የ2017 ቶታል አፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ውድድር በሳምንቱ መጨረሻ በሚደረጉ ጨዋታዎች ሲጀመር ቅዳሜ 12:00 ላይ የአፍሪካው ሻምፒዮን ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ቅዱስ ጊዮርጊስን በፕሪቶሪያው ሉካስ ሞሪፔ ስታዲየም የሚያስተናግድበት ጨዋታ ትልቅ ግምት አግኝቷል።
የቀድሞው የአዳማ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የአጥቂ መስመር ተጫዋች ፍቅሩ ተፈራም ከደቡብ አፍሪካው ኪክኦፍ ድረገፅ ጋር ባደረገው ቆይታ የቀድሞ ክለቡ ለማሜሎዲ ሰንዳውንስ ፈተና እንደሚሆንበት ያለውን እምነት ገልጿል።
“ቅዱስ ጊዮርጊስ ትልቅ ክለብ ነው፤ በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ምድብ ውድድር ውስጥ መግባት የቻለውም በዕድል አይደለም።
“እመኑኝ፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለማሜሎዲ ሰንዳውንስ እጅግ ፈታኝ ይሆንበታል። በኢትዮጵያ ደረጃ ስናየው ቅዱስ ጊዮርጊስ ትልቅ አቅም አለው። ጥሩ ብቃት ያላቸው የሀገር ውስጥ ተጫዋቾች እና ሌሎች የውጪ ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾችንም የያዘ ቡድን ነው። በፋይናንስ አቅም በኩልም በሼህ መሐመድ ሁሴን አል አሙዲ በሚባሉ ከሰንዳውንሱ ባለቤት (ፓትሪስ ሞትሴፔ) በላይ አቅም ባላቸው ባለሃብት ስለሚደገፍ የፈለገውን ማግኘት የሚችል ቡድን ነው። ቅዱስ ጊዮርጊስ በኢትዮጵያ ውስጥ ትልቁ እና በደጋፊ ብዛት እና በውጤት አንደኛ የሆነው ክለብ መሆኑ ስለቡድኑ የተወሰነ መረጃ የሚሰጥ ነው።”
አምና ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ወደ ምድብ ውድድሩ ለመጀመሪያ ጊዜ ገብቶ ዋንጫውን ማንሳት የቻለበትን ታሪክ ዘንድሮ ቅዱስ ጊዮርጊስ መድገም የሚችልበት አቅም እንዳለው ፍቅሩ ጨምሮ ገልጿል።
“የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታዎችን ተመልክቻለሁ፤ ከተከላካይ እስከ አጥቂ ድረስ ጥራት ያላቸው ተጫዋቾችን ይዘዋል። ከሰንዳውንስ ጋር መፎካከር የማይችሉበት ምንም አይነት ምክንያት አላየሁም። እንደውም ክለቡ አምና ሰንዳውንስ እንዳደረገው ሁሉ ከታች ተነስቶ የቻምፒዮንስ ሊጉን ዋንጫ የማንሳቱ አቅም አለው።”
ፍቅሩ ፈረሰኞቹ በደቡብ አፍሪካ ከሚገኙ በርካታ ኢትዮጵያውያን ሰፊ ድጋፍ እንደሚያገኝ እና በቁጥር ከሰንዳውንስ ያልተናነሰ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊ በስታዲየሙ እንደሚገኝ ተናግሯል።
” በስታዲየሙ ከሚገኘው ኢትዮጵያዊ ደጋፊ ቁጥር እንፃር ቅዱስ ጊዮርጊስ በሜዳው የሚጫወት ነው የሚመስለው። በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የኢትዮጵያ ማህበረሰብ በውስጡ መከፋፈል ስለሌለበት ቅዱስ ጊዮርጊስን ለመደገፍ በነቂስ ወደ ስታዲየም ይመጣል። እኔም ራሴ ቅዳሜ አንዱ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊ ነኝ።”
ግዙፉ አጥቂ እ.ኤ.አ. በ2006 ቅዱስ ጊዮርጊስን ለቅቆ ኦርላንዶ ፓይሬትስን ከተቀላቀለ በኋላ በ3 አህጉራት በሚገኙ ክለቦች በመጫወት ዓለምን አካሏል። ፍቅሩ በደቡብ አፍሪካ ብቻ ፓይሬትስን ጨምሮ ለ6 ክለቦች የተሰለፈ ሲሆን በአሁኑ ጊዜም በደቡብ አፍሪካ ፕሪምየር ሶከር ሊግ በሚሳተፈው ሃይላንድስ ፓርክ እየተጫወተ ይገኛል።