ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሲዳማ ቡና 4 እና 5ኛ ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ 10ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬም መካሄዳቸውን ቀጥለው ከ1-5ኛ የሚጨርሱት ቡድኖች ታውቀዋል፡፡

ምድብ ሀ

ጠዋት 03:00 የጀመረው የዚህ ምድብ ጨዋታ እስከ ምሽት 12:30 ድረስ ዘልቋል፡፡ በመጀመርያ የተገናኙት ንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ ከ አዳማ ከተማ ሲሆኑ አዳማ ከተማ በታታሪዋ አጥቂ አይዳ ኡስማን ብቸኛ ግብ 1-0 አሸንፏል፡፡ በዚህም በምድብ ሀ 2ኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ ለፕሪምየር ሊጉ 3ኛ ደረጃ ፍለልሚያ ከሀዋሻ ከተማ ጋር እንደሚጫወት አረጋግጧል፡፡

05:00 ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ድሬዳዋ ከተማን አስተናግዶ 2-1 በማሸነፍ በምድብ ሀ 4ኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቅ ችሏል፡፡

በ08:30 የተገናኙት የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚና ጥረት ነበሩ፡፡ ተመጣጣኝ ፉክክርና ይህ ነው የሚባል ግልፅ የማግባት አጋጣሚዎች ያልታየበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ 0-0 በሆነ ውጤት ሊጠናቀቅ ችሏል፡፡

በእለቱ የምድብ ሀ የመጨረሻ ጨዋታ አስቀድሞ የምድቡ አሸናፊ መሆኑን ሶስት ጨዋታዎች እየቀረው ያረጋገጠው ደደቢት ከኢትዮጵያ ቡና ተገናኝተው ሰማያዊዎቹ 4-0 ማሸነፍ ችለዋል፡፡

ደደቢቶች ከ4 ቋሚ ተሰላፊ ተጫዋቾቻቸው በስተቀር በአመዛኙ በውድድር ዘመኑ እምብዛም የመሰለፍ እድል ያለገኙ የቡድኑ አባላት በዛሬው ጨዋታ ተጠቅመዋል፡፡ ኢትዮጵያ ቡናዎች በተለይም በመጀመሪያው አጋማሽ ከደደቢቶች በተሻለ ኳስን ተቆጣጥረው በመጫወት ቶሎ ቶሎ ወደ ፊት ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡ በአንጻሩ ደደቢቶች በሎዛ አበራና በሰናይት ባሩዳ ካደረጓቸው ሙከራዎች በዘለለ ይህ ነው የሚባል የግብ እድልን መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ የደደቢቱ አሰልጣኝ ጌቱ ተሾመ የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾች የሆኑትን አንበሏን ኤደን ሽፈራውንና ብሩክታዊት ግርማን ቀይረው በማስገባት በመጀመሪያው አጋማሽ ብልጫ ተወስዶባቸው የነበረውን የመሀል ሜዳ እንቅስቃሴ ማስመለስ ችለዋል፡፡ የደደቢቶች ፍፁም የበላይነት በተስተዋለበት በዚሁ የሁለተኛው አጋማሽ ደደቢቶች በሎዛ አበራ ፣ ትበይን መስፍን ፣ ቤዛ አስረስ እንዲሁም ሰናይት ቦጋለ ባስቆጠረችው ግሩም ግብ በመታገዝ 4-0 መርታት ችለዋል፡፡

የምድብ ሀ የመጨረሻ ጨዋታ በመጪው እሁድ ሲካሄድ ቦሌ ክፍለ ከተማ ከ መከላከያ 05:00 ላይ ይጫወታሉ፡፡

ምድብ ለ

የምድብ ለ የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታዎች ትላንት ተጀምረው ዛሬ መቋጫቸውን አግኝተዋል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሲዳማ ቡናም 4ኛ እና 5ኛ ደረጃ ይዘው ማጠናቀቃቸውን ያረጋገጡበት ድል አስመዝግቧል፡፡

09:00 ላይ በባንክ ሜዳ በተካሄደው ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ኢትዮዽያ ንግድ ባንክን 1-0 በሆነ ውጤት አሸንፏል። ብዙም ሳቢና ማራኪ ባልነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ንግድ ባንክ በኩል አብዛኛውን ቋሚ ተሰላፊ ተጨዋቾችን ይዞ ያልገባ ሲሆን በጨዋታውም በንግድ ባንክ በኩል ብዙነሽ ሲሳይ ተቀይራ ገብታ ካደረገችው አንድ የጎል ሙከራ ውጭ ይህ ነው ተብሎ የሚጠቀስ የጎል ሙከራ አልተመለከትንም። በአንፃሩ ፈረሰኞቹ በጨዋታው ብልጫ ወስደው የተጫወቱ ሲሆን የማሸነፍያውን ጎል ከእረፍት በፊት ትግስት ኦላና አስቆጥራ አሸንፋው ሊወጡ ችለዋል።

በተመሳሳይ 09:00 ሀዋሳ ላይ የተካሄደው የሀዋሳ ከተማ እና የሲዳማ ቡና ጨዋታ በእንግዶቹ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ለሲዳማ ቡና ወሳኟን ጎል በ78ኛው ደቁቃ ያስቆጠረችው ረድኤት አሳሳኸኝ ናት፡፡

ሌላው በተመሳሳይ ሰአት ኤሌክትሪክ ሜዳ ላይ የተካሄደው የአዲስ አበባ ከተማ እና አርባምንጭ ከተማ ጨዋታ በአአ ከተማ 2-0 አሸናፊነት ቢጠናቀቅም ሲዳማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በማሸነፋቸው አአ ከተማ 6ኛ ደረጃ ይዞ ለማጠናቀቅ ተገዷል፡፡ የአጠ ከተማን የድል ጎሎች ያስቆጠሩት አስናቀች ትቤሶ እና ተራማጅ ተስፋዬ ናቸው፡፡

በዚህ ምድብ ትላንት ሁለት ጨዋታዎች አአ ስታድየም ላይ ተደርገው ጌድዮ ዲላ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለከተማን 3-1 ፤ ቅድስት ማርያም ደግሞ ልደታ ክፍለከተማን 5-2 በሆነ ውጤት አሸንፈዋል፡፡

የሴቶች ፕሪምየር ሊግ በመጪው ግንቦት 6 በሚደረጉ የፍጻሜ ጨዋታዎች ሲጠናቀቅ የምድብ ሀ አሸናፊው ደደቢት ከ ምድብ ለ አሸናፊው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ10:00  አአ ስታድየም ላይ ለዋንጫ ይጫወታሉ፡፡ ከዚህ ጨዋታ ቀደም ብሎ ደግሞ ለ3ኛ ደረጃ የሚደረገው ጨዋታ በአዳማ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ መካከል ይደረጋል፡፡


በሴቶች ፕሪምየር ሊግ የምድብ ጨዋታዎች ፣  የፍጻሜ ጨዋታ ፣ በቀጣዩ አመት ፎርማት እና በመሳሰሉት ጉዳዮች ዙርያ በድረገፃችን እና በአባይ ኤፍ ኤም በሚኖረን ፕሮግራም በተከታታይ እንደምናቀርብ ከወዲሁ እንገልጻለን፡፡


Leave a Reply