል፡፡  ” በእርግጥ ያሳስበኛል፡፡ ነገር ግን ጥንካሬ የሚሆነኝ አንድ እሱ ነው። በእነሱ ላይ እምነት መጣሉ እኛ ምንድን ነን? ምን እያደረግን ነው? የት ነው ያለሁት? ብለህ ራስህን እንድትጠይቅ ያደርግሀል፡፡ ይህም ” ከእነሱስ በምንም መንገድ የማንሰው ነገር የለም” ብለህ እንድትሰራ ያነሳሳሀል። ክለቦቻችን ከሌሎች የተሻለ አድቫንቴጅ ለመያዝ ነው ዜጎች እየበዙ ያሉት። ይህ ለሊጋችን ጥሩ ነገር ነው። ነገር ግን የሀገሪቱ ትልቁ ሊግ ላይ ከግማሽ በላይ የውጭ ግብ ጠባቂዎች ሲሆኑ ወደ ፊት አደጋ አለው። ምክንያቱም እግርኳሳችን ትልቅ ደረጃ መድረስ አለበት ሲባል ከግብ ጠባቂ እስከ አጥቂ ብቻ ሳይሆን ብዙ ነገር ላይ ነው ትኩረት የምታደርገው፡፡ ከዛ አንፃር የግብ ጠባቂዎች ሁኔታ አሳሳቢ ነው። አንድ የውጭ ግብ ጠባቂ በአንድ ክለብ ውስጥ ሲኖር ሁለት ኢትዮዽያውያን ግብ ጠባቂዎች አሉ፡፡ አቅም ቢኖራቸውም ቦታው ይያዝባቸዋል፡፡ ስለዚህ ከእነ አቅማቸው ቁጭ ብለዋል ፤ ይህ ደግሞ በጣም ከባድ ነው። ” ሲል አቤል የውጪ ግብ ጠባቂዎችን መብዛት ጥቅም እና ጉዳት ይገልጻል፡፡

በዘንድሮው የውድድር ዘመን ከአቤል የተሻለ ብቃታቸውን ያሳዩ ግብ ጠባቂዎች ጥቂት ናቸው፡፡ እነደ እሱ ብቃት ባይሆን የመከላከያ የዘንድሮ ውጤታማነት ጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚያስገቡም በርካቶች ናቸው፡፡ ከመከላከያ ወጥ አቋም የማሳየት ችግር ጀርባ አቤል እንዴት ወጥ አቋሙን ሊያሳይ ቻለ? አቤል ምክንያቱን ይገልጻል፡፡

” ከጉዳት እንደ መመለሴ የመጀመርያ እቅዴ የነበረው ቦታውን ማግኝት ነበር። ቦታውን ለማግኘት ደግሞ የሚጠበቁብኝ ነገሮች ነበሩ ፤ እነሱን ተወጥቼ ቦታውን በመያዝ ረገድ ተሳክቶልኛል። ነገር ግን ለወቅታዊ አቋሜ ጥሩ መሆን እኔ የምለው በፕሪሚየር ሊጉ ከእኔ ጋር የሚጫወቱ 15 ግብ ጠባቂዎች አሉ፡፡ ሁሌም ከእነሱ ለመሻል ነው ወደ ሜዳ የምገባው እንጂ እኔ ቡድን ያለውን በረኛ ለማስቀመጥ አይደለም። ሁሌም ከእነዛ ግብ ጠባቂዎች የተሻለ ሆኜ ለመገኘት እና ቡድኔ ጎል እንዳይቆጠርበት ለማድረግ ጠንክሬ በመስራቴ ነው ይህ ወቅታዊ አቋም የመጣው።”

አቤል በመጨረሻም በቅርቡ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጉዞውን ከሚጀምረው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጋር ብዙ ርቀት የመጓዝ ህልሙን ገልጿል፡፡ ” ይሄ የብዙ ተጨዋቾች እቅድ ነው። አንደኛ የሚገባውን ነገር እንዲያገኝ እፈልጋለው። የኢትዮዽያውያን ከረጅም ጊዜ በኃላ የተደሰቱበትን የአፍሪካ ዋንጫ መግባት እና ተጨዋቾቹ ያሳኩትን ስኬት እኔም በውስጡ ሆኜ ማሳካት እፈልጋለው ፤  ሀገሬን ዳግመኛ ወደ አፍሪካ ዋንጫው መመለስን! “

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *