የጨዋታ ሪፖርት | ወላይታ ድቻ ከወራጅ ቀጠናው የሚርቅበትን እድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል

 

በ27ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ ጨዋታ ዛሬ አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ሲደረግ አዲስ አበባ ከተማ ወላይታ ድቻን አስተናግዶ ያለግብ አቻ ተለያይቷል፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ዘንድሮ የተቀላቀለውን ፕሪምየር ሊግ ለመሰናበት ከጫፍ የደረሰ ሲሆን ወላይታ ድቻ ከወራጅ ቀጠና የሚያመልጥበትን ወርቃማ እድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡

አዲስ አበባ ከተማ ሃይሌ እሸቱን እና ፍቃዱ አለሙን በፊት አጥቂነት እንዲሁም ኤፍሬም ቀሬን በአጥቂ አማካይነት አሰልፎ ወደ ሜዳ ሲገባ ድቻ ዳግም በቀለን በፊት አጥቂነት አሰልፎ ጨዋታውን ጀምሯል፡፡

በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ክለቦች በአጭሩ የሚቆረጥ የኳስ ቅብብሎች እና ሳቢ ያልሆነ የኳስ ፍሰት ታይቶበታል፡፡ ይህንን አጋማሽ ይበልጥ አሰልቺ ያደረገው የጠሩ የግብ ማግባት እድሎችን እና ሙከራዎችን ሁለቱም ቡድኖች ሲፈጥሩ አለመታየቱ ነበር፡፡ በተለይ ባለሜዳው አዲስ አበባ ከተማ በዚህኛው የጨዋታ ክፍለ ግዜ ኢላማውን የጠበቀ አንድም ሙከራ ማድረግ አልቻለም፡፡ በአንፃሩ ድቻውች በ6ኛው ደቂቃ አማካዩ ዮሴፍ ደንገቱ በግንባሩ የገጨውን ኳስ ደረጄ አለሙ በ6ኛው ደቂቃ የያዘበት እንዲሁም በ30ኛው ደቂቃ ከማዕዘን የተሻገረውን አሁንም ዮሴፍ ገጭቶ ወደ ውጪ የወጣበት ሙከራዎች በድቻ በኩል ይጠቃሳል፡፡ በዛብህ መለዮ በመመሪያው አጋማሽ ግብ ቢያስቆጥርም ከጨዋታ ውጪ በማለት የእለቱ አርቢትር ጨዋታውን አስቀጥለዋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ክለቦች የተሻለ ፉክክር እና በርካታ የግብ ሙከራዎችን አሳይተዋል፡፡ በተለይ ከሶዶ በመጡ ደጋፊዎቻቸው ድጋፍ ታጅበው የተጫወቱት ድቻዎች በተደጋጋሚ የፈጠሯቸውን የግብ እድሎች መጠቀም ሲቸገሩ ተስተውሏል፡፡ በ67ኛው ደቂቃ በሳጥኑ ውስጥ የነበረው ዳግም ያገኘውን ግልፅ የማግባት እድል ኳስ በግቡ አናት በመስደዱ ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡ ከሁለት ደቂቃ በኃላ በሌላኛው የግብ ክልል አሊ አያና በግሩም ሁኔታ በቮሊ የመታውን ጠንካራ ኳስ ወንድወሰን ገረመው አምክኖበታል፡፡ ዳዊት ማሞ በ70ኛው ደቂቃ የመታውን ኳስ አሁንም ወንድወሰን ይዞበታል፡፡  በ72ኛው ደቂቃ የቀኝ መስመር ተከላካዩ ፈቱዲን ጀማል የሞከረው ኳስ የግቡ ቋሚ ሲመልስበት ከስድስት ደቂቃዎች በኃላም እንዲሁ የመታው ኳስ የግብ አግዳሚ መልሶበታል፡፡ የጨዋታው መገባደጃ ላይ በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው አላዛር ፋሲካ በግንባሩ የገጨው ኳስ ወደ ውጪ ሲወጣ አዲስ አበባን ሙሉ ሶስት ነጥብ ልታስገኝ የነበረች እድል አቤል ዘውዱ አግኝቶ ወንድወሰን አምክኖበት ጨዋታው ያለምንም ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቅቋል፡፡

ውጤቱን ተከትሎ ወላይታ ድቻ በ30 ነጥብ ደረጃውን ወደ 11ኛ ሲያሳድግ ለመውረድ እጅግ በጣም የቀረበው አዲስ አበባ ከተማ በ20 ነጥብ የሊጉን ግርጌ ይዞ ይገኛል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *