” በአስቸጋሪ እና አስጨናቂ ህይወት ውስጥ ነው የምገኘው” በረከት አዲሱ

የሲዳማ ቡናው አጥቂ በረከት አዲሱ የዲሲፕሊን ጥሰት ፈጽሟል በሚል በክለቡ የ2 አመት እገዳ እንደተጣለበት የሚታወስ ነው፡፡ በእገዳው ምክንያት ላለፉት 3 ወራት ከእግርኳስ የራቀው በረከት አዲሱ የህይወቱን ከባድ ጊዜ እያሳለፈ እንደሆነ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረገው ቆይታ ገልጿል፡፡

በረከት በጉዳዩ ዙርያ የሰጠውን አስተያየት እንዲህ አቅርበነዋል፡፡

ሲዳማ ቡና ከፍተኛ የሆነ ቅጣት የጣለብህ ምክንያት ምንድን ነበር ?

በወቅቱ አዕምሮዬ ጥሩ አልነበረም፡፡ ለክለቡ ምንም አገልግሎት የማልሰጥበት ሁኔታ ነበር የተፈጠረው። በትዳር ህይወቴ ችግር ውስጥ ነበርኩኝ። የተፈጠረው ነገር ፈፅሞ መቋቋም የማልችልበት ሁኔታ ነበር የተፈጠረው። ከጎኔ የነበሩት ተጨዋቾች እና የክለቡ አመራሮችም በወቅቱ የተፈጠረብኝ ነገር ያውቁ እና ይረዱኝ ነበር ። ያው በተፈጠረውም ነገር ክለቡ እንደሚታውቀው ከባድ የሆነ ቅጣት አስተላልፈውብኛል። ይሄም ቢሆን ክለቡ በወቅቱ የተፈጠረውን ነገር ሊረዳኝ ይገባ ነበር።

ቅጣቱ የፈጠረብህ ተፅዕኖ ምነድነው?

በጣም ከባድ ሁኔታ ላይ ነው የምገኘው። ቅጣቱ ዱብ እዳ ነው የሆነብኝ ብዙ ነገር ነው የተጎዳሁት፡፡ አስቸጋሪ እና አስጨናቂ ህይወት ውስጥ ነው የምገኘው፡፡ ከቤት አልወጣም ፤ እቤት ውስጥ ነው ተቀምጬ ያለሁት፡፡ መንገድም መሄድ የማልችልበት ነገር ነው ያለው፡፡ ስሜቴ ተጎድቷል፡፡ እግር ኳስ ደስታዬ ነው ፤ ደስታዬን ነው የነጠቁኝ፡፡ በዚህም አእምሮዬም እየተጎዳ ነው። እንዲህ ብዬ መግለፅ የማልችለው ነገሮች እየደረሰብኝ እገኛለው፡፡ ለኢትዮዽያ እግር ኳስ የለፋው ሰው ነኝ፡፡ ለሲዳማ ቡናም ቢሆን ጉልበቴን ሳልቆጥብ ተጫውቻለው፡፡ ሊረዱኝ ይገባል፡፡

ሲዳማ ቡና እንዲረዳህ ያቀረብከው ጥያቄ አለ ?

አዎ ደብዳቤ አሰገብቻለው፡፡ ሰው ነን ፤ በህይወት ስንኖር ስህተቶችን ልንሰራ እንችላለን፡፡ ስንጫወትም እንደዛው ስህተቶች እንሰራለን። በጣም ከባድ የሆነ ጥፉት ያጠፉ ተጨዋቾች እናውቃለን ፤ ብዙ አሉ፡፡ ማንም ኢትዮዽያዊ ተጨዋች እንዲህ ተደርጎ አያቅም ፤ ይህ ኢ-ሰብአዊነት ነው። እስካሁን ምንም አይነት መልስ ሊሰጡኝም አልቻሉም። ያቀረብኩት ቅጣቱ ይነሳልኝ የጥያቄ ደብዳቤ በቦርድ ነው የሚታየው ብለው እየጠበቅኩ ነው። አሁን ያለሁበትን ሁኔታ ተረድተው ቅጣቱን እንዲያነሱልኝ እጠይቃለው።

በዚህ ጉዳይ ላይ የሲዳማ ቡና ስፖርት ክለብ የሚሰጠውን ምላሽ የክለቡን አመራሮች አናግረን ይዘን የምንቀርብ መሆናችንን እንገልጻለን፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *