ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ |  ጅማ ከተማ መሪነቱን ያጠናከረበትን ድል ሀዲያ ሆሳዕና ላይ ሲያስመዘግብ ሀላባ እና ሻሸመኔ ነጥብ ጥለዋል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 22ኛ ሳምንት የምድብ ለ ጨዋታዎች እሁድ በተለያዩ የክልል ከተሞች ሲደረጉ ጅማ ከተማ መሪነቱን ለብቻው የያዘበትን ውጤት አስመዝግቧል፡፡ ተከታዮቹ ሀላባ ከተማ ፣ ሀዲያ ሆሳዕና እና ሻሸመኔ ተከተማ ነጥብ ሲጥሉ ዲላ ከተማ በአስፈሪ ግስጋሴው ቀጥሏል፡፡

ሀዋሳ ላይ ከወጣለት መርሀ ግብር ቀደም ብሎ 05፡00 ላይ የተካሄደው የደቡብ ፖሊስ እና ዲላ ከተማ ጨዋታ በእንግዳው 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ የኋላሸት ሰለሞን ዲላ ከተማን በ9ኛው ደቂቃ ቀዳሚ የሚያደርገውን ጎል ሲያስቆጥር ደቡብ ፖሊስ በደስታ ግቻሞ የ18 ደቂቃ አቻ ሆነዋል፡፡ በ44ኛው ደቂቃ ደግሞ አገኘው ልኬሳ ደቡብ ፖሊስ ወደ መሪነት አሸጋግሮ በደቡብ ፖሊስ መሪነት የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቋል፡፡ ከዕረፍት መልስ ጫና ፈጥረው የተጫወቱት ዲላዋች በ62ኛው ደቂቃ በዳዊት ከበደ ጎል አቻ ሲሆኑ በ78ኛው ደቂቃ የኋላሸት ሰለሞን ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ደግሞ ወሳኟን የማሸነፊያ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በዲላ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

የደቡብ ፖሊስ ክለብ አመራሮች በመርሃ ግብር ለውጡ ደስተኛ አለመሆናቸውን ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል፡፡ በለውጡ ምክንያት ጨዋታውን ያለ ደጋፊ በመጫወታቸው የሜዳ አድቫንቴጅ እንዳይጠቀሙ እክል እንደፈጠረባቸውም ቅሬቸወን አሰምተዋል፡፡

በመጀመርያው ዙር ደካማ አጀማመር ያደረገው ዲላ ከተማ በሁለተኛው ዙር ከፍተና መሻሻል በማሳየት መሪዎቹን በአስገራሚ ፍጥነት እየተጠጋ ይገኛል፡፡ ዘንድሮ ወደ ከፍተኛ ሊጉ ያደገው ዲላ ከተማ ድሉን ተከትሎ ነጥቡን ወደ 34 ከፍ በማድረግ ከመሪው ጅማ ያለውን ልዩነት 5 አድርሷል፡፡

የምድቡን መሪነት በጎል ልዩነት ከሀላባ እና ሀዲያ ሆሳዕና ጋር ሲመራ የበረው ጅማ ከተማ በሜዳው የደረጃ ተፎካካሪው ሀድያ ሆሳዕናን አስተናግዶ 2-1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ መሪነቱን ለብቻው መያዝ ችሏል፡፡ የ6 ነጥቦች ቅነሳው የተነሳለት ሀድያ ሆሳዕና በ22ኛው ደቂቃ በአሚኑ ነስሩ የቅጣት ምት ጎል ቀዳሚ ሲሆን ለዕረፍት በፊት ከመውጣታቸው በፊት ተመስገን ገብረኪዳን በተመሳሳይ ከቅጣት ምት ለጅማ ከተማ አስቆጥሮ አቻ ሆነዋል፡፡ ከዕረፍት መልስ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጥሩ እንቅስቃሴ የታየ ሲሆን በ68ኛው ደቂቃ ተመስገን ገ/ኪዳን  ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ የማሸነፊያዋን ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በጅማ ከተማ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ወደ አርሴ ነገሌ የተጓዘው ሀላባ ከተማ በአቻ ውጤት ጨዋታውን አጠናቋል፡፡ ሀላባ ከተማ ቴዎድሮስ ወልዴ በ12ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ጎል ቀዳሚ ሲሆን በ40ኛው ደቂቃ ወንድወሰን ዳኜ ባለሜዳዎቹ ነጥብ ተጋርተው የወጡበትን ጎል አስቆጥሯል፡፡

ወልቂጤ ከተማ ነቀምት ከተማን አስተናግዶ 3-0 በሆነ ውጤት አሸናፎ ወደ ድል ተመልሷል፡፡ የወልቂጢ ከተማን የድል ጎሎች ብስራት ገበየው በ10ኛው ፣ ሚካኤል ወ/ሩፋኤል በ67ኛው ደቂቃ እንዲሁም ብሩክ በየነ በ76ኛው ደቂቃ አስቆጥረዋል፡፡ በጨዋታው መሀል ላይ የጣለው ዝናብ የጨዋታውን እንቅስቃሴ ከባድ አድርጎት ተስተውሏል፡፡

ነገሌ ቦረና ፌደራል ፖሊስን አስተናግዶ 1-0 በሆነ ውጤት አሸንፏል፡፡ እስማኤል ሬድዋን በ78ኛው ደቂቃ ላይ ብቸኛዋን የድል ጎል አስቆጥሯል፡፡ ወራቤ ላይም በተመሳሳይ ስልጤ ወራቤ ሻሸመኔ ከተማን አስተናግዶ 1-0 በሆነ ውጤት አሸንፏል፡፡

ድሬዳዋ እሁድን በግብ ተንበሻብሻ አሳልፋለች፡፡ 08፡00 ላይ ካፋ ቡናን ያስተናገደው ድሬዳዋ ፖሊስ 3-1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል፡፡ ገና ጨዋታው በተጀመረ በ5ኛው ደቂቃ አማኑኤል አዳነ ካፋ ቡናን ቀዳሚ ቢያደርግም ዕዩኤል ሳሙኤል በ15ኛው እና 67ኛው እንዲሁም ዘርዓይ ገ/ስላሴ በ18ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠሯቸው ጎሎች ድሬዳዋ ፖሊስ 3-1 ማሸነፍ ችሏል፡፡

ቀጥሎ 10፡00 ላይ በተካሄደው የናሽናል ሴሜንት እና ጂንካ ከተማ ጨዋታ ናሽናል ሴሜንት ግማስ ደርዘን ግብ ጂንካ ላይ በማዝነብ 6-0 አሸንፏል፡፡ ዳንኤል ሰለሞን እና ፈርዓ ሰኢድ ሁለት ሁለት ጎሎችን በስማቸው ሲያስመዘግቡ መሀመድ ጀማል እና ፍፁም ቀሪዎቹን ጎሎች አስቆጥሮዋል፡፡

Leave a Reply