ቢንያም አሰፋ ለረጅም ወራት ከሜዳ ካራቀው ጉዳት አገግሞ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መልካም እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል፡፡ ቢንያም በወቅታዊ ጉዳዮች ዙርያ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
ለረጅም ወራት ከጉዳት ርቀህ ነበር፡፡ የጉዳቱ አይነት ምንድን ነበር? አሁንስ ያለህበት ሁኔታስ እንዴት ነው?
አሁን በጥሩ ሁኔታ ላይ እገኛለው፡፡ ልምምዴንም በአግባቡ እየሰራው እየተጫወትኩም እገኛለው ። ጉዳቴ ረጅም ጊዜ አስቀምጦኝ ነበር። የጉዳቴ ሁኔታም የጉልበቴ መገጣጠምያ መስፋት ነበር። ህክምና እስካደርግ ድረስ መገጣጠምያው እየተለጠጠ መስፋቱን አላወኩም ነበር፡፡ የተወሰ እያረፍኩ መልሼ እየተጫወትኩ ነበር፡፡ ያ ህመሙን አክብዶብኝ ነበር። አሁን ህክምናውን በአግባቡ ተከታትዬ በጥሩ ሁኔታ ላይ እገኛለው፡፡
ለጅማ አባቡና በዘንድሮ የውድድር አመት ለመጫወት ፈርመህ ነበር፡፡ ሆኖም ምንም አገልግሎት ሳትሰጥ ወደ ባንክ ተመልሰህ እየተጫወት ትገኛለህ። ከጅማ አባቡና የለቀቀክበትና ወደ ንግድ ባንክ የገባህበት ሁኔታ እንዴት ነው?
ጅማ አባቡና እንደገባሁ ነው ጉዳቱ ያጋጠመኝ። ከዛ በኋላ አንደኛው ዙር ሙሉ አልተጫወትኩም። ጉዳቱም ብዙ ጊዜ ፈጅቶብኝ ለጨዋታ አላበቃኝም ነበር፡፡ ሁለተኛው ዙር ሲጀመር ለጨዋታ የምደርስበት ሁኔታ ሲፈጠርና ዶክተሩም መጫወት እንደምችል ሲነግረኝ ጅማ አባቡናም አሰልጣኝ ቀይሮ ነበርና ያለሁበትን ሁኔታ ሲጠይቁኝ አሁን ለጨዋታ ዝግጁ እንደሆንኩና ከሁለት ጨዋታ በኋላ ማች ፊትነሴን አስተካክዬ መጫወት እንደምችል ስነግራቸው አይ በስምምነት እንለያይ ብለው ነገሩኝ፡፡ በዚህ ምክንያት ከጅማ አባቡና ጋር ተለያይቼ አሰልጣኝ ሲሳይ ከበደን አናግሬው ወደ ንግድ ባንክ ልገባ ችያለው ።
ንግድ ባንክ ምንም እንኳን ወራጅ ቀጠና ውስጥ ቢገኝም አንተ በግልህ ጥሩ እየተንቀሳቀስክ ጎልም እያስቆጠርክ ነው…
እንደሚታወቀው ለአምስት ወር ቁጭ ብዬ ነበር። የመጀመርያ ጨዋታ ሳደርግ እንኳን የአንድ ሳምንት ልምምድ አድርጌ ነው ወደ ጨዋታ የመጣሁት፡፡ ያም ክለቡን ለመርዳት ስለፈለኩ ነው ወደ ንግድ ባንክ የመጣሁት። ክለቡም በእኔ እምነት ጥሎብኝ እየተጫወትኩ እገኛለው። ጎል ባስቆጥርም ጥሩ ብንቀሳቀስም እስካሁን ይህ ነው የሚባል እንቅስቃሴ እንዳላደረኩ ነው የሚሰማኝ፡፡ ገና ነኝ ይቀረኛል ብዬ ነው የማስበው ።
ንግድ ባንክ ላለመውረድ እየታገለ ይገኛል፡፡ ከዚህ በኋላ ጉዟችሁ ምን ይሆናል ብለህ ታስባለህ?
ሁላችንም ተጨዋቾች ጠንክረን ቡድኑን ለማትረፍ እየታገልን እንገኛለን። የቀሩት አራት ጨዋታዎች ናቸው፡፡ ቡድኑ አስቸጋሪ ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ያም ቢሆን ግን እስከ መጨረሻው ጨዋታ ድረስ ተስፋ አለን፡፡ ስለሆነም በቀሩት ጨዋታዎች ላይ የምንችለውን ሁሉ አድርገን ክለቡን ለማትረፍ በትኩረት እንጫወታለን።