ቻምፒየንስ ሊግ | የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታዎች ዛሬ ይጀምራሉ

በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ወደ ምድብ ያለፉ ቡድኖች ከዛሬ ጀንሮ የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ሲሆን ዛሬ ምሽት 6 ጨዋታዎች የሚካሄዱ ይሆናል፡፡

ምድብ ሀ

የቱኒዚያው ኤቷል ደ ሳህል በሜዳው ፎሬቫያሪዮ ደ ቤይራን ያስተናግዳል፡፡ የሞዛምቢኩ ክለብ በቻምፒየንስ ሊግ የምድብ ጨዋታው ሲካፈል ይህ የመጀመሪያው ሲሆን ሰፊ እና የካበተ የአፍሪካ ክለቦች ውድድር ልምድ ያለው የሰሜን አፍሪካ ተጋጣሚውን የመርታት እድሉ ዝቅተኛ እንደሆነ እየተነገረ ይገኛል፡፡ ኤቷል አምና ያሳካውን የቱኒዚያው ሊግን አሁንም ለመድገም ከመዲናዋ ቱኒዝ ክለብ ኤስፔራንስ ጋር ተፋጧል፡፡

በምድቡ ሌላኛው እና ተጠባቂ ጨዋታ ሁለቱ የሱዳን ሃያላን ሲያገናኝ በኦምዱሩማን ደርቢ አል ሂላል የምንግዜም ተቀናቃኙን ኤል ሜሪክን ያስተናግዳል፡፡ ከዚህ ቀደም ከአመታት በፊት በኮንፌድሬሽን ዋንጫ በአንድ ምድብ ውስጥ የተገኙት ሁለቱ ክለቦች አሁን ላይ ዳግም በቻምፒየንስ ሊግ ተገናኝተዋል፡፡ አል ሂላል የሱዳን ፕሪምየር ሊግን በ30 ነጥቦች ሲመራ ሜሪክ ሁለት ጨዋታዎች እየቀሩት በ10 ነጥብ ዝቅ ብሎ ሁለተኛ ነው፡፡ ጨዋታውን የማሸነፍ ቅድመ ግምት ለባለሜዳው ሂላል ተሰቷል፡፡

ምድብ ለ

የ2016 የፍፃሜ ተፋላሚ ዛማሌክ እያሳለፈ የሚገኘውን አስከፊ የሊግ ውድድር ዘመን ለመርሳት ከ2002 በኃላ ያጣውን የአፍሪካ ቻምፒዮንነት ክብር ለማግኘት ዛሬ ምሽት የዚምባቡዌው ካፕስ ዩናይትድ በሜዳው በመግጠም ይጀምራል፡፡ ካፕስ ዩናይትድ ቲፒ ማዜምቤን ረቶ ወደ ምድብ መግባት የቻለ ሲሆን ለዛማሌክም ፈተና እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ ቢሆንም ክለቡ የምድብ ጨዋታዎች ልምድ የሌለው መሆኑ አሉታዊ ጎን አለው፡፡

አሃሊ ትሪፖሊ ወደ አልጀርስ አቅንቶ ዩኤምኤስ አልጀርን ይገጥማል፡፡ በሊቢያ ባለው ያለመረጋጋት ምክንያት አሃሊ ትሪፖሊ ተፅእኖ ውስጥ ገብቷል፡፡ ክለቡ ምንምእንኳን የሊቢያ እግርኳስን ሙሉ ለሙሉ ቢቆጣጠርም በአፍሪካ መድረክ በቅርብ ግዜያት ከምድብ ማለፍ ሲሳነው ታይቷል፡፡ የአምናው የአልጄሪያ ቻምፒዮን እና የ2015 የቻምፒየንስ ሊግ የፍፃሜ ተፋላሚ ዩኤምኤስ አልጀር በአልጄሪያ ሊግ ከመሪው ኢኤስ ሴቲፍ በ7 ነጥቦች ርቆ በ40 ነጥብ አራተኛ ነው፡፡

