የጨዋታ ሪፖርት | ደደቢት ወደ 2ኛ ደረጃ ሲመለስ ጌታነህ ከበደ ለከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ክብር ተቃርቧል

በኢትዮጵያፕሪሚየር ሊግ 27ኛ ሳምንት መርሃግብር አፄዎቹን ያስተናገዱት ሰማያዊዎቹ ደደቢቶች በጌታነህ ከበደ ሁለት ግቦች በመታገዝ ደረጃቸውን ያሻሻሉበትን ድል ማስመዝገብ ችለዋል፡፡ ጌታነህ ከበደም የግብ መጠኑን ወደ 21 በማሳደግ ለ16 አመታት የቆየውን የ24 ግብ በአንድ የውድድር ዘመን በሊጉ የማስቆጠርን ክብረወሰን ለመጋራት ተቃርቧል፡፡

ባለሜዳዎቹ ደደቢቶች ባሳለፍነው ሳምንት ከመከላከያ ጋር 0-0 ከተለያየው ቡድን ውስጥ ኤፍሬም አሻሞን በቅጣት ምክንያት ባልተሰለፈው ዳዊት ፍቃዱ በመተካት በተመሳሳይ የ4-2-3-1 ቅርጽ ጨዋታውን መጀመር ችለዋል፡፡ ፋሲሎች በበኩላቸው ባሳለፍነው ሳምንት በሜዳው በአዲሱ አሰልጣኝ ምንተስኖት ጌጡ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተመሩ አርባምንጭ ከተማን 2-0 ካሸነፈው ቡድን ምንም አይነት ለውጥ ሳያደርጉ በተመሳሳይ 4-3-3 ቅርጽ ጨዋታውን ጀምረዋል፡፡

ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት የፋሲል ከተማ ተጫዋቾች በቅርቡ በተከታታይ ከዚህ አለም በሞት ለተለዩት የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ለሆኑት ዘነበ በላይ እና ቢኒያም ምትኩ መታሰቢያ የሆነ ባነር በማሰራት በሚስማር ተራ አካባቢ ለሚገኙ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች አበርክተዋል፡፡

ሌላኛው በዚሁ ጨዋታ ላይ የታየው ክስተት ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ስታዲየሞች ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የስታድየሙን የፀጥታ ሁኔታ ለመከታተል የሰለጠኑ አነፍናፊ ውሾች በስታድየሙ የተለያዩ ክፍሎች እየተንቀሳቀሱ ክትትል ሲያደርጉ መስተዋሉ ነበር፡፡

በመጀመሪያው 15 ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች ወደ ግራ መስመራቸው ባደላ መልኩ በፈጣን የመስመር አጨዋወት በተደጋጋሚ ወደ ጎል ለመድረስ ቢሞክሩም እምብዛም አመርቂ አልነበሩም፡፡ በተለይ በደደቢት በኩል ከሶስቱ የአጥቂ አማካዮች ውስጥ በጨዋታው የመጀመሪያ 15 ደቂቃዎች በቀኝ መስመር እንዲሁም በቀሩት ደቂቃዎች በግራ መስመር የአጥቂ አማካይነት ሲጫወት የነበረው ሰለሞን ሀብቴ በአመዛኙ ደደቢቶች በመጀመሪያው አጋማሽ ባደረጓቸው የማጥቃት እንቅስቃሴዎች ውስጥ በቀጥታ ተሳትፎ ለማድረግ ችሏል፡፡ ከነዚህም መካከል በተለይ በ19ኛው ደቂቃ ኤፍሬም አሻሞ ከግራ መስመር ወደ መሀል ያሳለፈውን ኳስ ሰለሞን በአግባቡ ተቆጣጥሮ አንድ የፋሲል ተከላካይ ካለፈ በኃላ ወደ ግብ የሞከራትና ለጥቂት ከግቡ አናት በላይ የወጣችበት እንዲሁም በ33ኛው ደቂቃ ላይ ሽመክት ጉግሳ ከቀኝ መስመር ወደ መሀል ሰብሮ ከገባ በኃላ በግራ መስመር ላይ በጥሩ አቋቋም ላይ ለነበረው ሰለሞን ያቀበለውና ሰለሞን በግሩም ሁኔታ አክርሮ መትቶ ዮሀንስ ሽኩር በግሩም ሁኔታ ያዳነበት የሚጠቀሱ ነበሩ፡፡

ለወትሮው በፈጣን ከመከላከል ወደ ማጥቃት በሚደረጉ ሽግግሮች የሚታወቁት ፋሲሎች በዚህ ጨዋታ ከወትሮው ተዳክመው ተስተውለዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በመጀመሪያው አጋማሽ በርከት ያሉ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን ቢያገኙም ስኬታማ ባልሆኑ ቅብብሎች ሲበላሹ ተስተውሏል፡፡ በ20ኛው ደቂቃ ላይ ኤርሚያስ ሀይሉ የደደቢት ተከላካዮችን በአደገኛ ቀጠና ውስጥ የነጠቀውን ኳስ በግሩም ሆኔታ አሳልፎለት ኤዶም ሳይጠቀምባት የቀረው እንዲሁም ናትናኤል ጋንቹላ ከግራ መስመር ወደ መሀል ሰብሮ ከገባ በኃላ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታትን ኳስ ታሪክ ጌትነት በግሩም ሁኔታ ያዳነበት ሙከራ በፋሲሎች በኩል ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ፡፡

በ41ኛው ደቂቃ ላይ ብርሃኑ ቦጋለ ከግራ መስመር ወደ ሳጥን ውስጥ ያሻማውን ኳስ ልማደኛው ግብ አዳኝ ጌታነህ ከበደ በግንባሩ በመግጨት ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል፡፡ ግቧም ለጌታነህ በሊጉ ያስቆጠራት 20ኛ ግብ ሆና ተመዝግባለች፡፡

በደቂቃዎች ልዩነት ጌታነህ ከበደ የግብ ልዮነቱን ወደ ሁለት ሊያሰፋበትን የሚችለውን አጋጣሚ ቢያገኝም የሞከራት ኳስ ለጥቂት የግቡን ቋሚ ታካ ልትወጣ ችላለች፡፡ ፋሲል ከተማዎችም በኩል በ45ኛው ደቂቃ ላይ አቻ ሊሆኑ የሚችሉበትን አጋጣሚ ሄኖክ ገምቴሳ በተከላካዮች መሀከል አሾልኮለት ሰኢድ ሁሴን አስቆጠረ ተብሎ ሲጠበቅ አክሊሉ አየነው በግሩም ሆኔታ ተንሸራቶ አድኖበታል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ከጉዳት መልስ ባለፈው ሳምንቱ የአርባምንጭ ጨዋታ ወደ ሜዳ የተመለሰው ዮሀንስ ሽኩር ከጌታነህ ከበደና ከድር ኸይረድን ጋር ለኳስ ተሻምቶ ኳስ ከያዘ በኃላ ወደ መሬት ምቹ ባልሆነ መልኩ ማረፉን ተከትሎ ባገጠመው ጉዳት በ49ኛው ደቂቃ ላይ በቴዎድሮስ ጌትነት ተቀይሮ ለመውጣት ተገዷል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ከመጀመሪያው የተሻለ የመሸናነፍ ፉክክር ሊታይ ችሏል፡፡ ነገርግን ጨዋታው በሁለቱም ቡድኖች ተጫዋቾች በተከተሉት የሀይል አጨዋወት ምክንያት ጨዋታው በተደጋጋሚ ለመቋረጥ ተገዷል፡፡ ፋሲል ከተማዎች ከመጀመሪያው በተሻለ ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል በፍጥነት በመድረስ ረገድ የተሻሉ ቢሆኑም ይህ ነው የሚባል የግብ እድሎችን መፍጠር አልቻሉም፡፡

በ54ኛው ደቂቃ ላይ ናትናኤል ጋንቹላ ከግራ መስመር ያሻማውን ኳስ ቶጓዊዉ አጥቂ ኤደም ሆሮሶውቪ ገጭቶ ቢሞክርም ታሪክ ጌትነት እንደምንም ቢያድነውም የተመለሰችውን ኳስ ዳግም ኤደም በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር ቡድኑን ወደ ጨዋታው መመለስ ቻለ፡፡

