አፍሪካ | ክዌሲ ናያታቺ እና ኮንስታንት ኦማሪ የካፍ ምክትል ፕሬዝደንቶች ሆነው ተሾሙ 

የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌድሬሽን (ካፍ) ዛሬ ጠዋት በባህሬን ዋና መዲና ማናማ ባደረገው የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ስብሰባ ላይ ሁለት አዲስ ምክንትል ፕሬዝደንቶችን ሹመት አፅድቋል፡፡

በማናማ አዲሱ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ለመጀመሪያ ግዜ ስብሰባ የተቀመጠ ሲሆን በአዲስ አበባ በነበረው የመጨረሻ ስብሰባ ላይ የነሱ አጀንዳዎችን ጨምሮ ሌሎች ጉዳዮች ላይ መክሯል፡፡ ከዚህም ባሻገር የአዲሱ ፕሬዝደንት አህመድ አህመድ ረዳት ሆነው የሚሰሩ ሁለት ምክትል ፕሬዝደንቶች መርጧል፡፡ የጋናው እግርኳስ ማህበር ፕሬዝደነት ክዌሲ ናያታቺ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝደንት ሲሆኑ የዲ.ሪ. ኮንጎ እግርኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝደንት ኮንስታንት ኦማሪ ምክትል ፕሬዝደንት ሆነዋል፡፡

የቀድሞን ፕሬዝደንት ኢሳ ሃያቱ የ29 ዓመት የስልጣን ዘመን እንዲያበቃ አህመድን በከፍተኛ መልኩ ያገዙት ክዌሲ እና የኦማሪ ሹመት የሚጠበቅ ነበር፡፡ ሁለቱ ቁልፍ የአህመድ ደጋፊዎች ለፕሬዝደንቱ ድምፅ እንዲያገኙ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩ ናቸው፡፡ በአህመድ ደጋፊዎች በተጠቀለቀው የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሁለቱ የእግርኳስ ባለስልጣናት የመጀመሪያ ድጋፋቸውን ለአህመድ በመስጠታቸውም ይታወቃሉ፡፡ ክዌሲ እና ኦማሪ ለቀጣዮቹ አራት አመታት አህመድን በማገዝ እንደሚሰሩ ታውቋል፡፡ በስራቸው የህግ አማካሪ የሆኑት ክዌሲ ለ10 አመታት የካፍ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ሆነው አገልግለዋል፡፡ አሁን ላይ ደግሞ ከስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልነታቸው ባሻገር የፊፋ ካውንስል አባል ናቸው፡፡

ከወራት በፊት የሞሮኮ ሚዲያዎች የሞሮኮ እግርኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝደንት የሆኑት ፋውዚ ሌካ ተቀዳሚ ፕሬዝደነት ይሆናሉ የሚል ዘገባዎች ማሰራጨታቸው ይታወሳል፡፡

Leave a Reply