የጨዋታ ሪፖርት | የአርባምንጭ ከተማ ድል አልባ ጉዞ ቀጥሏል

በ27ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አርባምንጭ ከተማ በሜዳው አዳማ ከተማን አስተናግዶ ያለግብ በአቻ ውጤት ጨዋታውን ደምድሟል፡፡ አዞዎቹ በሁለተኛው ዙር ከገቡበት የውጤት ቀውስም መውጣት ተስኗቸዋል፡፡

አርባምንጭ ከተማ ከወራጅነት ስጋት ለመራቅ ፤ አዳማ ከተማ ወደ ዋንጫ ፍክክሩ ለመመለስ ያለመ ጠንካራ ፉክክርን በጨዋታው ቢያሳዩም ያገኟቸው የግብ እድሎችን ወደ ውጤት መቀየር ተስኗቸዋል፡፡

በጨዋታው የመጀመሪያ15 ደቂቃዎች ላይ አርባምንጭ ከተማዎች ወደ ግብ በመድረስ የተሻሉ ነበሩ፡፡ በተለይ እንዳለ ከበደ ያገኛቸውን ሁለት ያለቀላቸው እድሎች ወደ ግብነት መለወጥ ቢችል አዞዎቹ መሪ የሚሆኑበት አጋጣሚ ይፈጠር ነበር፡፡ በአንፃሩ አዳማ ከተማዎች ተደጋጋሚ ሙከራዎችን በዳዋ ሁቴሳ አማይነት መፍጠር ችለዋል፡፡

ጨዋታው በሁለቱም በኩል በሚደረጉ የማጥቃት እንቅስቃሴዎች ተሟሙቆ ቀጥሎ በ30ኛው ደቂቃ አርባምንጭ ከተማዎች ቅጣት ምት አግኝተው ወደ ግብ በሚመታበት ወቅት የአዳማ ከተማው ኮንጓዊ ግብ ጠባቂ ጃኮ ፔንዜ ከኳስ ውጭ የአርባምንጭ ከተማው ተመስገን ካስትሮ ላይ በሰራው አደገኛ ጥፋት በፌድራል ዳኛ አሰፋ ወንጨፋ ቀይ ካርድ ተመዞበታች፡፡ ሆኖም አግባብ ያልሆነ ውሳኔ ነው በሚል በተፈጠረው ውዝግብ  ጃኮ ከሜዳው አልወጣም በማለቱ ጨዋታው ለ12 ያህል ደቂቃ ለመቋረጥ ተገዷል፡፡

ጃፈር ደሊልን ወደ ሜዳ በማስገባት ጨዋታውን የቀጠሉት አዳማ ከተማዎች ቀሪዎቹን ደቂቃዎች በጎደሎ ተጫዋቾች በመጫወት ውጤቱን ለማስጠበቅ ብርቱ ትግል አድርገዋል፡፡ የመጀመሪያው አጋማሽም 0 ለ 0 ተጠናቋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ አዳማ ከተማዎች አንድ ነጥብ ለማግኝት በማሰብ በተደጋጋሚ በሜዳ ላይ በመውደቅ ሰአት ለማባከን ያደረጉት ጥረት አርባምንጮችን ብስጭት ውስጥ ሲከት ተስተውሏል፡፡ ለ60 ደቂቃዎች የቁጥር ብልጫ ያገኙት አርባምንጮች ግልፅ የግብ እድሎች መፍጠር ባይችሉም ጫና በመፍጠር መንቀሳቀስ ችለዋል፡፡ በተለይ ተቀይሮ የገባው ታሪከኩ ጎጀሌ በግንባሩ በመግጨት ሞክሮ የግቡን ቋሚ ታኮ ወደ ውጪ የወጣበት የሚያስቆጭ የግብ አጋጣሚ ነበር፡፡

እመምብዛም ሳቢ ያልነበረው የሁለተኛው አጋማሽ ከጎል ሙከራዎች ይልቅ አወዛጋቢ የዳኝነት ውሳኔዎች አመዝነው የታዩበት ነበር፡፡ እንዳለ ከበደ ግብ አስቆጥሮ በመሀል ዳኛው ፀድቆ በረዳት ዳኛው ከጨዋታ ውጪ ተብሎ የተሻረበት ክስተት በአርባምንጮች በኩል ተቃውሞ ሲያስከትል ዳዋ ሆቴሳ በፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ተጠልፎ የፍጹም ቅጣት ምት ተከልክለናል በሚል የአዳማ ከተማ ተጫዋቾች ያሰሙት ቅሬታ የሚጠቀሱ ነበሩ፡፡

የአቻ ውጤቱን ተከትሎ በሁለተኛው ዙር አንድ ጨዋታ ብቻ ያሸነፈው አርባምንጭ ከተማ በአስከፊ ጉዞው ቀጥሎ ከወራጅ ቀጠናው በ4 ነጥቦች ርቆ 10ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ አዳማ ከተማ በ44 ነጥቦች በነበረበት 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡

Leave a Reply