የጨዋታ ሪፖርት | መከላከያ ከሁለት የአቻ ውጤቶች በኋላ ወደ ድል ተመልሷል

የ27ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ጨዋታ በመከላከያ እና በድሬደዋ ከተማ መሀከል ተደርጎ መከላከያ በባዬ ገዛሀኝ ብቸኛ ጎል በማሸነፍ ከወራጅ ቀጠነው በእጅጉ መራቅ ችሏል።

ቀዝቀዝ ብሎ ተጀምሮ እየተሟሟቀ በቀጠለው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ መጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ድሬዎች በተሻለ ኳስን ተቆጣጥረው ወደ ተጋጣሚያቸው ሜዳ ለመግባት የያደርጉት የነበረው ጥረት መከላከያዎችን በመጠኑ ወደኋላ አፈግፍገው የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን እንዲጠብቁ ያስገደዳቸው ይመስል ነበር ። ሆኖም እስከ መጀመሪያዎቹ 30 ደቂቃዎች የዘለቀው የብርቱካናማዎቹ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ያስገኘላቸው በ12ተኛው ደቂቃ በረከት ይስሀቅ ከሳጥን ውጪ ሞክሮት ኢላማውን ሳይጠብቅ የቀረውን ዕድል ብቻ ነበር ።

በ3 5 2 ቅርፅ ጨዋታውን የጀመረው የአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ቡድን ምንም እንኳን አራት አማካዮችን በሚጠቀመው የመከላከያ የአማካይ ክፍል ላይ የቁጥር ብልጫ የነበረው ቢሆንም በጦሩ የመስመር አማካዮች እንቅስቃሴ ምክንያት በማጥቃቱ ላይ በአግባቡ መሳተፍ ያልቻሉት የመስመር ተመላላሾቹ ወደኋላ መሳባቸው ቡድኑ እንደመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የዘለቀ የኳስ ቁጥጥር እንዳይኖረው አድርጓል ። መከላከያዎችም በሂደት ጨዋታውን በመቆጣጠር እና ወደ ድሬዎች የግብ ክልል ገፍተው መጫወት በመጀመር ተደጋጋሚ ዕድሎችን መፍጠር ችለዋል ።

28ኛው ደቂቃ ላይ ቴውድሮስ በቀለ ከሳምሶን ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ ግብ ጠባቂው ቀድሞ ኳስ ካወጣበት በኋላ መከላከያዎች የተሻ ግዛው ከ ሳሙኤል ሳሊሶ ተቀብሎ በቅርብ ርቀት ሞክሮት ወደላይ የተነሳበትን እና 36ኛው ደቂቃ ላይ ባዬ ገዘሀኝ ከሳጥን ውጪ በድንቅ ሁኔታ ሞክሮ አሁን ሳምሶን ያወጣበትን ዕድል መፍጠር ችለዋል ። ጫናቸውን በዚህ መልኩ የቀጠሉት መከላከያዎች ከ ሶስት ደቂቃዎች በኋላ ባዬ ገዛሀኝ ከመሀል የተላከለትን ኳስ ከድሬዎች ሳጥን ጠርዝ ላይ በቀጥታ በመምታት ባስቆጠራት ድንቅ ኳስ መሪ መሆን ቻሉ ። አጥቂው ባዬ ገዛሀኝም ከጉዳት መልስ የመጀመሪያ ግቡን ማስቆጠር ችሏል፡፡

ጨዋታውን መምራት የጀመሩት መከላከያዎች በመጀመሪያው አጋማሽ ጭማሪ ደቂቃ ላይም ሳሙኤል ሳሊሶ ከግራ በኩል ከባዬ ገዛሀኝ ግልፅ ዕድል ተፈጥሮለት ለማመን በሚከብድ መልኩ አመከነው እንጂ ምንአልባትም ጦሩ በሁለት ግቦች የመጀመሪያውን አጋማሽ ሊያጠናቅቅ ይችል ነበር ። ብርቱካናማዎቹም ከዕረፍት በፊት አቻ መሆን ሚችሉበትን ዕድል  ከ ባዬ ጎል በኋላ በ41ኛው ደቂቃ ከመሀል ሜዳ በዘነበ ከበደ በተሻማውን እና አቤል ማሞ ሲያወጣ ይሁን እንዳሻው ከግቡ ጥቂት ሜትሮች ላይ ባገኘው ኳስ ቢያገኙም ይሁን ያለግብ ጠባቂ የቀረው መረብ ላይ  አስቆጠረ ሲባል የሞከራት ኳስ ወደላይ ተነስታበታለች ።

ከሁለቱ አጥቂዎች በረከት ይስሀቅ እና ሀብታሙ ወልዴ ጀርባ የተሰለፈው እና በመከላከያ የአማካይ መስመር ተሰላፊዎች ብልጫ የተወሰደበትን ዮሴፍ ደሙዬን በሚካኤል ለማ ተክተው ሁለተኛውን ግማሽ የጀመሩት ድሬደዋ ከተማዎች በመጠኑ ወደመጀመሪያው የኳስ ቁጥጥር ብልጫቸው ቢመለሱም ወደ ሶስተኛው የሜዳ ክፍል ዘልቆ መግባት ግን ተስኗቸው ታይቷል ። መከላከያዎችም ጥሩ ሊባሉ የሚችሉ የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን መጀመር ቢችሉም ግልፅ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ግን ተቸግረው ታይተዋል ።

ሁለተኛውም አጋማሽ በአብዛኛው የጎል አጋጣሚዎች ሳይፈጠሩበት ቆይቶ የመጨረሻዎቹ 10 ደቂቃዎች ላይ ብቻ የተሻለ ፍጥነት የተላበሰ እንቅስቃሴ ለማየት ችለናል ። በተለይም 85ኛው ደቂቃ ላይ ድሬዎች ከዘነበ ከበደ የተነሳውን እና መከላከያዎች በሚገባ ያላወጡትን ኳስ ደጋግመው ቢሞክሩም መከላከያዎች ተደርበው አውጥተውባቸው  ከዛም አልፎ በሳሙኤል ታዬ አማካይነት ጥሩ የመልሶ ማጥቃት ዕድል ፈጥረው በመጨረሻም የተሻ ግዛው ለሳሙኤል ሳሊሶ አሻግሮለት ሳሙኤል ከሳምሶን ጋር ተገናኝቶ ማስቆጠር ሳይችል የቀረበት አጋጣሚ የጨዋታው ቀልብ የሚይዝ ሂደት ነበር ። ከዚህ በኋላ በነበሩት ደቂቃዎች መከላከያዎች ውጤት ለማስጠበቅ ተጠንቅቀው የተጫወቱ ሲሆን በሀብታሙ ወልዴ እና ሱራፌል ዳንኤል አማካይነት ሙከራዎችን ያደረጉት ድሬዎች እምብዛም ተጋጣሚያቸውን ማስጨነቅ ሳይችሉ ቀርተዋል ። በውጤቱም መሰረት መከላከያ ነጥቡን ወደ 35 ደረጃውን ደግሞ ወደ 7 በማሳደግ ከወራጅ ቀጠናው 7 ነጥቦች ርቋል ። ተሸናፊው ድሬደዋ ከተማም ከጨዋታው ምንም ነጥብ አለመሳካቱን ተከትሎ የመውረድ ስጋቱ እንዲባባስበት ሆኗል ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *