በኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ 27ኛ ሳምንት ጨዋታ ወደ ጅማ የተጓዘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጅማ አባቡናን በሳላዲን ሰኢድ ብቸኛ ጎል 1-0 በማሸነፍ ለ4ኛ ተከታታይ የሊግ ዋንጫው መቃረብ ችሏል ።
አስገራሚ የጨዋታ እንቅስቃሴ ፣ የሚያስገርም የደጋፊ ድባብ ፣ የጅማ አባ ቡና ፍፁም የጨዋታ ብልጫ ፣ የፈረሰኞቹ ጨዋታ የማሸነፍ ልምድ እንዲሁም የፀጥታ አካላት ከልክ ያለፈ እነና አሳሳቢ የሀይል እርምጃ የጨዋታው ዋና ዋና ኩነቶች ነበሩ።
ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ አሁን አሁን በመልካም ሁኔታ በደጋፊዎችና በክለቦች መካከል ያለውን የወንድማማችነት መንፈስ ለማጠንከር ይረዳ ዘንድ የጅማ አባ ቡና የክለብ አመራሮች እና ደጋፊዎች ለቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ እና ደጋፊዎች ያላቸውን አክብሮት ለመግለፅ የክብር አቀባበል በማድረግ እና ስጦታም አበርክተውላቸዋል። ከዚህ በተጨማሪም የጅማ አባቡና የክለብ ሀላፊዎች በ1963 ዓ.ም ለጅማ አባቡና የተጫወቱት ሰኢድ አህመድ (የሳላዲን ሰኢድ አባት) መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ለሳላዲን ሰኢድ አባቱ በተጨዋችነት ዘመናቸው የተነሱትን ታሪካዊ ፎቶን ስጦታ የሰጡበት መንገድ በዕለቱ ለተገኛው የስፖርት ቤተሰብ እንዲሁም ሳላዲን ሰኢድን በእጅጉ አስደስቷል።
ጅማ አባቡና በኢትዮዽያ ቡና ጨዋታ ላይ ከተጠቀመባቸው የመጀመርያ አስራ አንድ ውስጥ ሀይደር ሸረፋ እና መሀመድ ናስርን ያልተጠቀመ ሲሆን ዳዊት ተፈራ ሱራፌል አወልን ተክቶ ወደ ሜዳ ገብቷል። በፈረሰኞቹ በኩል ደግሞ ከሀዋሳ ከተማ ጋር በነበረው ጨዋታ የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ከነበሩ ተጨዋቾች መሀከል ዘሪሁን ታደለ ፣ ፍሬዘር ካሳ ፣ መሀሪ መና እና ምንተስኖት አዳነ አራፊ ሲሆኑ ሮበርት ኦዶንካራ ፣ ደጉ ደበበ ፣ አበባው ቡጣቆ እና ተስፋዬ አለባቸው በምትካቸው በቋሚነት ጨዋታውን ጀምረዋል።
በፌደራል ዳኛ ይርጋለም ወ/ጊዮርጊስ ዋና ዳኝነት በጅማ አባቡና አማካኝነት የተጀመረው ጨዋታ የመጀመርያው 10 ደቂቃ ብዙም ማራኪ ያልሆነ እና በጠንካራ ሙከራ ያልታጀበ እንዲሁም በመሀል ሜዳ ላይ ብቻ የተገደበ ቢሆንም ጅማ አባቡና በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ወስዶ ተጫውቷል። የጨዋታውንም የመጀመርያ የጎል ሙከራ በማድረግም ባለ ሜዳዎቹ ጅማ አባቡናዎች ቀዳሚ ነበሩ ። ይህ ሙከራም 13ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ ኢሳያስ በግራ መስመር ሰብሮ በመግባት ያሻገረለትን አሜ መሀመድ ሞክሮት ሮበርት ኦዶንካራ እንደምንም ያወጣበት አጋጣሚ ነበር ። ከዚህ የጎል ሙከራ በኋላ የፈረሰኞቹ የመሀል ሜዳ ክፍል በፈጣኖቹ ተጨዋቾች ሄኖክ ካሳሁን ፣ ክርዚስቶን ታንቢን እና በዳዊት ተፈራ ማራኪ የኳስ ቅብብል አማካይነት ሙሉ ለሙሉ የበላይነት ተወስዶበት ታይቷል ። ሆኖም አሜ መሀመድ 31ኛው 45ኛው ደቂቃ ላይ ያመከናቸው ግልፅ የሆኑ የጎል አጋጣሚዎች የሚያስቆጩ ነበሩ ።
በአንፃሩ የጨዋታ ብልጫ የተወሰደባቸው ጊዮርጊሶች በመልሶ ማጥቃት ከተከላካዮች በሚሻገሩ ኳሶች ወደ ጎል በመድረስ ከሚፈጥሩት አጋጣሚ ሌላ 33ኛው ደቂቃ ላይ አዳነ ግርማ ከሳጥን ውጭ አክርሮ መቶ ጀማል ጣሰው ካዳነበት እና ሳላዲን ሰኢድ በግሉ ከሚያደርገው እንቅስቃሴ ውጭ ይህ ነው የሚባል ነገር አልተመለከትንም። ጨዋታውም ምንም ጎል ሳይስተናገድበት የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቆ ሁለቱም ቡድኖች ለእረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል ።
ድራማዊ የሆኑ የጨዋታ እንቅስቃሴዎች የታዩበት እና አላስፈላጊ የሀይል እርምጃ በፀጥታ አካላቶች የተወሰደበት የሁለተኛው አጋማሽ በከፍተኛ ዝናብ ታጅቦ ሲቀጥል እንደ መጀመርያው አጋማሽ ሁሉ ጅማ አባቡናዎች በኳስ ቁጥጥርም ሆነ በማራኪ አጨዋወት ብልጫ ወስደዋል፡፡ በፈረሰኞቹ በኩል በመከላከል ውስጥ የሚፈጠር የመልሶ ማጥቃት ስልት የጨዋታቸው አካል ነበር።
47ኛው ደቂቃ ላይ ናትናኤል ዘለቀ 19 ሜትር ርቀት ላይ መሬት ለመሬት አክርሮ ቢሞክርም ጀማል እንደምንም ወደ ውጭ አውጥቶበታል።
ሆኖም ጊዮርጊሶች የጅማ አባቡናን የአማካኝ ስፍራ ተጨዋቾች በፍፁም መቆጣጠር ያቃታቸው ሲሆን ተስፋዬ አለባቸው እና ናትናኤል ዘለቀ ሜዳ ውሰጥ አልነበሩም ማለት ይቻላል። 54ኛው ደቂቃ ላይም ተስፋዬ አለባቸው ኪዳኔ አሰፋን በክርን በመማታቱ በእለቱ ደኛ በቀጥታ ቀይ ከሜዳ ወጥቷል ።
የፈረሰኞቹን በጎዶሎ ተጫዋቾች መጫወትን ተከትሎ ቀድሞ በመሀል ሜዳ ከተወሰደባቸው ብልጫ አንፃር የበለጠ ክፍተቱ ይሰፋል ሲባል የጅማ አባቡና ተጨዋቾች ከትኩረት ወጥተው ባሉበት ሁኔታ 56ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ ሳላዲን ሰኢድ በግንባሩ ገጭቶ የጨዋታው ብቸኛ እና ፈረሰኞቹንም አሸናፊ የምታደርግ ጎል አስቆጠሯል ።
ከዚህ በኋላ የጨዋታው መልክ ተቀይሮ ጎል ፍለጋ የግብ ክልላቸውን ነቅለው የወጡት አባ ቡናዎች በጊዮርጊሶች ከሚሰነዘርባቸው የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት በመነሳት 59ኛው እና 63ኛው ደቂቃ ላይ ሳላዲን ሰኢድ ጣጣቸው ያለቁ ምን አልባትም ፈረሰኞቹ ከሁለት ለዜሮ በላይ መምራት የሚያስችሉ የጎል አጋጣሚዎች አግኝቶ አምክኗቸዋል። በአንፃሩ ጅማ አባቡናዎች ከጎሉ መቆጠር በኋላ የተዳከሙ ቢሆንም የአቻነት ጎል ፍለጋ ጥረት ማድረጋቸው አልቀረም ። በዚህም 74ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው በድሉ መርዕድ በግንባሩ ገጭቶ የግቡ አግዳሚ የመለሰበት ፣ 77ኛው ደቂቃ ላይ ክርዚስቶን ንታንቢ የሞከረው እና 83ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ ካሳሁን ከርቀት መቶት ሮበርት ኦዶንካራ ያዳነበት ዕድሎች የሚጠቀሱ ናቸው ። በተለይም ተቀይሮ የገባው ቢንያም ትዕዛዙ በቀኝ መስመር ከጅማ አባቡና የግብ ክልል አንስቶ በሚገር ሁኔታ ተከላካዮቹን በማለፍ ሳጥን ውስጥ ገብቶ መሬት ለመሬት የመታውን ሳላዲን በርጌቾ በሸርተቴ አወጣለው ብሎ የግቡ አግዳሚ የመለሰው ኳስ ጅማ አባቡናን አቻ የሚያደርግ አጋጣሚ ነበር ።
በተቀሩት ደቂቃዎች ፈረሰኞቹ በጎዶሎ ተጫዋቾች እንደመጫወታቸው ሰአት በማባከን እና ተጨዋች በመቀየር ውጤቱን ለማስጠበቅ ያደረጉት ጥረት ተሳክቶላቸው ጨዋታውን በአሸናፊነት አጠናቀው ወጥተዋል። ድሉን ተከትሎ ክለባቸውን ለመደገፍ 300 ኪሎ ሜትር በላይ አቋርጠው ለመጡት ደጋፊዎች ትልቅ ደስታን ሲፈጥር ክለቡም ወደ ዋንጫ የሚያደርገውን ጉዞ አሳምሮለታል ።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ካታንጋ አካባቢ ተወሰኑ የጅማ አባቡና ደጋፊዎች ድንጋይ መወርወራቸውን ተከትሎ ፀጥታ አካላት በቀላሉ ችግሩን መቆጣጠር እየተቻለ ከመጠን ያለፈ የሀይል እርምጃ መውሰዳቸው ተከትሎ በተፈጠረ ግርግር በርካታ ሰው መጎዳቱ የዕለቱ አሳዛኝ አጋጣሚ ነበር።