የጨዋታ ሪፖርት | ሀዋሳ ከተማ ከ3 ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ ወደ ድል ተመልሷል

በ27ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሀዋሳ ላይ ወልድያን ያስተናገደው ሀዋሳ ከተማ 2-1 በማሸነፍ ከተከታታይ ሶስት ሽንፈት በኋላ ወደ ድል መመለስ ችሏል፡፡

ጨዋታው በርካታ ቁጥር ባለው ተመልካች ታጅቦ የተካሄደ ሲሆን በተለይም ከወልድያ በአዲስ አበባ አድርገው ሀዋሳ የገቡት እጅግ ረጅም እና አድካሚ ጉዞ ማድረጋቸው ሳይበግራቸው ቡድናቸውን ሲያበረታቱ ውለዋል፡፡

በጨዋታው ሙሉ ክፍለጊዜ ባለሜዳው ሀዋሳ ከተማ በወልድያ ላይ የእንቅስቃሴ እና የግብ ሙከራ የበላይነት ማሳየት ችለዋል፡፡ በተለይ በመጀመርያዎቹ 15 ደቂቃዎች ውስጥ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ማድረግ ሲችሉ ጎል ለማስቆጠር የፈጀባቸውም 9 ደቂቃ ብቻ ነበር፡፡ ጃኮ አረፋት ከጋዲሳ መብራቴ ጋር አንድ ሁለት ቅብብል አድርጎ ለፍሬው ሰለሞን ያቀበለውን ኳስ ፍሬው አስቆጥሮ ሀዋሳን መሪ ማድረግ ችሏል፡፡ አማካዩ ፍሬው በውድድር ዘመኑ ያስቆጠራቸውን የሊግ ጎሎች መጠን 10 በማድረስ አስደናቂ አመት ማሳለፉን ቀጥሏል፡፡

ከግቧ በኋላ ሀዋሳ ከተማዎች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር የሚያስችላቸውን በርካታ አጋጣሚዎች መፍጠር ቢችሉም ወደ ግብነት መቀየር ተስኗቸዋል፡፡ በተለይም አጥቂው ጃኮ አራፋት ከደስታ ዮሀንስ የተሻገረለትን ኳስ ሞክሮ ኢሚክሪል ቤሌንጌ በግሩም ሁኔታ ያወጣበት የምትጠቀስ አጋጣሚ ነበረች፡፡ የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃ ሲቀር ጋዲሣ መብራቴ ከዳንኤል ደርቤ ጋር አንድ ሁለት ተቀባብሎ ያሻገረውን ኳስ ጃኮ አራፋት ሳይደርስባት የቀረበት አጋጣሚም ተጠቃሽ ነበረች፡፡

በአንፃሩ ወልድያዎች የሚያደርጉት የማጥቃት እንቅስቃሴ በአንዱአለም ንጉሴ ተደጋጋሚ የጨዋታ ውጭ አቋቋም ምክንያት የተሳካ አልነበረም፡፡ ሀብታሙ ሸዋለም ከመታትና ኢላማውን ሳጠብቅ ከወጣችው የቅጣት ምት ሙከራ ውጭ ይህ ነው ተብሎ የሚጠቀስ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም፡፡

በሁለተኛው ግማሽ የጨዋታ ሂደት ሀዋሳ ከተማ እንደመጀመርያው ሁሉ የተሻለ መንቀሳቀስ የቻለ ሲሆን ወልድያም ተሻሽሎ መቅረብ ችሏል፡፡

ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ ተከላካዩ መሣይ ጳውሎስ በረጅሙ ያቀበለውን ኳስ ጃኮ አራፋት ተቆጣጥሮ ለታፈሰ ሰለሞን አቀብሎት ታፈሰ ሁለት ተጫዋቾችን አልፎ የመታውን ኳስ ቢሌንጌ በግሩም ሁኔታ አውጥቶበታል፡፡ ሀዋሳዎች ወደ ወልድያ የግብ ክልል ማምራታቸውን ቀጥለው በ56ኛው ደቂቃ ዳንኤል ደርቤ ከእጅ ውርወራ የሰጠው ኳስ አራፋትን ከቢሌንጌ ጋር ቢያገናኘውም አሁንም ወደ ውጭ ሰዷታል፡፡

በ61ኛው ደቂቃ ላይ ታፈሰ ሰለሞን ፣ አስጨናቂ ሉቃስ እና ጋዲሳ ግሩም ቅብብል ካደረጉ በኋላ ጋዲሳ ያሻገረውን ኳስ ጃኮ አራፋት የወልድያ ተከላካዮች ስህተት ታክለሎበት ለክለቡ ሁለተኛውን በግሉ ደግሞ 12ኛ የሊግ ግቡን አስቆጥሯል፡፡

ወልድያ ወደ ጨዋታው ለመመለስ የፈጀባቸው 2 ደቂቃዎች ብቻ ነበር፡፡ በ63ኛው ደቂቃ መልሶ ማጥቃትን በመጠቀም ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ሙሉጌታ ረጋሣ ከቀኝ መስመር በቀጥታ ያሻገረውን ኳስ አንዱአለም ንጉሴ በቀድም ክለቡ ላይ ከፍጹም ቅጣት ምት ክልሉ ውጪ በመምታት አላዛር መርኔ መረብ ላይ አስቆጥሯል፡፡ ይህ ጎል አንጋፋው አጥቂ አንዱአለም ንጉሴ በሊጉ ያስቆጠራቸው ጎሎች መጠን 10 ያደረሰበት ሆኗል፡፡

ከጎሉ መቆጠር በኋላ ባለሜዳዎቹ ሀዋሳዎች መሪነታቸውን አስተማማኝ ለማድረግ ጫና ፈጥረው መጫወት ችለዋል፡፡ በተለይ በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ በዳንኤል ደርቤ ፣ ፍሬው ሰለሞን እና ዮሀንስ ሰጌቦ አማካኝነት የተፈጠሩትን የግብ አጋጣሚን በእለቱ ድንቅ የነበረው ኢምክሪል ቢሌንጌ መክሸፍ ችለዋል፡፡

በ71ኛው ደቂቃ ላይ የሀዋሳ ከተማ ግብ ጠባቂ አላዛር መርኔ በድሩ ኑር ሁሴን ላይ በሰራው ጥፋት ቀይ ካርድ ይገባዋል በማለት የመሀል ዳኛውን የወልዲያ ተጫዋቾች እና አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ከፍተኛ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡

ጨዋታው ተጨማሪ ግቦች ሳይስተናገድበት በሀዋሳ ከተማ 2-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል፡፡ በዚህም ሀዋሳ ከ3 ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ ወደ አሸናፊነት በመመለስ ነጥቡን 34 አድርሶ 8ኛ ደረጃን ከወልድያ ሲረከብ ወልድያ በአንጻሩ ደረጃው ወደ 9ኛ ተንሸራቷል፡፡

የአሰልጣኞች አስተያየት

ውበቱ አባተ – የሀዋሳ ከተማ አሰልጣኝ

“ጨዋታው ጥሩ ነበር፡፡ በተከታታይ ሶስት ጨዋታ ተሸንፈን እንደመምጣታችን የዛሬው ድል ይገባናል፡፡ እውነት ለመናገር ከዚህም በላይ ተጫውተን በርካታ ግብ ማስቆጠር እንችል ነበር፡፡ ማሸነፋችን ይህንን ስተቶች አይሸፍንልንም፡”

” እኛ አሁንም ቢሆን ከስጋት ውጭ አደለንም፡፡ መውጣት መውረድ ያለ ነው፡፡ ከዚህ በላይ የመጫወት አቅማችንን በቀጣይ ማሣየት እንፈልጋለን፡፡”

የወልድያው አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ የድህረ ጨዋታ ቃለ ምልልስ ለመስጠት ፍቃደኛ አልነበሩም፡፡ ይህ ጉዳይ ሊስተካከል የሚገባው መሆኑን ሶከር ኢትዮጵያ ለመግለጽ ትወዳለች፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *