የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቀጣይ 3 መርሀ ግብሮች ላይ ለውጥ ማድረጉን ዛሬ ካዛንቺስ በሚገኘው የፌዴሬሽኑ ፅህፈት ቤት በጠራው ድንገተኛ ጋዜጣዊ መግለጫ ገልጿል፡፡ ውጤትን አላግባብ ለማግኘት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠር መዘጋጀቱንም አስታውቋል፡፡
09:00 ላይ በተጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ በፌዴሬሽኑ የተለያየ ሀላፊነት ላይ የሚገኙት አቶ አበበ ገላጋይ ፣ አቶ አሊሚራህ መሀመድ ፣ ዶ/ር ነስረዲን አህመድ እና አቶ ሰለሞን ገብረስላሴ የተገኙ ሲሆን የመግለጫው ዋና አጀንዳ የነበረው በቀሪዎቹ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 3 ሳምንታት መርሀ ግብሮች ለዋንጫ እና ላለመውረድ የሚፎካከሩ ክለቦች ሚዛናዊ በሆነ ሁኔታ ጨዋታዎቻቸውን እንዲያደርጉ በማሰብ በተመሳሳይ ሰአት እንዲደረጉ ተወስኗል፡፡
በዚህም መሰረት ግንቦት 4 ሊካሄድ የነበረው የ28ኛ ሳምንት መርሀ ግብር ወደ ግንቦት 10 የተሸጋገረ ሲሆን በዋንጫ እና ላለመውረድ በሚደረገው ፉክክር ውስጥ የሚገኙ ክለቦች የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች በተመሳሳይ ሰአት የሚካሄዱ ይሆናል፡፡ የ29ኛ እና 30ኛው ሳምንት ጨዋታዎችም በተመሳሳይ መልኩ እንደሚደረጉ ተገልጿል፡፡
ፌዴሬሽኑ በመግለጫው የፉክክር ሚዛኑን ያዛባሉ ተብለው በሚጠረጠሩ ጨዋታዎች ላይ ከፍተኛ ክትትል ለማድረግ መዘጋጀቱን እና ጨዋታዎቹን በካሜራ እንደሚያስቀርጽ ጨምሮ ገልጿል፡፡ ውጤትን አግባብ ባልሆነ መንገድ ለማግኘት ሲንቀሳቀሱ በሚገኙ ክለቦች ፣ ተጫዋቾች ፣ አሰልጣኞች እና አመራሮች ላይም ጠበቅ ያለ እርምጃ ይወሰዳል ተብሏል፡፡