ዋልያዎቹ ባህርዳር ይጫወታሉ

 

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከሌሴቶ ጋር የሚያደርገውን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ እና ከኬንያ ጋር የሚደረገው የቻን ማጣርያ ጨዋታዎች በባህርዳር ስታድየም እንዲካሄዱ መወሰኑ ተነግሯል፡፡

ፌዴሬሽኑ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው በሰኔ ወር አዲስ አበባ ላይ የሚኖረው የአየር ንብረት ዝናባማ የሚሆን በመሆኑ ሜዳው ለመጫወት አዳጋች ይሆናል ከሚል መነሻ ነው፡፡

የእግርኳስ ፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ጁነይዲ ባሻ በትዊተር ገፃቸው ላይም የብሄራዊ ቡድኑ ጨዋታዎች ወደ ባህርዳር መዞራቸውን አረጋግጠዋል፡፡

የባህርዳር ስታድየም በግዝፈቱ እና ዘመናዊነቱ በኢትዮጵያ ቀዳሚው ሲሆን በዚህ አመት አንድ የቻምፒዮንስ ሊግ እና ሁለት የኮንፌድሬሽን ዋንጫ ጨዋታዎችን በብቃት አስተናግዷል፡፡

በተያያዘ ዜና ስዩም ተስፋዬ የብሄራዊ ቡድኑ አምበል ተደርጎ መረጡ ተነግሯል፡፡ የቀኝ መስመር ተከላካዩ በሰውነት ቢሻው ቡድን ውስጥ ቁልፍ ከነበሩ ተጫዋቾች አንዱ የነበረ ሲሆን በጉዳት እና አቋም መውረድ ምክንያት በደደቢት እና በብሄራዊ ቡድኑ እምብዛም ተሳትፎ ማድረግ አልቻለም ነበር፡፡ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ደደቢትን ከተረከቡ በኋላ ወደ ቀድሞ አቋሙ መመለስ የቻለ ሲሆን ከወራት በፊት ባህርዳር ላይ ከኮት ዲ ኦር ጋር በተደረገው የኮንፌድሬሽን ዋንጫ ጨዋታ ላይ ግብ ያስቆጠረ ሲሆን የጨዋታው ኮከብ ተብሎ መመረጡ ይታወሳል፡፡

 

ያጋሩ