ከግቧ መቆጠር በኃላ በነበሩት ደቂቃዎች ላይ ከደደቢቶች በተሻለ በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ጫና መፍጠራቸውን የቀጠሉት ፋሲሎች በተለይ በ59ኛው ደቂቃ ላይ ኤፍሬም አለሙ ሶስት የደደቢት ተጫዋቾችን አልፎ ከግራ መስመር ወደ መሀል ሰብሮ ከገባ በኃላ የሞከራትና ለጥቂት ወደ ውጪ የወጣችበት ኳስ ተጠቃሽ ሙከራ ነበረች፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ እጅግ በርከት ብለው ከተስዋሉት ሽኩቻዎች በአንዱ የደደቢቱ የቀኝ መስመር ተከላካይ የነበረው ስዮም ተስፋዬ ባጋጠመው ጉዳት የተነሳ በደስታ ደሙ ተቀይሮ ወጥቷል፡፡

በጨዋታው ከ65ኛው ደቂቃ ጀምሮ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ክስተት በሆነው ከስታዲየሙ የአንደኛው ወገን ወደሌላኛው ክፍል በሚገኙ ደጋፊዎች መካከል በሚደረገው የቅብብሎሽ ህብረ ዝማሪ የፋሲል ከተማና የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች በአብሮነት የሁለትን ቡድኖች ወንድማችነትን በሚያሳይ መልኩ ያሳዩት ማራኪ የቅብብሎሽ ህብረ ዜማ በስታድየሙ አስገራሚ ድባብን የፈጠረ ክስተት ነበር፡፡

በ78ኛው ደቂቃ ላይ በፈጣን የመልሶ ማጥቃት የተገኘውን አጋጣሚ ናትናኤል ንንቹላ በተከላካዮች መካከል ያሾለከለትን ኳስ ተጠቅሞ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው አብዱራህማን ሙባረክ በደደቢቶች የግብ ክልል የግራ ጠርዝ ላይ ብርሃኑ ቦጋለን በግሩም ሁኔታ ካለፈ በኃላ እጅግ ደካማ የሆነ ኳስን ወደ ግብ ባይልክ ኖሮ ግብ መቀየር የምትችል አጋጣሚ ነበረች፡፡

በደቂቃዎች ልዩነት በ79ኛው ደቂቃ ላይ ደደቢቶች ያገኙትን አጋጣሚ ኤፍሬም አሻሞ በሁለቱ የፋሲል የመሀል ተከላካዮች መሀል ያሾለከለትን ግሩም ኳስ ጌታነህ ከበደ የፋሲሉ ግብ ጠባቂ ቴዎድሮስን በማለፍ በጨዋታው ሁለተኛውን እንዲሁም የውድድር ዘመኑን 21ኛ ግቡን ማስቆጠር ችሏል፡፡

በቀሩት ደቂቃዎች ደደቢቶች ወደኃላ በማፈግፈግ በእጃቸው የገባውን ሶስት ነጥብ ላለማጣት በጥብ መከላከል ላይ መሠረት አድርገው ሲንቀሳቀሱ ፋሲሎች ይህን የመከላከል ስልት ሰብሮ ለማለፍ የሜዳውን ቁመት ከመጠቀም ይልቅ በቀጥተኛ አጨዋወት በረጃጅሙ ከተከላካይ በሚሻገሩ ኳሶች ለመጠቀም ያደረጉት ጥረት በቀላሉ በደደቢት ተከላካዮች ሲከሽፍ ተስተውሏል፡፡ በተጨማሪ ደቂቃ ላይ ፋሲል ከተማዎች አቻ ሊሆኑ የሚችሉበትን አጋጣሚ ኤደም በግንባሩ በመግጨት ቢሞክርም ታሪክ ጌትነት እንደምንም ሊያድንበት ችሏል፡፡

ይህን ውጤት ተከትሎ ደደቢት ነጥቡን ወደ 48 በማሳደግ ሲዳማ ቡናን በመብለጥ ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ4 ነጥብ አንሶ በሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ሲችል ተሸናፊው ፋሲል ከተማ በ38 ነጥብ አሁንም በ6ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *