ኢትዮጵያ ቡና አሰልጣኝ ገዛኸኝ ከተማን ከዋና አሰልጣኝነት አንስቶ እድሉ ደረጀን በዋና አሰልጣኝነት መሾሙን በይፋዊ የፌስቡክ ገፁ አስታውቋል፡፡
” የዋናው ቡድን ውጤት መውረድን ተከትሎ በተደረገ ግምገማ አቶ እድሉ ደረጀ በግዜያዊ ዋና አሰልጣኝነት እንዲሁም የተስፋ ቡድን ዋና አሰልጣኝ የነበሩት አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ በጊዜያዊ ምክትል አሰልጣኝነት ቡድኑን እንዲያሰለጥኑ ተረክበዋል፡፡ ” ሲል ክለቡ በፌስቡክ ገፁ ገልጿል፡፡
ለረጅም አመታት በኢትዮጵያ ቡና የተለያዩ የአሰልጣኝነት ኃላፊነቶች የሰሩት አሰልጣኝ ገዛኸኝ ከተማ ከክለቡ ይሰናበቱ አልያም ወደ ሌሎች ስራዎች ይሸጋሸጉ ክለቡ የገለጸው ነገር የለም፡፡
አሰልጣኝ ገዛኸኝ ከተማ በጥር ወር የተሰናበቱት አሰልጣኝ ኒቦሳ ቪቼቪችን ተክተው የክለቡ አሰልጣኘነትን ከተረከቡ ወዲህ ክለቡ ከመጥፎ አጀማመሩ ማገገም ቢችልም በቅርብ ጨዋታዎች የውጤት መዋዠቅ ታይቶበታል፡፡
ቀጣዮቹን የፕሪምየር ሊግ እና የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች በጊዜያዊነት የመምራት ኃላፊነት የተጣለበት የቀድሞው የቡድኑ አምበል እድሉ ደረጄ ዘንድሮ በ20 አመት በታች ቡድነኑ አሰልጣኝነት ጀምሮ ወደ የአሰልጣኝ ኒቦሳ ቪቼቪችን ስንብት ተከትሎ የአሰልጣኝ ገዛኸኝ ረዳት በመሆን ዋናውን ቡድን ተቀላቅሏል፡፡ አሁን ደግሞ በዋና አስልጣኝነት እስከ ውድድር ዘመኑ መጨረሻ ክለቡን የሚመራ ይሆናል፡፡
በዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በርካታ ክለቦች የአሰልጣኝ ለውጥ ያረጉ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡና ከደደቢት በመቀጠል በውድድር ዘመኑ ሁለት ጊዜ የአሰልጣኝ ለውጥ ያደረገ ክለብ ሆኗል፡፡