የጨዋታ ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ነጥብ ተጋርተዋል

የ27ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ቀጥለው ሲካሄዱ 10፡30 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም የተገናኙት ሁለቱ የመዲናዋ ቡድኖች ጨዋታቸውን በአቻ ውጤት አጠናቀዋል ።

በቅርቡ ከዚህ አለም በሞት የተለየውን የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊ ዘነበ በላይ በህሊና ፀለቶ በማሰብ የተጀመረው ጨዋታ በኢትዮጵያ ቡና እና ቀደም ብሎ ከደደቢት ጋር በተጫወተው የፋሲል ከተማ ደጋፊዎች ልዩ ድባብ ነበር የተካሄደው ። ጨዋታው 15ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስም በስቴድየሙ የተገኙት ደጋፊዎች ለ 1 ደቂቃ ያህል በማጨብጨብ ዘነበን ዘክረዋል።

የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታው እንቅስቃሴ የተዳከመ ሆኖ ጀምሮ የግብ ሙከራ ለማስተናገድ 11 ደቂቃዎች ወስደውበታል ። በዚህች አጋጣሚም ፍፁም ገ/ማርያም ኢብራሒም ፍፋኖ ከግራ መስመር የላከለትን ኳስ ከፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ሞክሮ ሀሪሰን አድኖበታል ። ኤሌክትሪኮች ከ አምስት ደቂቃዎች በኋላ ሌላ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ዳዊት ከማዕዘን ምት ባሻማው እና  ፍፁም በግንባሩ በሞከረው ኳስ አማካይነት ማድረግ ቢችሉም አሁንም ሀሪሰን አድኖባቸዋል ። ሳሙኤል ሳኑሚን ከፊት አድርገው አማካይ መስመር ላይ በብዛት በመገኘት በብዙ ኳስ ንክኪ ወደጎል የመድረስ ዕቅድ የነበራቸው ቡናዎች በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ ጥሩ የመከላከል ሽግግር አተገባበር  የነበራቸው ኤሌክትሪኮችን ሰብረው መግባትም ሆነ የግብ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም ። ቡናዎች ወደግብ መድረስ የቻሉባቸው አጋጣሚዎችም ይታዩ የነበረው የኤሌክትሪክ አማካዮች በአግባቡ ወደመከላከል ወረዳቸው መድረስ ባልቻሉባቸው አጋጣሚዎች ነበር ። ጨዋታው በኤሌክትሪኮች መጠናኛ የበላይነት ቀጥሎ 27ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ዳዊት እስጢፋኖስ ከቀኝ መስመር ያሻማውን የቅጣት ምት በጨዋታው ብዙ ሜዳ እያካለለ ጥሩ ሲንቀሳቀስ ያመሸው ተክሉ ታፈሰ በግንባር በማስቆጠር ክለቡን ቀዳሚ ማድረግ ቻለ ።

በህብረት በመከላከል እና ቶሎ ኳሶችን ለአጥቂዎች በማድረስ የተሻሉ የግብ ዕድሎችን ሲፈጥሩ የቆዩት ኤሌክትሪኮች ግብ ካስቆጠሩ በኋላ የቀደመ ጥንካሪያቸውን ማስቀጠል አልቻሉም ። የተክሉ ግብም የቡድኑ የመጀመሪያ አጋማሽ የመጨረሻ ጥቃት ነበረች ። በአንፃሩ ግቡ ቡናማዎችን ያነቃቃ ይመስል ነበር ። አቻ ሆነው ለእረፍት ባይወጡም በሳሙኤል ሳኑሚ በመሥዑድ መሀመድ እና አክሊሉ ዋለልኝ አማካይነት የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለው ነበር ። በተለይ የመስዑድ እና የአክሊሉ ሙከራዎች ቡድኑ በእጅጉ ለጎል የቀረበባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ ።

ከእረፍት መልስ ኢትዮጵያ ቡና አቡበከር ነስሩን እና ኢኮ ፌቨርን ቀይሮ በማስገባት ሁለተኛውን አጋማሽ በፈጣን ማጥቃት ነበር የጀመረው ።  የአቻነቷን ግብም በሳሙኤል ሳኑሚ ለማስቆጠር እስከ 48ኛው ደቂቃ ብቻ ነበር የጠበቁት ። ግቡም ኤሌክትሪኮች እንዳስቆጠሩባቸው ሁሉ ከቀኝ መስመር ከመስዑድ ቅጣት ምት ተነስቶ በሳሙኤል ሳኑሚ በግንባር ተገጭቶ የተቆጠረ ነበር። የጎሎቹ ተመሳሳይነትም የጨዋታው ለየት ያለ አጋጣሚ ሆኖ አልፏል ።

ከጎሉ በኋላ የነበረው የጨዋታ እንቅስቃሴ ግን እጅግ የተዳከመ እና ተመልካቹንም ያሰላቸ ነበር ። ጨዋታው በጥቂቱ ነፍስ ዘርቶበት የነበረው ከ 63ተኛው እስከ 68ኛው ደቂቃ ድረስ በነበረው እንቅስቃሴ ብቻ ነበር ። በ63 እና 67ኛው ደቂቃ ላይ ኢብራሂም ፍፋኖ ከዳዊት እና ከተክሉ ያገኛቸውን ግልፅ ዕድሎች ቢሞክርም የመጀመሪያውን ለማመን በሚከብድ መልኩ ከኢላማ ውጪ ሲልከው ሁለተኛውን ሀሪሰን አድኖበታል ። 68ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ኢትዮጵያ ቡናዎች በቀኝ በኩል በመስዑድ አማካይነት  የከፈቱትን ፈጣን መልሶ ማጥቃት ተከትሎ አብዱልከሪም ከመስመር ላይ ወደውስጥ የላከውን ኳስ ሳኑሚ አግኝቶ አክርሮ ሲመታ ኳሱ ሱሊማን አቡን በማለፍ የግቡን የውስጥ አግዳሚ ለትሞ መጥቷል ።

ኤሌክትሪኮች ምንም እንኳን በሊጉ ላለመውረድ እየታገሉ ቢሆንም ሙሉ ሶስት ነጥብ ለማግኘት የተሻለ ጥረት ሲያደርጉ ታይተዋል ። ሆኖም  ወደተጋጣሚ ሜዳ ይዘው የሚገቧቸውን ኳሶች በአግባቡ መቀባበል ባለመቻላቸው ያገኟቸውን የመልሶ ማጥቃት ዕድሎች ወደሙከራ ሳይቀይሩ ሲባክኑባቸው ታይቷል ። ኢትዮጵያ ቡናዎችም የጨዋታ ተነሳሽነታቸውን ጥያቄ ውስጥ በሚጥል መልኩ የማጥቃት ሂደታቸው ከመሀል ሜዳ የማያልፍ እና የተዳከመ ሆኖ ነበር ያመሸው ። ጨዋታውም በዚህ መልኩ ተጨማሪ ግብ ሳይስተናገድበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል ። በውጤቱም ኢትዮጵያ ቡና ነጥቡን 44 አድርሶ በነበረበት 4ኛ ደረጃ ላይ ሲረጋ ኤሌክትሪክ ባገኘው አንድ ነጥብ ነገ ጨዋታውን የሚያደርገውን ወላይታ ድቻን በግብ ክፍያ በመብለጥ ወደ 11ኛ ደረጃ ከፍ ብሏል ።

Leave a Reply