ምድብ ሐ

የምድቡ አንድ ጨዋታ ዛሬ ምሽት ቱኒዝ ላይ ይደረጋል፡፡ ኤስፔራንስ ኤኤስ ቪታ ክለብን ያስተናግዳል፡፡ ቪታ ክለብ ባሳለፍነው ሳምንት በሊናፉት ጨዋታ ሃያሉን ቲፒ ማዜምቤን መርታት የቻለ ሲሆን ለኤስፔራንስም ከባድ ፈተና እንደሚሆን ይታመናል፡፡ ኤስፔራንስ የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ከኤቷል ደ ሳህል ጋር ተናንቋል፡፡ ኤስፔራንስ ባሳለፍነው ሳምንት ሴፋክሲየንን 1-0 መርታት የቻለ ሲሆን የቱኒዚያ ሊግንም እየመራ ቪታን ይገጥማል፡፡

የምድቡ ሁለተኛው ጨዋታ የኢትዮጵያው ብቸኛ ተወካይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ፕሪቶሪያ አቅንቶ የወቅቱ ቻምፒዮን ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ቅዳሜ በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር 12፡00 ይገጥማል፡፡

ምድብ መ

ዋይዳድ ካዛብላንካ በሜዳው የካሜሮኑን ኮተን ስፖርት ይገጥማል፡፡ ኮተን ስፖርት ከዓመታት ቆይታ በኃላ ወደ ምድብ ተመልሶ የሚጫወት ሲሆን ዋይዳድ አምና በተመሳሳይ ውድድር እስከ ፍፃሜ ግማሽ መድረሱ ይታወሳል፡፡ ዋይዳድ በቅርብ ሳምንታት በቦቶላ ሊግ እያሳየ በሚገኘው ጥንካሬ በአፍሪካ መድረክ ማዝለቅ ከቻለ ረጅም ርቀት መጓዝ ይችላል፡፡ ኮተን ስፖርት በካሜሮን ኤምቲኤን ኢሊቲ አንድ በ21 ነጥብ ከመሪው በአምስት ነጥብ ዝቅ ብሎ አራተኛ ነው፡፡

ባለሪከርድ የአፍሪካ ቻምፒዮኑ አል አህሊ ቅዳሜ የዛምቢያውን ዛናኮን ይገጥማል፡፡ አህሊ አምና ከምድብ ተሰናብቷል፡፡ የ2012 ቻምፒየንስ ሊግ ከክለቡ ጋር ያነሱትን አሰልጣኝ ሆስኒ ኤል ባድሪን የመለሰው አሃሊ በዘንድሮው ውድድር የተሻለ ርቀት መጓዝ ይችላል፡፡ ዛናኮ በዛምቢያ ኤምቲኤን ፋዝ ሱፐር ሊግ በአምስት ጨዋታዎች ያሳካውን 10 ነጥብ ተከትሎ ሁለተኛ ነው፡፡ ዛናኮ በተለይ ከሜዳው ውጪ በቻምፒየንስ ሊግ የግብ ማስቆጠር ሪከርድ የተሻለ ነው፡፡ አሃሊ በተቃራኒው ሊጉን በሰፊ ርቀት እየመራ ሲሆን የተቆጠረበት የግብ መጠንም 6 ብቻ ነው፡፡

የዛሬ ጨዋታዎች

ኤቷል ደ ሳህል ከ ፎሮቫያሪዮ ደ ቤይራ

አል ሂላል ከ ኤል ሜሪክ

ዛማሌክ ከ ካፕስ ዩናይትድ

ዩኤስኤም አልጀር ከ አል አሃሊ ትሪፖሊ

ኤስፔራንስ ደ ቱኒዝ ከ ኤኤስ ቪታ ክለብ

ዋይዳድ አትሌቲክ ክለብ ከ ኮተን ስፖርት

Leave a Reply