የጨዋታ ሪፖርት| የሲዳማ ቡና የቻምፒዮንነት ጉዞ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል 

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 27ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን መርሃግብር ለዋንጫ እየተፎካከረ የሚገኘው ሲዳማ ቡና በእጁ ገብቶ የነበረውን ሶስት ነጥብ ላለመውረድ እየታገለ በሚገኘው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በጨዋታው መገባደጃ በተቆጠረበት ግብ ተነጥቋል፡፡

ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ባሳለፍነው ሳምንት ከሜዳው ውጪ ወደ አዳማ አቅንቶ ከአዳማ ከተማ ጋር 1-1 ከተለያየው የቡድን ስብስብ ውስጥ በጉዳት ያልተሰለፈው ቢኒያም በላይን በደረጀ መንግስቱ በመተካት በመጀመርያ 11 ውስጥ ሲያካትት ግርማ በቀለም አቤል አበበን በመተካት በተመሳሳይ የ4-1-4-1 ቅርጽ ጨዋታውን ጀምረዋል፡፡ በዋንጫ ፉክክር ውስጥ የሚገኙት ሲዳማ ቡናዎች በበኩላቸው ባሳለፍነው ሳምንት በሜዳው ከመመራት ተነስቶ አዲስ አበባ ከተማን 3-1 ከረታው የቡድን ስብስብ ላይ ምንም ቅያሪ ሳያደርጉ በተመሳሳይ የ4-5-1 ቅርጽ ጨዋታውን መጀመር ችለዋል፡፡

በጨዋታው የመጀመሪያ 15 ደቂቃዎች በተለይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ኳስን መስርተው ለመጫወት ጥረት ቢያደርጉም ኳሶች ወደ ማጥቃት ክልል በሚገቡበት ወቅት በቀላሉ ሲበላሹ ታይተዋል፡፡ በአንጻሩ ሲዳማ ቡናዎች ወደ ኃላ እንደ ቡድን በማፈግፈግ ከተከላከሉ በኃላ ኳሶችን በሙሉአለም መስፍን አማካኝነት ፊት ላይ ለሚገኙት ሁለቱ ፈጣን አጥቂዎች ማለትም አዲስ ግደይና ላኪ ሳኒ በረጅሙ ለማድረስ ሲሞክሩ ተስተውሏል፡፡

እጅግ ጥቂት የሆኑ የግብ ሙከራዎች በታዩበት በዚሁ በመጀመሪያው አጋማሽ 11ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመሀል ተከላካይ ስፍራ ተሰላፊ የሆነው የግርማ በቀለን ስህተት ተጠቅሞ ያገኘውን ኳስ ላኪ ሳኒ ከቀኝ መስመር ያሻማለትን ኳስ አዲስ ግደይ በመግጨት ወደ ግብ የላካትና የግቡ ቋሚን ለትማ የተመሰችው ኳስ በሲዳማዎች በኩል የምትጠቀስ አጋጣሚ ነበረች፡፡

በመጀመሪያዎቹ 25 ደቂቃዎች በንግድ ባንኮች በኩል በ4-1-4-1 ቅርፅ ከተከላዮቹ ፊት የተሰለፈው ጋብሪኤል አህመድ በተደጋጋሚ ቡድኑ ከማጥቃት ወደ መከላከል በሚያደርገው ሽግግር ወቅት በሚፈጥራቸው የቦታ አያያዝ ችግር የተነሳ በሲዳማ ቡናዎች ፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ በተደጋጋሚ ተጋላጭ ከነበሩት 4ቱ የንግድ ባንክ ተከላካይ ስፍራ ተጫዋቾች ፊት የሚገኙትን ሰፋፊ ክፍተቶችን መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡

በ19ኛው ደቂቃ ላይ ሮቤል ግርማ ትርታዬ ደመቀ ላይ በሰራው ጥፋት የተሰጠውን የቅጣት ምት ፍፁም ተፈሪ በግሩም ሁኔታ አሻምቶ ሙሉአለም መስፍን በግንባሩ በመግጨት ሲዳማ ቡናን ቀዳሚ ያደረገች ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡ ለግቧ መቆጠርም የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ደካማ የሆነ ዞንን የመከላከል ሂደት ዋንኛ ምክንያት ነበር፡፡ ግቧ በተቆጠረችበት አጋጣሚ የንግድ ባንኩ ግብ ጠባቂ ኢማኑኤል ፌቮ የወገብ ጉዳት አጋጥሞት ለ7 ደቂቃዎች በሜዳ ላይ ህክምናውን ተከታትሎ ጨዋታውን ለተወሰኑ ያክል ደቂቃዎች መቀጠል ቢችልም በደቂቃዎች ልዩነት በሙሴ ገ/ኪዳን ተተክቶ ከሜዳ ሊወጣ ግድ ብሎታል፡፡

ከግቧ መቆጠር በኃላ የተነቃቁ የሚመስሉት ንግድ ባንኮች ከተጋጣሚያቸው በተሻለ በቀሩት ደቂቃዎች መንቀሳቀስ ችለዋል፡፡ ሆኖም በተደጋጋሚ በቀጥተኛ የመስመር አጨዋወት ወደ ሲዳማ የግብ ክልል መድረስ ቢችሉም በማጥቃት እንቅስቃሴ ወቅት በቁጥር አነስ ብለው ስለሚንቀሳቀሱ ስኬታማ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡ በ35ኛው ደቂቃ ላይ ዳንኤል አድሀኖም ከመስመር ያሻማውን ኳስ ቢኒያም በላይ በግሩም ሁኔታ ሞክሯት የግቡ አግዳሚ የመለሰበት አጋጣሚ ንግድ ባንኮች በመጀመሪያው አጋማሽ ያመከኗት አስቆጭ አጋጣሚ ነበረች፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በቻሉት አቅም ሁሉ አጥቅተው ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ ሲዳማ ቡናዎች ያገኟትን አንድ ግብ ለማስጠበቅ በሚመስል መልኩ ለጥንቃቄ ቅድሚያ በመስጠት በአመዛኙ በመከላከል እንቅስቃሴ ላይ ትኩረት አድርገው ተንቀሳቅሰዋል፡፡

በንግድ ባንኮች በኩል በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ 20 ደቂቃዎች ላይ ቢኒያም በላይ በግሉ በተደጋጋሚ ፍጥነቱን በመጠቀም ተጫዋቾችን አልፎ በመሄድ ወደ አደጋ ክልል ኳሶችን ለማድረስ ጥረት አድርጓል፡፡ ሲዳማ ቡናዎች በበኩላቸው ወደ ኃላ አፈግፍገው በመጫወት ከተጋጣያቸው በተደጋጋሚ ይሰነዘሩባቸው የነበሩትን ጥቃቶች በመመከት በኩል የተዋጣላቸው የነበሩ ቢሆንም የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴያቸው እምብዛም አመርቂ አልነበረም፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ አሰልጣኝ ሲሳይ ከበደ በቀሯቸው ሁለት ቅያሬዎች ፒተር ኑዋድኬንና አቢኪዮ ሻኪሩን በማስገባት በ3 አጥቂዎች ለመጫወት ጥረት አድርገዋል፡፡ በ69 ደቂቃ ላይም ንግድ ባንክን ወደ ጨዋታው ሊትመልስ የምትችለውንና  የሲዳማ ቡናው የቀኝ መስመር ተከላካይ ግሩም አሰፋ ኳስ በእጅ በመንካቱ የተገኘችውን የፍፁም ቅጣት ምት ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ፒተር ንዋድኬ ሳይጠቀምባት ቀርቷል፡፡ ነገር ግን የፍፁም ቅጣት ምቱ በተሰጠበት ወቅት የሲዳማ ቡና ተጫዋቾች (በተለይም የቡድኑ አምበል ለአለም ብርሃ)  ጨዋታውን የመሩት ዳኛ ላይ ያሳዩት ከስፖርታዊ ውጪ የሆነ ስነምግባር ሊታረም የሚገባው ነው፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ የተዳከሙት ሲዳማ ቡናዎች በ74ኛው ደቂቃ ላይ ሙሉአለም መስፍን ከራሳቸው የግብ ክልል በግሩም ሁኔታ ያሳለፈለትን ኳስ አዲስ ግደይ አፈትልኮ ከገባ በኃላ ያመከናት ኳስ ብቸኛዋ ተጠቃሽ ሙከራ ነበረች፡፡

በጨዋታው የመገባደጃ ደቂቃዎች ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ረጃጅም ኳሶችን ወደ ሲዳማ የግብ ክልል በተደጋጋሚ በመጣል አደጋዎችን ለመፍጠር ችለዋል፡፡ ይህም ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ በ88ኛው ደቂቃ ላይ ዳንኤል አድሀኖም ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ የሲዳማ ቡና ተከላካዮች በአግባቡ ማራቅ ባለመቻላቸው ጋብሬል አህመድ አግኝቶ በማስቆጠር የንግድ ባንክን ተስፋ ያለመለመች የአቻነት ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡ ግቧ ከመቆጠሯ ሰከንዶች በፊት የሲዳማ ቡናው አማካይ ሙሉአለም መስፍን ባጋጠመው የትከሻ ጉዳት ለህክምና እርዳታ በቀጥታ ወደ ቤተዛታ ሆስፒታል ለማምራት ተገዷል፡፡

ከግቧ መቆጠር በኃላ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በተጨማሪ ደቂቃ ላይ ያገኙትን ፍፁም ግልጽ የሆነ የማግባት አጋጣሚ ቤኒናዊው አቢኪዮ ሻኪሩ ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡

ጨዋታው 1-1 በሆነ የአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ሲዳማ ቡና የሊጉን መሪነት ነገ ቅዱስ ጊዮርጊስ እስኪጫወት ድረስ መውሰድ የሚችልበትን አጋጣሚ ሳይጠቀም ቀርቷል፡፡ ሲዳማዎች በነበራቸው ነጥብ ላይ አንድ አክለው በ47 ነጥብ አሁንም በ2ኛ ደረጃ ላይ ሲገኙ በአንጻሩ በወራጅ ቀጠና እየዳከረ የሚገኘው ንግድ ባንክ በ24 ነጥብ አሁንም 15ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *