“ከህንድ ህክምና አድርጌ ስመለስ በእርግጠኝነት ወደምወደው እግር ኳስ እመለሳለው” ታከለ አለማየሁ

የአዳማ ከተማው የመስመር አማካይ ታከለ አለማየሁ በሐምሌ ወር 2008 በአንድ ምሽት በአዳማ በሚገኝ የመዝናኛ ስፍራ በተነሳ ፀብ አይኑ ላይ በጠርሙስ ተወግቶ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት ላለፉት ወራት ህክምና በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ ታከለ በወቅታዊ ሁኔታው ዙርያ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠው አስተያየት ለመጨረሻ የህክምና ምርመራ ወደ ህንድ እንደሚጓዝ ገልጿል፡፡

” አሁን ጤንነቴ በጣም ጥሩ ነው፡፡ እየተሰማኝ ያለው ስሜትም ጥሩ ነው፡፡ በቀጣይ ወደ ህንድ በማቅናት በቅርብ ቀናት ውስጥ ለመጨረሻ የህክምና ምርመራ ወደ ህንድ እሄዳለው፡፡ ዶክተሮቹም ጥሩ የሆነ ተስፋ ሰጥተውኛል፡፡ እንግዲህ የሚሆነውን ሄጄ ነው የማቀው፡፡ ” ሲል አስተያየቱን የሰጠው ታከለ ለጉዞው እንቅፋት ሊሆንበት የሚችለውን ስጋትም ገልጿል፡፡

” የአምስት ወር ደሞዝ እስካሁን አልተከፈለኝም፡፡ ወደ ህንድ የማቀናው ከክለቡ በማገኘው ብር ነው። እስካሁን ደሞዜን ባይሰጡኝም ከክለቡ አመራሮች ጋር ተነጋግሬ የሰጡኝ ምላሽ ጥሩ ነው፡፡ በቅርብም ቀናት ሊሰጡኝ እንደሚችሉ ነግረውኛል” ብሏል፡፡

ታከለ በመጨረሻም ከህንድ ህክምናውን አድርጎ ሲመለስ ወደ እግርኳስ እንደሚመለስ ተስፋውን ገልጿል፡፡

” አሁን ጥሩ ስሜት ነው የሚሰማኝ፡፡ የጤንነቴ ጉዳይ ጥሩ መሻሻል እያሳየ ነው፡፡ ከህንድ ስመለስ በእርግጠኛነት ወደምወደው እግር ኳስ ጨዋታ እመለሳለው ብዬ አስባለሁ።” በማለት ሀሳቡን አጠቃሏል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *