ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ |  ሽረ እንዳስላሴ እና ባህርዳር ከተማ ከመሪዎቹ ያለቸውን ልዩነት አጥብበዋል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ 22ኛ ሳምንት ጨዋታዎች እሁድ ሲደረጉ የምድቡ መሪ ወልዋሎ ተሸንፏል። መቀለ ከተማ ነጥብ ሲጥል ሽረ እንዳስላሴ እና ባህርዳር ከተማ ተጋጣሚዎቻቸውን በመርታት ከመሪዎቹ ያላቸውን ርቀት ማጥብ ችለዋል፡፡

ለገጣፎ ላይ ለገጣፎን ለገዳዲ የምድቡ መሪ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲን አስተናግዶ 1-0 ማሸነፍ ችሏል፡፡ ጨዋታው ከፍተኛ ግምትና አትኮሮት የተሰጠው ሲሆን የፌዴሬሽኑ የስራ ኃላፊዎችም የተከታተሉት ጨዋታ ነበር፡፡

ጨዋታው በተጀመረ በ6ኛው ደቂቃ ላይ የወልዋሎው ቴዎድሮስ መንገሻ እንግዳውን ቡድን ቀዳሚ የምታደርግ እድል ቢያገኝም ሳይጠቀምባት ቀረ እንጂ የጨዋታው መልክ ሊቀይር የሚችል አጋጣሚ ነበር፡፡ ከሁለት ደቂቃ በኋላ በተመሳሳይ ሳዲቅ ተማም ለገጣፎን መሪ ማድረግ የሚችልበትን አጋጣሚ ቢያገኝም ሳይጠቅምበት ቀርቶል፡፡

በመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃ ተጭነው ሲጫወቱ የነበሩት ለገጣፎ ለገዳዲዎች በ16ኛው ደቂቃ ላይ የወልዋሎ አፈወርቅ ኃይሉ በመልሶ ማጥቃት የመጣችውን ኳስ በእጁ በማስቀረቱ የተገኘውን ቅጣት ምት አስናቀ ተስፋዬ በረጅሙ ያሻምቶ መሀመድ ሻፊ በግንባሩ ገጭቶ ወደጎልነት መለወጥ ችሏል፡፡

በጉሉ መቆጠር የተደናገጡ የሚመስሉት የብርሃኔ ገብረግዛብሄር ተጨዋቾች በተደጋጋሚ ስህተት ሲሰሩ ተስተውሏል፡፡ ይህንንም ተተቅመው አጥቂዎች ሳዲቅ ተማም እና ልደቱ ለማ ጫና ፈጥረው እንዲንቀሳቀሱ ነፃነት ሰጥቷቸዋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ተረጋግው እና መሻሻል አሳይተው ወደ ሜዳ የገቡት ወልዋሎዎች የተሻለ የኳስ ፍሰት እና እንቅስቃሴ ያሳዩ ሲሆን በተቃራኒው ለገጣፎዎች ተጠቅጥቆ በመጫወት ውጤታቸውን ማስጠበቅ ችለዋል፡፡ ወልዋሎዎች በተደጋጋሚ የለገጣፎ ለገዳዲ ግብ ክልል በመድረስ በከድር ሳህለና በመኩሪያ ደሱ አማካኝነት ሙከራዎች ማድረግ ቢችሉም ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ጨዋታው በለገጣፎ ለገዳዲ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ዘንድሮ ወደ ከፍተኛ ሊጉ ያደገው ለገጣፎ ለገዳዲ በሜዳው የማይቀመስ ሆኗል፡፡ የያሬድ ቶሌራው ቡድን በተለይ በምድቡ አናት ላይ የሚገኙትን ሁሉም ክለቦች በሜዳው በማሸነፍ ጠንካራነቱን ማሳየት ችሏል፡፡

መቐለ ከተማ ወደ ደብረብርሃን ተጉዞ ከሰሜን ሸዋ ደብር ብርሃን 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይቶ የምድቡን መሪነት የመረከብ እድሉን አምክኗል፡፡ የምድቡ ግርጌ ላይ የሚገኘው ሰሜንሸዋ ደብር ብርሃን በጨዋታው መሆን የቻለበትን ግብ በሮቤል ጥላሁን አማካይነት በ18ኛው ደቂቃ ሲያስቆጥር አማኑኤል ገ/ሚካኤል በ38ኛው ደቂቃ መቐለን አቻ ያደረገች ግብ አስቆጥሯል፡፡ መቐለ ከተማ ከውድድር ዘመኑ መጀመርያ አንስቶ ወልዋሎን በቅርብ ርቀት እየተከተለ ቢገኝም መሪ የሚሆንባቸውን ተደጋጋሚ አጋጣሚዎች መጠቀም ሳይችል መቅረቱ አስገራሚ ሆኗል፡፡

የዘንድሮው አስደናቂ ቡድን ሽረ እንዳስላሴ አዲስ አበባ ፖሊስን አስተናግዶ 1-0 በማሸነፍ መሪዎቹን ተጠግቷል፡፡ የመጀመርያው አጋማሽ ጎል ያልተስተናገደበት ሲሆን ከዕረፍት መልስ ጫና ፈትረው የተጫወቱት ሽረዎች በ58 ደቂቃ ቢንያም ደባሳይ ባስቆጠራት ግብ አሸንፈው መውጣት ችለዋል፡፡ ዘንድሮ ወደ ከፍተኛ ሊግ ያደጉት የዳንኤል ጸሃዬ ሽረዎች ነጥባቸውን 38 በማድረስ ከመሪው ወልዋሎ ያላቸውን ልዩነት ወደ 6 ያጠበቡ ሲሆን የ8 ሳምንታት ጨዋታዎች ከመቅረታቸው እና ወጥ እቋም እያሳዩ ከመሆናቸው አንፃር ወደ ፕሪምየር ሊግ የመግባት ተስፋ አሁንም አላቸው፡፡

ባህርዳር ላይ ባህርዳር ከተማ ከተከታታይ የአቻ ውጤቶች በኋላ ወደ ድል የተመለሰበትን ውጤት ቡራዩ ከተማን አስተናግዶ 1-0 በማሸነፍ አስመዝግቧል፡፡ በውድድር ዘመኑ አጋማሽ ባህርዳርን የተቀላቀለው ኤርምያስ ዳንኤል በ30ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ግብ ባህርዳር ከተማን አሸናፊ ማድረግ ችላለች፡፡ በሁለተኛው ዙር የተዳከመው ባህርዳር ድሉን ተከትሎ ከመሪው ወልዋሎ ያለውን ልዩነት ወደ 8 ማጥበብ ችሏል፡፡

ባህርዳር ላይ ቀጥሎ በተካሄደው የአማራ ውሃ ስራ እና ወሎ ኮምቦልቻ  ጨዋታ አማራ ውሃ ስራ 1-0 በሆነ ውጤት አሸንፏል፡፡ ከዕረፍት በፊት 45ኛው ደቂቃ የቀድሞው የወልድያ ግብ አዳኝ ዕዮብ ወ/ማርያም የአማራ ውሃ ስራን ብቸኛ የድል ጎል አስቆጥሯል፡፡ አክሱም ላይ ሱሉልታ ከተማን ያስተናገደው አክሱም ከተማ በተመሳሳይ 1-0 ማሸነፍ ችሏል፡፡ የአክሱም ከተማን ብቸኛ የማሸነፍያ ጎል ክብሮም አፅብሀ በ65ኛው ደቂቃ አስቆጥሯል፡፡

በሱሉልታው ያያ ሪዞርት ሜዳ ላይ የተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል፡፡ ኢትዮ ውሃ ስፖርት ከ ኢትዮጵያ መድን 1-1 በተለያዩበት ጨዋታ ክብረዓብ ማቱሳላ በፍፁም ቅጣት ምት ውሃ ስፖርትን ቀዳሚ ቢያደርግም ደሳለኝ ባዬ በ90 2ኛው ደቂቃ ላይ ኢትዮጵያ መድንን ከሽንፈት የታደገች ጎል አስቆጥሯል፡፡ ከዚህ ጨዋታ ቀደም ብሎ የተከናወነው የአራዳ ክፍለ ከተማ እና ሰበታ ከተማ ጨዋታ ያለግብ በአቻ ውጤት ሲጠናቀቅ በሳምንቱ በምድብ ሀ ያለግብ የተጠናቀቀ ብቸኛ ጨዋታም ሆኗል፡፡

ምስጋና

በክፍተኛ ሊጉ የተመረጡ ጨዋታዎችን በተለያዩ ስፍራዎች በመጓዝ ሽፋን የምትሰጠው ሶከር ኢትዮጵያ በዚህ ሳምንት ወደ ለገጣፎ አምርታ የለገጣፎ ለገዳዲ እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲን ጨዋታ ለመከታተል ወደ ስፍራው ባመራችበት ወቅት የለገጣፎ ክለብ አባላት እና የከተማው ህዝብ ላደረገላት መልካም አቀባበል እና መስተንግዶ ሶከር ኢትዮጵያ ከፍ ያለ ምስጋና ታቀርባለች፡፡ 

1 Comment

Leave a Reply